Ethiopia Zare (ዓርብ ኅዳር 19 ቀን 2001 ዓ.ም. November 28, 2008)፦ ካዛንችስ ከሱፐር ማርኬት ፊት ለፊት፣ ከዘመን ባንክ በስተግራ በኩል የሚገኘው አልማዝ ላሊበላ ባርና ሬስቶራንት ረቡዕ ኅዳር 17 ቀን ከቀጠና ሦስት በመጣ ማዘዣ ቤቱን እንዲለቅ ተደረገ።

 

የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ንብረት የሆነው "አልማዝ ላሊበላ ባርና ሬስቶራንት" በኪራይ ለ27 ዓመታት ሲገለገሉበት እንደነበር ባለቤቷ ገልፀዋል።

 

ወ/ሮ አልማዝ እስከ 2001 ጥቅምት 30 ዓ.ም. ድረስ የቤቱን ኪራይ ከፍለው የጨረሱና የቤቱን ውል ግን ከ1993 ዓ.ም. ጀምረው እድሳት እንዳላደረጉ ይናገራሉ። ምክንያቱም ውሉን ለማደስ የኪራይ ቤቶች አስተዳደርን ሲጠይቁ፤ የቤቱ ባለቤቶች ይግባኝ በመጠየቃቸው ፋይላቸው ወደ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ መወሰዱ እንደተገለፀላቸው ተናግረዋል።

 

ለቅሬታ ሰሚ አካላት ቅሬታቸውን ቢያቀርቡም፣ ተሰሚነት አለማግኘታቸውንና ቤቱን ለኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ እንዲያስተላልፉ ከተነገራቸው ከ20 ቀን በኋላ ረቡዕ ኅዳር 17 ቀን ከጠዋቱ 4 ሰዓት ላይ፣ ከቀጠና ሦስት ማዘዣ ይዘው በመምጣት፣ ዕቃዎቹን በሙሉ ከቤት አስወጥተው ውጪ እንዳሳደሯቸው ይገልፃሉ።

 

ወ/ሮ አልማዝ እንደተናገሩት "ምንም ጥፋት የለብኝም፣ አሁን የሚያስጠይቀኝ ነገር የለም፣ ቀጠና ሦስት በመሄድ ችግሩን ለመጠየቅ ባደረኩት ጥረት ምንም ዓይነት ምላሽ የሚሰጠኝ ሰው አላገኘሁም። ለጊዜው ግን አዲስ አበባ ውስጥ ምንም ማረፊያ ስለሌለኝ ደብረዘይት ከተማ ወደሚገኘው የዶሮ እርባታ ድርጅቴ ዕቃዎቼን በማጓጓዝ ላይ ነኝ" ብለዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ