Ethiopian Human Rights Commission

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮምሽን (ኢሰመኮ)

በተፎካካሪ ፓርቲ አባላቶች እና ደጋፊዎች ላይ ግድያ፣ ድብደባ እና የአካል ጉዳት ደርሷል

ኢዛ (ቅዳሜ ሰኔ ፲፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 26, 2021)፦ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮምሽን በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ 2013 ላይ ኮምሽኑ ያካሔደውን አጠቃላይ ክትትልና ግምገማ፣ እንዲሁም ተፈጸሙ ያላቸውን ግድፈቶች የሚያመላክተውን የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱን ይፋ አደረገ። በተፎካካሪ ፓርቲ አባላቶች እና ደጋፊዎች ላይ ግድያ፣ ድብደባ እና የአካል ጉዳት መድረሱን ሪፖርቱ አካትቷል።

እስካሁን ምርጫውን በተመለከተ በገለልተኝነት ከቀረቡ ሪፖርቶች ሁሉ ዝርዝር ነገሮችን የያዘው ይህ የኢሰመኮ ሪፖርት፤ በአሥራ አንድ ገፆች የተሰነደ ሲሆን፤ የምርጫ ሒደቱን ከዚያም በየአካባቢው ተፈጸሙ የተባሉትን ችግሮችን ያካተተ ከመኾኑም በላይ ምክረ ሐሳቦችንም አካትቶ የያዘ ነው።

ምርጫውን አጠቃላይ ሒደት የደረሰባቸውን ቦታዎች በመጥቀስ ጭምር የተጠናከረው ሪፖርት፤ ግድያና የአካል ጉዳት፣ እስር፣ ማስፈራራትና ማስገደድ፣ ታዛቢዎችን፣ የሲቪክ ማኅበራትንና ጥበቃ፣ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የነበረው ተደራሽነት፣ የጸጥታ አካላት ሚና፣ የጸጥታ ሁኔታና ከምርጫ አስተዳደር ጋር የነበረው ሁኔታ በሚል በስምንት አንኳር አንኳር ነጥቦች በመከፋፈል ሪፖርቱ ዘርዘር ያለ ማብራሪያ ሰጥቷል።

የምርጫ ሒደቱ በሰላማዊ መንገድ የተካሔደ ስለመኾኑም የሚጠቅሰው ይኸው ሪፖርት፤ የተወሰኑ የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ክፍተት የታየ ቢኾንም በአብዛኛዎቹ ቦታዎች ላይ የጐላ ወይም የተስፋፋ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳልነበረም ጠቅሷል።

ኢሰመኮ ዛሬ ይፋ ባደረገው ሪፖርት፤ በአንዳንድ ቦታዎች የኮምሽኑ አካላት ክትትል ለማድረግ ያልቻሉበት ሁኔታ ተፈጥሮባቸው እንደነበር ያመለከተ ሲሆን፣ እንዲህና መሰል ታዩ ያላቸውን ግድፈቶች በዚሁ ሪፖርት ውስጥ አካትቷል።

ከምርጫው ጋር በተያያዘ ግድያና የአካል ጉዳትን በተመለከተ ቅኝቱን ባስቀመጠበት የሪፖርቱ ክፍል ውስጥ ተፈጸሙ ያላቸውን ግድያዎችና ጥቃቶች አመላክቷል።

ኮምሽኑ በዘንድሮው ምርጫ ድምፅ መስጫ ቀን የተደረገ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ቀዳሚ ሪፖርት በሚል ርዕስ ዛሬ ይፋ የተደረገው ሙሉ ሪፖርት በፒ.ዲ.ኤፍ. ለማንበብ እዚህ ይጫኑ! (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ