የአማርኛ ቋንቋ በካንሳስ ዩኒቨርሲቲ ሊጀመር ነው
Ethiopia Zare (ዓርብ ኅዳር 5 ቀን 2001 ዓ.ም. November 14, 2008)፦ የካንሳስ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ አሜሪካን ጥናት ክፍል በ2009 እ.ኤ.አ. የአማርኛን ቋንቋ ለማስተማር 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ተደርጎለታል።
ዲፓርትመንቱ የተከፈተው ለበጎ አድራጎት እና ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ ኢትዮጵያ ለሚሄዱ ሰዎች በሚል ሃሣብ ነው። የውጭ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት ቋንቋውን የማያውቁት ሲሆን፣ አንዳንድ የአሜሪካ ነዋሪዎች እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲው አማርኛ ቋንቋን ማስተማሩ ወደ ኢትዮጵያ ለሚሄዱ ተጓዦች ሁኔታውን ያቀልላቸዋል ብለዋል።
የአፍሪካ-አሜሪካውያን ጥናት ተቋም ሊቀመንበር የሆኑት ፒተር ኡክፓኩዱ እንደገለፁት፣ ዲፓርትመንቱ የተከፈተው የአማርኛ ቋንቋ ለመማር ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በመብዛታቸው ነው።
በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የአፍሪካ ላይብሪያን አቶ ሽፈራው አሰፋ በዩኒቨርሲቲው አማርኛ ቋንቋን ለማስተማር ማሰቡ እንዳስደሰታቸው፤ ይህም የሆነበት ምክንያት አብዛኞቹ ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ቅርንጫፍ ስላላቸው ነው ብለዋል።
አማርኛ በሴማቲክ የቋንቋ ቤተሰብ ውስጥ የሚመደብ ሲሆን፣ በዋናነት በኢትዮጵያ በተወሰኑ የኤርትራና የሱዳን አካባቢዎችም የሚነገር ቋንቋ እንደሆነ ይታወቃል።



