ደራሲና ባለቅኔ ኃይሉ ገ/ዮሐንስ የክብር እንግዳ ሆነው የኖታ ጨዋታ ናሙና ላጠኑ ምስክር ወረቀት ሰጡ

EMDG

Ethiopia Zare (እሁድ ኅዳር 21 ቀን 2001 ዓ.ም. November 30, 2008)፦ ከስምንት ወራት በፊት በስዊድን ዋና ከተማ በስቶክሆልም የተቋቋመው ”የኢትዮጵያ መዚቃና ድራማ ቡድን” (EMDG) ቅዳሜ ኅዳር 20 ቀን 2001 ዓ.ም. (November 29, 2008) ሥልጠናውን በሚሰጥበት አዳራሽ ውስጥ ለተሰበሰቡት እንግዶች የሙዚቃ ናሙና አሳይቷል። ሠልጣኞቹ ከክብር እንግዳው የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።

 

የቡድኑ ዋና ዓላማ የኢትዮጵያን ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች በምራብያውያን ኖታ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ለማስተማርና ባለሙያዎችን ለማፍራት ሲሆን፣ በማጎዳኘትም የድራማ ሥልጠና በመስጠት ትያትሮችን ለማቅረብ ዕቅድ እንዳለው የገለጹት የቡድኑ ሥራ መሪና የሙዚቃ መምህር የሆኑት አቶ ዘነበ በቀለ ናቸው።

 

አቶ ዘነበ አያይዘው እንደገለጹት ሙዚቃ በሀገራችን ምን መልክ እንደነበረው፣ ከየት ተነስቶ እዚህ እንደደረሰ፣ በአሁኑ ጊዜም ያለበትን ሁኔታ በሰፊው በማብራራት፤ ቀደም ባሉት ዘመናት ለኢትዮጵያ ሙዚቃ እድገት አስተዋጽዖ ያደረጉትን ታላታቅ ሰዎች በመጥቀስ ባለውለታ መሆናቸውን በመመስከር አመስግነዋል።

 

በአሁኑ ጊዜ ግን የኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ በመጥፋት እና በመበላሸት ላይ ግስጋሴ እንደያዘ ገልጠው፤ የቴዲ አፍሮ አይነት አዲስ የፈጠራ ሥራ ደግሞ በሌላ በኩል የሚያበረታታ እንደሆነ አስምረውበታል። የዚህ በአዲስ መልክ የጀመሩት የኖታ አሠራር የባህላዊ መሣሪያዎቻችንን በኖታ መዝግቦ ለማስቀመጥም እንደሚረዳ አስረድተዋል።

 

አቶ ዘነበ በቀለ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1958 ዓ.ም. ሲከፈት ትምህርት ቤቱን በመምራትና በመምህርነት ያገለግሉ የነበሩት የታዋቂው የሙዚቃ ጠበብት የፕሮፌሠር አሸናፊ ከበደ ተማሪና ከመጀመሪያዎቹ ምርቆች መካከል አንዱ ናቸው።

 

ከአቶ ዘነበ ገለጻ ቀጥሎ በክራር፣ በማሲንቆ፣ በቶም፣ በዋሽንትና በከበሮ መሣሪያዎች የኖታ ጥናት የሠለጠኑት ተማሪዎች በየተራ በተማሩበት የሙዚቃ መሣሪያ በመጫወት ለተመልካቹ የተለያዩ ዜማዎችን አሰምተዋል። እንዲሁም በትምህርቱ ጊዜ የገጠማቸውን በመግለጽ አቶ ዘነበ በቀለን አመስግነዋል። ከዚህ በመቀጠል በጋራ የተቀነባበረ ሙዚቃ አሰምተዋል። በተጨማሪ በአቶ ማትያስ ከተማና በወ/ሪት መስከረም ሦስት ግጥሞች ቀርበዋል።

 

በስተመጨረሻም ነዋሪነታቸው በስቶክሆልም የሆነው ታዋቂው ባለቅኔና ደራሲ ኃይሉ ገ/ዮሐንስ (ጎሞራው) የኖታ ጥናቱን ላደረጉት ተማሪዎች የምስክር ወረቀት እንዲሰጡ ተጋብዘው ወደ መድረኩ በመውጣት ግዕዝ እዝልና አራራይ የተባሉት የቅዱስ ያሬድ የዜማ መነሻዎች የዜማ ሁሉ ምንጭ መሆናቸውን ገልጸው፤ ዜማዎቹን በየተራ በማሰማት ልዩነታቸውን አስረድተው ለተመራቂዎቹ የምስክር ወረቀት ሰጥተዋል።

 

በመጨረሻም ”ውብ ሀገሬ” በሚል የሀገር ፍቅርን በሚቀሰቅስ መዝሙር ሁሉም ተሰብሳቢ በሙዚቃ መሣሪያ ታጅቦ በመዘመር እረፋዱ ላይ በ9፡00 (15፡00) ሰዓት የተጀመረው ዝግጅት በሻይ ግብዣ በ10፡20 (16፡20) ሰዓት ላይ ተጠናቋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ