እሁድ ጥቅምት 30 ካስቴልቮልቱርኖ መድረክ ላይ ራስዋን ከመሳትዋ በፊት(ፎቶ AP)

Maria Makeba, died 76

Ethiopia Zare (ኅዳር 1 ቀን 2001 ዓ.ም. November 10, 2008)፦ እውቋ የደቡብ አፍሪካ የፀረ-አፓርታይድ ታጋይ ድምፃዊት ማሪያ ማኬባ (ማማ አፍሪካ) ዛሬ ሰኞ ኅዳር 1 ቀን 2001 ዓ.ም. በ76 ዓመቷ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች። ህልፈተ ሕይወቷ ለበጎ ሥራ በመድረክ ላይ እየተጫወተች እንዲሆን ምኞቷ ነበር፤ ተሳካላትም።

 

ጣሊያን ሀገር ለካሴራታ ቅርብ በሆነችው ካስቴልቮልቱርኖ ውስጥ እሁድ ጥቅምት 30 ቀን ምሽት መድረክ ላይ እየዘፈነች በልብ በሽታ ራስዋን ስታ ስትወድቅ፤ ጣሊያናዊቷ ድምፃዊ ማሪአ ናዚኦናሌ ልትረዳት እንደሞከረች አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል። በማግስቱ ሰኞ ጠዋት ለደቡባዊ ኔፕልስ በምትቀርበው ከተማ ካስቴል ቮልቱርኖ በሚገኘው በፒኔታ ገራንዴ ክሊኒክ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች።

 

ኮንሰርቱ ተዘጋጅቶ የነበረው ባለፈው ሴፕቴምበር 19 ቀን 2008 እ.ኤ.አ. በካስቴልቮልቱርኖ ከተማ በጥይት ተደብድበው ለተገደሉት ስድስት አፍሪካውያን ስደተኞች በተጠራ የአንድነትና የትብብር መድረክ ላይ ነው። የተገደሉት አፍሪካውያን ከጋና፣ ከቶጎ እና ከላይቤሪያ የተሰደዱ ሲሆን፣ በግድያው የተጠረጠሩት ”ካሙራ” በመባል የሚታወቁት የአደንዛዥ ዕፅ ማፍያዎች ናቸው።

 

በህልፈተ ሕይወቷ ከችግር ለመላቀቅ እየታገሉ ያሉ አፍሪካውያን ወገኖችዋ ዘፈኖችዋን በራዲዮና በታክሲዎች ውስጥ እንዲያደምጡላት እንደተመኘችው ተሳክቶላታል። በዘመነ አፓርታይድ የማሪያ ማኬባ ዘፈኖች የዓለምን ህዝብ፣ በተለይም ደቡብ አፍሪካን ህዝብ ለፀረ-አፓርታይድ ትግል በማነሳሳቱ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ ብዙዎች ይስማሙበታል።

 

እ.ኤ.አ. በ1966 ዓ.ም. በምርጥ የፎልክ ቅጂ ከቤላፎንቴ ጋር በጋራ የግራሚ ሽልማት ማሪያ ማኬባ ማግኘቷ ይታወሳል። የግራሚ ሽልማቱን ያስገኘላቸው ”ምሽቱን ከቤላፎንቴና ከማኬባ” (An Evening With Belafonte/Makeba) የተሰኘው አልበም ሲሆን፣ በወቅቱ የጥቁር ደቡብ አፍሪካውያንን ላይ አፓርታይድ ያደርስ የነበረውን መቅሰፍትና መከራ ያንፀባርቅ ነበር።

 

ማሪያ ማኬባ በዓለም ላይ ምርጥ አርቲስቶች ጋር በጋራ በመሆን ሥራዎችዋን ለህዝብ አቅርባለች። ከእነዚህም ውስጥ ኒና ሲሞኔ፣ ዲዚ ጊሌስፒ፣ ሃሪ ቤላፎንቴ እና ፖል ሳይመን ተጠቃሽ ሲሆኑ፤ ለሟቹ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ. ኬኔዲ እና ለኔልሰን ማንዴላ ዘፈኖችዋን አቅርባ ታውቃለች።

 

ማማ አፍሪካ ጃዝ፣ ፎልክ እና የደቡብ አፍሪካ የሙዚቃ ስልቶችን ትጫወት የነበረ ሲሆን፣ ሙዚቃዎችዋ ለ30 ዓመታት በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ታግደው እንደነበር አይዘነጋም። ማሪያ ማኬባ ”ትዝ አለኝ የጥንቱ” የሚለውን የእውቁን የኢትዮጵያ ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠን ዘፈን በአማርኛ መዝፈኗ ይታወቃል። በዓለም ላይ ታዋቂ ከሆነችባቸው ዘፈኖችዋ ውስጥ ”ፓታ ፓታ” (Pata Pata) እና ”ዘ ክሊክ ሶንግ” (The Click Song) ተጠቃሽ ናቸው።

 

ማሪያ ዜነዚ ማኬባ ማርች 4 ቀን 1932 እ.ኤ.አ. በደቡብ አፍሪካ መዲና ጆሃንስበርግ ውስጥ ከእናትዋ ስዋዚ ሳንጎማ እና ከአባቷ ዞሳ የተወለደች ሲሆን፣ አባቷ ያረፈው የስድስት ዓመት ልጅ እያለች ነበር።

 

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!