የአፍሪካ የገንዘብ ሚኒስትሮች መፍትሔ ፍለጋ ሊወያዩ ነው

Ethiopia Zare (እሁድ ጥቅምት 23 ቀን 2001 ዓ.ም. November 2, 2008)፦ የዓለም የገንዘብ ቀውስ በአፍሪካ ልማትና ዕርዳታ ላይ ተጽኖ በማሳደሩ፣ የአፍሪካ ሀገሮች የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትሮች ስብሰባ ሊያደርጉ መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኮሚሽነር አስታወቁ።

 

ኮሚሽነሩ ዶ/ር ማክስዌል ማክዌዜ ለምባ (Maxwelle M. Mkwezalamba (DR)) ረቡዕ ዕለት በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ የዓለም የገንዘብ ቀውስ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ላይ በተለየ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ መግለጫ ሰጥተዋል።

 

ዶ/ር ማክስዌል እንደገለፁት፤ የገንዘብ ቀውሱ አፍሪካን በምን ያህል ሊጎዳት እንደሚችል፤ አንድ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የአፍሪካ ልማት ባንክ (ADB) እና አፍሪካ ሕብረት (AU) በቱኒዚያ አንድ ስብሰባ አዘጋጅተዋል።

 

በአፍሪካ ሀገራት የገንዘብ ሚኒስትሮች መካከል የሚደረገው ስብሰባ በኅዳር 3 ቀን 2001 ዓ.ም. (November 12, 2008) በቱኒዚያ የሚደረግ ሲሆን፤ የዓለም የገንዘብ ቀውስ፤ አፍሪካን ምን ያህል ይጎዳታል?፣ በአፍሪካ ልማት ባንክ ላይ የሚያሳድረው ተፅኖ ምን ያህል ነው?፣ የዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ለአፍሪካ በሚሰጡት ዕርዳታ ያስተጓጉላል ወይ? የአፍሪካ ሀገራት ካደጉት ሀገሮች ጋር ያላቸውን የንግድ ግንኙነት ያበላሸዋል ወይ? በሚሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገው በሚደርሱበት ድምዳሜ አንድ የጋራ መግለጫ እንደሚያወጡ ዶ/ር ማክስዌል ተናግረዋል።

 

ለውይይቱ ይረዳቸው ዘንድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ECA) እና የአፍሪካ ልማት ባንክ (ADB) በጉዳዩ ላይ በጋራ ያዘጋጁት ጥናት መነሻ እንደሚሆናቸው ዶ/ር ማክስዌል ገልፀው፤ የሚወጣው የአቋም መግለጫ ለቡድንሃያ (G20) ሀገራት ስብሰባ ላይ ይቀርባል ተብሏል።

 

የገንዘብ ቀውሱ በአሁኑ ሰዓት በአፍሪካ ሀገሮች ላይ ያሳደረው ተፅኖ ምን እንደሆነ ተጠይቀው ዶ/ር ማክስዌል ሲመልሱ፤ ለአፍሪካ ሀገራት ዕርዳታ ከሚሰጡ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ጋር ባደረጉት መደበኛ ያልሆነ ውይይት (Informal discussion) የዓለም የገንዘብ ቀውስ ለአፍሪካ ሊሰጥ ቃል በተገባው ዕርዳታ ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር መረዳታቸውን ጠቁመዋል።

 

በሀብት የበለፀጉት ሀገራት በቡድን ስምንት (G8) ስብሰባቸው ላይ፤ የአፍሪካን የሚሌኒየም የልማት ግብ (Millennium development Goal [MDG]) በታቀደው ግዜ ለማሳካት ተጨማሪ ዕርዳታ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም የገንዘብ ቀውስ ይህን ዕርዳታ ሊያስተጓጉለው ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ጠቁመዋል።

 

የአፍሪካ የሚሊኒየም የልማት ግብ በ2015 ድህነትን በግማሽ ለመቀነስ የሚል ቢሆንም፤ በዓለም የገንዘብ ቀውስ ይህ እንዳይሆን ተጽዕኖ ያሳድራል የሚል ስጋት አላቸው።

 

ከሁለት ሣምንታት በፊት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ሚ/ር አብዱላዩ ጃኔ በሰጡት መግለጫ፤ የገቢና ሀብት አለመመጣጠን፣ የአየር ለውጥ፣ የምግብ ዋጋ ጭማሪና የዋጋ ንረት የዓለምን ህዝብ እየተፈታተኑ ያሉ ችግሮች መሆናቸውን ገልፀው፤ በዚህ ላይ የዓለም የገንዘብ ቀውስ ሲጨመርበት በአፍሪካ የሚካሄዱ የኢኮኖሚ ልማትና የዕድገት ሂደቶችን ሊያስተጓጉል ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልፀው ነበር።

 

ከሁለት ሣምንት በፊት ተቃዋሚ የፓለቲካ ፓርቲዎት በፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ ባደረጉት ንግግር ላይ ባቀረቡት ዋሽን የዓለም አቀፍ የገንዘብ ቀውስ በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖን በሚመለከት መንግሥት ያስጠናው ጥናት እንዳለ ተጠይቀው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሲመልሱ፤ ”… በፋይናንስ ቀውሱ እየተናጉ ያሉት ትልልቅ መርከቦች ናቸው። ኢትዮጵያ በመንደር ውስጥ በሚገኝ ወንዝ አካባቢ ነች ያለችው፤ የኢትዮጵያን ኢኮኖማ ከዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ጋር አላጣመርነውም ገትረነዋል። በተለይ በአሁኑ ወቅት የማጣመሩን ሁኔታ አንቀበልም። ያምሆነ ይህ በጎም ሆነ ክፉ ተጽዕኖ ያሳድራል። ዕድገታቸው በመቀነሱ የነዳጅ ዋጋ ለጊዜው ቀንሷል፤ የብረት ዋጋም ቀንሷል። በዚህ ምክንያት ተጠቃሚ እንሆናለን። ከውጭ የሚመጡ ኢንቨስተሮች የፋይናንስ ችግር ሊገጥማቸው ይችላል። ሀገሮቹ ገበያቸው ሲናጋ ከኛ የሚገዙትን መጠን ሊቀንስ ይችላል። በዚህም ምክንያት ወደ ውጭ የምንልከው ዕቃ መጠናችን ሊጎዳ ይችላል። ግን ወደ ውጭ የምንልከው ዕቃ እዚህ ግባ አይባልም።” ሲሉ ምላሽ ሰጥተው እንደነበር ይታወሳል።

 

በኅዳር 3 የአፍሪካ የገንዘብ ሚኒስትሮች በጉዳዮ ላይ በቱኒዚያ በሚያደርጉት ስብሰባ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ሶፍያን አህመድ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!