በከባድ ዝናብ 52ሺ ሰዎች ተፈናቀሉ
ሦስት ሰዎች ሞቱ
Ethiopia Zare (ዓርብ ኅዳር 12 ቀን 2001 ዓ.ም. November 21, 2008)፦ በኢትዮጵያ ምሥራቃዊ ሶማሌ ክልል በያዝነው ወር መጀመሪያ የጣለው ከባድ ዝናብ ሦስት ሰዎች ሲገድል፣ ከ52ሺ የሚበልጡ ሰዎች ማፈናቀሉን የዕርዳታ ድርጅቶች ገልፀዋል።
በሶማሌ ክልል ጐዴ ዞን ቀላፎ ወረዳ፣ የዋቢ ሸበሌና ገናሌ ወንዞች ከመጠን በላይ ሞልተው በመፍሰሳቸው በትንሹ ከ52ሺ ሰዎች በላይ ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የዜና ወኪል (ኢሪን) ዘግቧል።
የዜና ወኪሉ እንደገለጸው ዝናቡ ለስድስት ቀናት አከታትሎ የጣለ ሲሆን፣ በጎርፉ ክፉኛ የተጐዳችው የቀላፎ ወረዳ ናት፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትም የጉዳቱን መጠን የሚያጣራ ግብረ ኃይል ወደአካባቢው ልከዋል።
በድርቅና ጐርፍ ክፉኛ እየተመታች ባለችው ኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ መሆኑን፣ የተባበሩት መንግሥታትና ሌሎች የዕርዳታ ድርጅቶች ገልፀዋል።



