MAY Day 2021

ሜይ ዴይ ፳፻፲፫

በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሠራተኞች መብት እየተጣሰ መኾኑን ገልጿል

ኢዛ (ዓርብ ሚያዝያ ፳፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 30, 2021)፦ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) በአሁኑ ወቅት በተያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየታየ ያለውን ግጭት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በመተባበር እና በመመካከር ማስቆም እንደሚገባቸው አስታወቀ። የሠራተኞች መብት እና ጥቅሞች በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተጣሰ መኾኑንም ገለጸ።

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ነገ የሚከበረውን የዓለም የሠራተኞ ቀን (ሜይ ዴይ) በማስመልከት ባወጣው መግለጫ፤ በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አቋሙን ያንጸባረቀበት ነው። በተለይ ከወቅታዊው የአገራችን ሁኔታ በየቦታው የሚታዩ ግጭቶች መንግሥት እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት፣ እንዲሁም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት ግጭቶቹን ለማስቆም በጋራ መሥራት እንደሚገባቸው አመልክቷል።

ከሠራተኞች መብት አንጻርም አሁንም በአብዛኞቹ የግል ተቋማት የሠራተኞች መብት እና ጥቅሞችን የሚመለከቱ ሕጎች እየተከበሩ እንዳልኾኑም በመግለጽ፤ መንግሥት ሕጉን እንዲያስከብር በዚሁ መግለጫው አሳስቧል። በትግራይ ክልል የግል ድርጅት ሠራተኞች ላይም እየደረሰ ነው ያለውን ችግር ጭምር የያዘው የኢሠማኮ መግለጫ፤ በሌሎች ጉዳዮችም ሊኾን ይገባል ያለውን አቋሙን አስታውቋል።

ኢሠማኮ የዓለም ሠራተኞች ቀንን (ሜይ ዴይን) በማስመልከት ያወጣው ሙሉ መግለጫ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

የዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን (ሜይ ዴይ) በዓል ምክንያት በማድረግ ከኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ፤

የተከበራችሁ በየደረጃው ያላችሁ የሠራተኛ ማኅበራት መሪዎች
የተከበራችሁ መላው የኢትዮጵያ ሠራተኞች፣

በመጀመሪያ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ132ኛ ጊዜ በአገራችን ደግሞ ለ46ኛ ጊዜ በምናከብረው ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን (ሜይ ዴይ) እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን እላለሁ። እንዲሁም ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮችም እንኳን ለትንሳኤ በዓል አደረሳችሁ እላለሁ።

በመቀጠልም ይህንን መግለጫ ለመዘገብ በዚህ ሥፍራ ለተገኛችሁ የሚድያ ተቋማትና ባለሙያወች በኢሠማኮ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና በራሴ ስም ምስጋናየን አቀርባለሁ።

የዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን (ሜይ ዴይ) ዋና ዓላማ ለሠራተኞች መብትና ጥቅም መከበር መሥዋዕት የኾኑ ቀደምት ሠራተኞችን በመዘከርና ለቀጣይ የሠራተኛው የትግል አንድነት ቃል ኪዳን ለማደስም ጭምር ነው። እንደሚታወቀው ለዓለም አቀፉ የሠራተኞች ቀን ሜይ ዴይ በዓል በየዓመቱ መከበር መነሻ የኾነው ሠራተኞች በብናኝና በጭስ ጭጋግ በደበዘዙ ፋብሪካዎች ውስጥ በቀን ከ10 እስከ 20 ሰዓታት ለመሥራት ይገደዱ በነበሩባቸው ዘመናት ለሥራ ሰዓታት መቀነስና ለተሻለ ክፍያ በተደረገው ትግል ውስጥ የአሜሪካና የካናዳ ሠራተኞች ማኅበራት ኅብረት እ.ኤ.አ በ1884 አጠቃላይ የሥራ ማቆም እርምጃ ለመውሰድ በወሰነው መሠረት "የሄይማርኬት ሁከት" በመባል በሚታወቀው በችካጐ እ.ኤ.አ የሜይ 1/1886 የሥራ ማቆም እርምጃ በርካታ ሠራተኞች በፖሊሶች በመገደላቸውና "የአድማ አነሳሽ" የተባሉ መሪዎች በስቅላት ሞት በመቀጣታቸው እ.ኤ.አ በ1889 ፓሪስ ላይ የተጠራው ሁለተኛው የሠራተኞች ህብረት መሥራች ጉባዔ ሜይ 1 ቀን ከ1890 ጀምሮ የሠራተኞች ቀን ሜይ ዴይ ዕለቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበር ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ነው።ይህን የመሰለው የሠራተኞች የበርካታ ዓመታት ትግል ውጤት በዓለም መንግሥታት ማኅበር (League of Nations) ሥር አሠሪዎች ሠራተኞችና መንግሥታት በሦስትዮሽ በጋራ ጉዳዮች ላይ ለሚመክሩበት የዓለም ሥራ ድርጅት (ILO) እ.ኤ.አ በ1919 መቋቋምና ከሠራተኞች የሥራ ሰዓታትና የሙያ ደኅንነትና ጤንነት ጥበቃ እስከ በነፃነት መደራጀትና መደራደር መብቶች ድረስ በርካታ ጉዳዮችን ያካተቱ ስምምነቶችንና ምክረ ሃሳቦችን ሲያጸድቅና አባል አገራትን ሲያስፈርም ቆይቷል።

እንደሚታወቀው በአገራችን ኢንዱስትሪው ዘግይቶ የተቋቋመ ቢኾንም የኢትዮጵያ ሠራተኞች እንደሌሎች አገሮች ሁሉ ለመብትና ጥቅማቸው መከበር ታግለው መሥዋዕትነት ከፍለዋል። ከነዚህም ውስጥ እነ አቶ አበራ ገሙ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው።

የተከበራችሁ የሠራተኛ ማኅበራት መሪዎች
የተከበራችሁ መላው የኢትዮጵያ ሠራተኞች፣

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማሕበራት ኮንፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የዘንድሮውን የሜይ ዴይ በዓል "የኮሮና ወረርሽኝን እየተከላከልን፤ በመደራጀት ለሰላምና ለምርታማነት እንሠራለን!" በሚል መሪ ቃል እንዲከበር የወሰነው፤ የኮሮና ወረርሽኝ አገራችንን ጨምሮ በመላው ዓለም የሚገኙ ሠራተኞችም ላይ በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ እያደረሰ እና የብዙ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለ፤ ሃያላን መንግሥታትን ሳይቀር ከባድ ፈተና እያስከተለባቸው ከመኾኑም በላይ፤ የተገኘው ክትባትም ለአፍሪካ አገራት ተደራሽነቱ ውስን በመኾኑ ያለን አማራጭ የወረርሽኙ የመተላለፊያ መንገድ በሰዎች ንክኪና ትንፋሽ በመኾኑ እጅግ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባን ለማመላከት ነው።

በተመሳሳይ መልኩ በመሪ ቃሉ የተጠቀሰው፤ “መደራጀት” የሚያመለክተው ለሠራተኛው መብትና ጥቅም መከበር ከሚኖረው አንኳር ተግባር በዘለለ ሠራተኛው መደራጀት የሚችለው የተረጋጋ እና ሰላሙ የተጠበቀ አገር ሲኖር መኾኑን ለማስገንዘብ ነው። አሁን እንደሚታየው በአንዳንድ አካባቢዎች በሚፈጠረው ግጭት የንጹሀን ዜጎች ሕይወት እየጠፋ፤ እየተፈናቀሉና ንብረት እየወደመ በመኾኑ፤ መፍትሄው ለመንግሥት ብቻ ኃላፊነትን ከመተው ይልቅ ሁላችንም በምንሠራበት የሥራ ቦታ፤ በምንኖርበት መንደርና በምንዝናናባቸው ቦታዎች ሁሉ ሳይቀር ለሰላም መረጋገጥ በኃላፊነት መንፈስ መሥራት እንደሚጠበቅብንና፤ በሌላ በኩልም የአገር ኢኮኖሚን ለማስቀጠል ሠራተኞች በመደራጀት ምርታማነት በማሳደግ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚቻል በማሰብ መሪ ቃሉ ሊመረጥ ችሏል። በዚህ መሠረት ይህን ሜይ ዴይ በዓል ስናከብር የምንጠይቀው፤

1. በአገራችን በተለያዩ ቦታዎች እየተፈጠረ ያለው ግጭት ለዘላለም አብረው የኖሩትን ንጹኃን ሕዝቦች በማለያየት የሚገኝ ትርፍ ባለመኖሩ፤ ሕዝባችን ሰላሙ እንዲጠበቅ፤ ተከባብሮ መኖር እንዲችልና የማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር ሕይወት እንዳይጠፋ መንግሥት፤ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶችና የፖለቲካ ፓርቲዎችም ጭምር በኃላፊነት ስሜትና በሰከነ መልኩ በመወያየትና በመነጋገር በየቦታው የሚፈጠሩ ግጭቶች ቆመው ሰላም እንዲፈጠር በጋራ በመተባበር እንድንሠራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

2. ተባብሮና ተከባብሮ አንድ ላይ ከመቆም ይልቅ ወንድም ወንድሙን ሲገድል መስማትና ማየት ውርደት እንጂ እድገትና ስልጣኔ አይደለም። ጤናማ የኾነ ሰው ማለት አንዱ ለሌላው በመከራ ጊዜ ከጎኑ ሲቆምና ከችግር ሲያወጣው ነው። ማንም ሰው ከማንም በታች ወይም ከማንም በላይ አይደለም። እግዚሀብሄር ሁሉንም የፈጠረው እኩል ነው። ማንም ሕዝብ ከማንም ሕዝብ የበላይ ወይም የበታች አይደለም። ሁሉም ሕዝቦች እኩል ናቸው። ይህንን ከልብ አምነንና ተቀብለን የጋራ መፍትሔ እንድንፈልግ በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

3. እኛ ሠራተኞች ወጥተን የምንገባው፤ሠርተን መኖር የምንችለው ሰላም ሲኖር ብቻ መኾኑን በመገንዘብ ከላይ እስከ ታች በተደራጀ መንገድ የአገር ሰላም እንዲጠበቅ መላው ሠራተኛ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ እናሳስባለን።

4. ሰላም የሰፈነበት አገር፤የተረጋጋ ኢንዱስትሪ እንዲፈጠር በማድረግ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ያግዛል። የሰላም ጉዳይ የመንግሥትና የአሰሪው ወይም የሌላ አካል ጉዳይ ብቻ ሳይኾን የሠራተኛውም አጀንዳ በመኾኑ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብሮ ለመሥራት ዝግጁ መኾናችንን እናረጋግጣለሁ።

5. የሠራተኛው መብትና ጥቅሞች በአገሪቷ ሕግ መሠረት በአብዛኛው የግል ድርጅቶች በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተከበረ አይደለም። በተመሳሳይ መልኩ በጥቂት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችም ሳይቀር የመደራጀትና የመደራደር መብታችን ያልተከበረ ስለኾነ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ስምምነቶች፤ ሕገ-መንግሥቱንና የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጁን እንዲያስከብሩልን አጥብቀን እንጠይቃለን።

6. በሥራ ቦታ የሙያ ደኅንነትና ጤንነት መከላከልን አስመልክቶ የወጡ ሕጎች በአብዛኛው አሰሪዎች የማይከበሩ በመኾኑ በሠራተኛው ላይ የአካል ጉዳትና ሞት እያስከተለ ይገኛል። በመኾኑም የሠራተኛው የሙያ ደኅንነትና ጤንነት አለመጠበቅ ጉዳቱ ለሠራተኛው ብቻ ሣይኾን ለድርጅቶች ብሎም ለአገር ኢኮኖሚ በመኾኑ፤ የሥራ ቦታ የሙያ ደኅንነትና ጤንነትን አስመልክቶ የወጡ ሕጎች ተግባራዊ እንድኾኑ አጥብቀን እንጠይቃለን።

7. በመላው ዓለም ኾነ በአገራችን በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ኢኮኖሚው የተቀዛቀዘ በመኾኑ የዋጋ ግዥበት መፈጠሩን ተከትሎ በአንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ምክንያት ሠራተኛው በሚያገኘው እጅግ በጣም ዝቅተኛ ደመወዝ የዕለት ጉርሱን መሸፈን ስላልቻለ መንግሥት የጀመረው ቁጥጥር ጠበቅ እንዲልና ተከታታይ እንዲኾን እንጠይቃለን።

8. በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በትግራይ ክልል በተፈጠረው ችግር አንዳንድ የግል ድርጅቶች ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው በመኾኑ፤ አንዳንዶቹም የማምረቻ መሳሪያቸው በከፊል የተጎዱት ማስተካከያ ተደርጎ በቀላሉ ሥራ መጀመር ባለመቻላቸው፤ በነዚህ ድርጅቶች ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞች በከፍተኛ ችግር ላይ ስለሚገኙ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው እና የመልሶ ማቋቋም ሥራ እንድሠራ አበክረን እንጠይቃለን።

9. በታላቁ የህዳሴ ግድባችን ዙሪያ ከታችኛው ተፋሰሥ አገራት ጋር የሚደረገው ድርድር እንደተጠበቀ ኾኖ የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በተያዘለት የጊዜ ሠሌዳ መሠረት ለማከናወን መንግሥት የወሰደውን አቋም እንደግፋለን። የኢትዮጵያ ሠራተኞችም ከዕለት ጉርሳችሁ ቀንሳችሁ ድጋፍ ስታደርጉ እንደነበር ሁሉ ዛሬም ድጋፋችሁን እንድትቀጥሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

10. 6ኛው አገራዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ የመሠረታዊ ማኅበራትና የኢሠማኮ ጠቅላይ ምክር ቤት በ2011 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ተወያይቶ ገለልተኛ በመኾን የመራጮች ስልጠና የመስጠትና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ከመሥራት በተጨማሪ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች መድረክ ማዘጋጀትና ምርጫውን እንድንታዘብ በወሰነው መሠረት ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ፍቃድ አግኝተን እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንገኛለን። በዚሁ አጋጣሚ የምርጫ ካርድ ያልወሰዳችሁ ሠራተኞች በቀሩት ቀናት እንድትመዘገቡ እና የመምረጥ ዲሞክራሲያዊ መብታችሁን እንድትጠቀሙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

በመጨረሻም የዘንድሮው የሜይ ዴይ በዓል አከባበር ስረዓትን በተመለከተ ከላይ እንደገለጽኩት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተሰባስቦ ማክበር ስለማይቻል፤ በአዲስ አበባ ደረጃ ብቻ የተወሰኑ ሠራተኞች በተገኙበት የኮቪድ ስርጭቱን ጥንቃቄ በማድረግ ከአድስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር በሸገር መናፈሻ ፓርክ የሚከበር ሲሆን፤ በክልሎች ደግሞ፤የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በሚድያ በሚያስተላልፉት መግለጫ መኾኑን እየገለጽኩ፤ መላው የኢትዮጵያ ሠራተኞች የመጣብንን ወረርሽኝ ለመከላከልና ሰላማችንን ለማስጠበቅ፤ ከአሠሪዎች፤ ከመንግሥትና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እያደረጋችሁ ያለውን ድጋፍ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉና በተጨማሪም፤ ሰላማችንና አገራችንን ተባብረን እንድናሻግር፤ እንድሁም ያለፉትን ሰማእታት ሠራተኞች ስንዘክር እኛም ቃል ኪዳናችንን እንድናድስ መልእክቴን አስተላልፋለሁ።

"የኮሮና ወረርሽኝ እየተከላከልን፤ በመደራጀት ለሰላምና ለምርታማነት እንሠራለን!"
ሜይ ዴይ ለዘላለም ይኑር!!!
አመሰግናለሁ!
ሚያዝያ 21 ቀን 2013 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ