አንድነት ፓርቲ የመጀመሪያ ህዝባዊ ስብሰባ አካሄደ
"ስብሰባው የተሳካ ነበር" ወ/ት ብርቱካን
ዶ/ር ነጋሶ፣ አቶ ስዬ፣ ፕ/ር በየነ፣ ... ተገኝተዋል

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ኅዳር 27 ቀን 2001 ዓ.ም. December 6, 2008)፦ አብዛኛውን የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በመያዝ ስያሜውን አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ በማለት ሕጋዊ እውቅና አግኝቶ የሚንቀሳቀሰው አንድነት ፓርቲ ዛሬ የመጀመሪያውን ህዝባዊ ስብሰባ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ። በስብሰባው ላይ የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አቶ ስዬ አብርሃ፣ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስና ሌሎችም ተገኝተዋል።
ህዝባዊ ስብሰባው ላይ የፓርቲውን ሊቀመንበር ብርቱካን ሚደቅሳን ጨምሮ ኢንጂነር ግዛቸው፣ አቶ አስራት ጣሴ፣ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያና አቶ ተመስገን ዘውዴ በመድረክ ላይ የተገኙ ሲሆን፣ አርቲስት ደበበ እሸቱ በዋናነት ስባሰባውን መርተዋል።
(ከቀኝ ወደ ግራ) ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና አቶ ስዬ አብርሃ |
የአንድነት የመጀመሪያ ህዝባዊ ስብሰባ 3000 ሰው እንደሚይዝ በሚታወቀውና ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኘው የመብራት ኃይል አዳራሽ ሞልቶ ብዙ ሰዎች ቆመው የተከታተሉት መሆኑን ለማወቅ ችለናል።
ከመድረኩ አንድነት ያከናወነውን ተግባሮችና ወደፊት ሊያከናውን የተዘጋጀባቸውን ጠቅላላ ዓላማዎች በዝርዝር የቀረበ ሲሆን፣ ከህዝብ የተነሱ በርካታ ጥያቄዎች መካከልም ክፍፍሉን በሚመለከት፣ ስለሠላማዊ ትግል ሁኔታና ከአሁን በፊት የተፈጠሩ ችግሮች ወደፊት ስላለመምጣታቸው የተነሱ ሲሆን፣ ከመድረክ በቂ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
በስብሰባው ላይ የነበሩት የድርጅቱ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ "ስብሰባው ከጠበቅነው በላይ የተሳካ ነው" ብለዋል።




