በእንግሊዝ ሊሸጡ የነበሩ የኢትዮጵያ ቅርሶች ጨረታ ታገደ
ጥንታዊ በቆዳ የተለበጠ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከቆዳ ከተሠራው የመጽሐፍ ቅዱሱ መያዣ ጋር
ለጨረታ ቀርቦ የነበረው መጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊና መጀመሪያ ከተጻፉት ጥቂት ቅጂዎች ውስጥ እንደኾነ ይገመታል
ጨረታውን ያሳገደው እንግሊዝ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ነው
ኢዛ (ሐሙስ ሰኔ ፲ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 17, 2021)፦ አጼ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ከእንግሊዞች ጋር ባደረጉት ውጊያ ሚያዝያ 10 ቀን 1860 ዓ.ም. ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ፤ በእንግሊዝ ወታደሮች ተዘርፈው የተወሰዱና በብሪድፖርት፣ ዶርሴት ከተማ ሊሸጡ የነበሩ የኢትዮጵያ ቅርሶች እንዳይሸጡ ማሳገደ መቻሉን በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።

መሠረቱን በእንግሊዝ ያደረገውና በብሪድፖርት፣ ዶርሴት ከተማ የሚገኘው “ቡስቢ” የተሰኘው አጫራች በዛሬው ዕለት (ሐሙስ ሰኔ 10 ቀን 2013 ዓ.ም.) በጨረታ ሊሸጣቸው የነበሩት እነዚህ የኢትዮጵያ ቅርሶች፤ ጥንታዊ በቆዳ የተለበጠ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከቆዳ የተሠራ የመጽሐፍ ቅዱሱ መያዣ እና ከቀንድ የተሠሩ በብር የተለበጡ ጥንታዊ ዋንጫዎች እንደነበሩ ታውቋል።
እነዚህ ቅርሶች ሁለት የተለያዩ ጨረታዎች ወጥቶባቸው የነበረ ሲሆን፤ መጽሐፍ ቅዱሱ ከነ የቆዳ መያዣው ለብቻ፣ ከቀንድ የተሠሩት ዋጫዎች ደግሞ ለብቻ ነበሩ። የሁለቱ ጨረታዎች ዋጋ 700 የእንግሊዝ ፓውንድ (43 ሺህ ብር) እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።
“የኢትዮጵያ ኮፕቲክ መጽሐፍ ቅዱስ” እንደኾነ ጨረታው ላይ የተጠቀሰ ሲሆን፤ “ኮፕቲክ” የሚባለው መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ የጥንት እና መጀመሪያ ላይ ከሺህ ዓመታት በፊት የተጻፉት እንደኾኑ ይነገራል። ከዚህም ሌላ “ኮፕቲክ” የኾኑት መጽሐፍ ቅዱሶች በዓለም ላይ የሚገኙት ከአንድ ሺህ ቅጂ በላይ እንደማበልጡ ይነገራል።
እነዚህ የዛሬ 153 ዓመት ከኢትዮጵያ የተዘረፉ ቅርሶች በዚህ ታዋቂ በኾነውና “ቡስቢ” በተሰኘው የጨረታ ኩባንያ በኩል ሊሸጡ መኾናቸውን የተረዳውና መረጃ የደረሰው በሎንዶን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ ለጨረታ ኩባንያው ደብዳቤ ጽፏል። በዚህ ደብዳቤ ላይም፤ “ጨረታው ሥነምግባር የጎደለውና ከዚያም በከፋ ሁኔታ በጦርነትና በምርኮዎች ተጠቃሚ መኾን የሚፈልጉ ሰዎችን ቀጣይነት ያለው ዑደት የሚያሳይ ነው” በማለት ለቡስቢ መግለጹ ታውቋል።
ቡስቢ ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከቅርሶቹነ በቡስቢ በኩል ለጨረታ አቅራቢ ከኾነው ሻጭ ጋር በመነጋገር ጨረታውን አግዶታል።
የኢትዮጵያ ኤምባሲ የእገዳው ውሳኔ ከመቅደላ የተዘረፉትን ሁሉንም የኢትዮጵያ ቅርሶች ከእንግሊዝ ተቋማት እንዲመለሱ ለማድረግ ለታለመው ግብ አበረታች እርምጃ ነው ብሏል። “መቅደላ በእንግሊዝና በኢትዮጵያ መካከል ካለው የጋራ ታሪክ አንጻር መቅደላ በጣም ዋንኛ ከመኾኑ አንጻር፤ የዛሬው ቀን ታላቅ ነው። የእገዳ እርምጃው ደግሞ ትንሽ እርምጃ ነው” ሲሉ የኤምባሲ ቃል አቀባይ መናገራቸው ታውቋል። (ኢዛ)



