ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዮሴፍ

የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊና የሲዳማና የጌዲዮ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዮሴፍ

“ፓትርያርኩ የሲኖዶሱን ይሁንታ ሳያገኙ መግለጫ መስጠት አይችሉም” አቡነ ዮሴፍ

ኢዛ (ሰኞ ግንቦት ፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. May 10, 2021)፦ ሰሞኑን አነጋጋሪ ኾኖ የሰነበተው ብፁዕ ወ ቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓርትሪያክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የሰጡት መግለጫ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሳይኾን፤ የግላቸው መኾኑን አቡነ ዮሴፍ አስታወቁ።

ሾልኮ የወጣ ነው በተባለውና ፓትርያርኩ ሰጡት በተባለው መግለጫቸው ላይ፤ ዛሬ ሰኞ ግንቦት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊና የሲዳማና የጌዲዮ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዮሴፍ በሰጡት መግለጫ፤ የፓትርያርኩ መግለጫ የሲኖዶሱን አሠራር ያልተከተለ፤ እንዲሁም ከሲኖዶሱ እውቅና ውጭ የተከናወነ እንደኾነ አስታውቀዋል።

ቅዱስ ሲኖዶሱ እና ቋሚ ሲኖዶሱ ሳይወስን ፓትርያርኩ በግላቸው ቤተ ክርስቲያኒቱን እና ቅዱስ ሲኖዶሱን ወክለው መግለጫ መስጠት እንደማይችሉ በፓትርያርኩ መግለጫ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት አቡነ ዮሴፍ ገለጸዋል።

ከዚህ ቀደም መግለጫዎች የተሰጡትና የሚሰጡት የምልዓተ ጉባዔውና የቋሚ ሲኖዶሱ አዎንታ ሲያገኝ እንደኾነ ያብራሩት አቡነ ዮሴፍ፤ ሰሞኑን በፓትርያርኩ የተሰጠው መግለጫም የሲኖዶሱን አሠራር ያልተከተለ፤ እንዲሁም ከሲኖዶሱ እውቅና ውጭ የፈጸሙት መኾኑን አመልክቷል።

በፓትርያርኩ መግለጫ ዙሪያ አጀንዳ ተይዞበት የሚነጋገርበት መኾኑም በዛሬው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።

የዛሬውን የአቡነ ዮሴፍ መግለጫ ተከትሎ አንዳንድ ወገኖች እየሰጡ ካሉት አስተያየት ውስጥ፤ በአጠቃላይ ሲታይ ሁለት ዐይነት ናቸው። የአቡነ ዮሴፍን መግለጫ የደገፉና ተገቢ ነው የሚሉ አንደኞቹ ሲሆኑ፤ በተቃራኒው ደግሞ “ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በግላቸው ያስተላለፉ መልእክት እንጂ፤ የሲኖዶሱ አለመኾኑ እየታወቀ፤ አቡነ ዮሴፍ መግለጫ መስጠት አያስፈልጋቸውም ነበር” ሲሉ የተደመጡ አሉ። አንዳንዶችም፤ “ፓትርያርኩ የግል መልእክት ለማስተላለፍ ሲኖዶሱን ማስፈቀድ ይገባቸዋልን? አቡነ ዮሴፍስ ሲኖዶሱ ፈቅዶላቸው ነው ይሄንን መግለጫ ሊሰጡ የቻሉትን?” በማለት የሚከራከሩ አሉ።

አነጋጋሪ ኾኖ የሰነበተው እና ብፁዕ ወ ቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ያስተላለፉትን የቪዲዮ መልእክት ለማየትና ለማድመጥ የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑ! (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ