Ato Tamerat Layne

Ethiopia Zare (ዓርብ ታህሳስ 3 ቀን 2001 ዓ.ም. December 12, 2008)፦ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ፤ እስከ መጪው ሣምንት ድረስ ለ12 ዓመታት በእስር ከቆዩበት ቃሊቲ ከሚገኘው የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንደሚለቀቁ ምንጮች ጠቆሙ።

 

Blen Tamerat & her sisterከ12 ዓመታት በፊት በሦስት ጉዳዮች ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ በአንዱ ክስ ነፃ ሲባሉ፤ ለተለያዩ ክልሎች የኮንስትራክሽን ዕቃዎች ግዥ ያለ ጨረታና ያለተወዳዳሪ ሰጥተዋል። የጣልያን ኩባንያዎች ለተወሰኑ የጨርቃ ጨርቅ ድርጅቶች ያቀረቡትን ጥሬ ዕቃ ዕዳ መክፈያ በሚል በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያወጣ ቡና እንዲሰጥ አደርገዋል ሲል፤ በሚዘረዝረው ሁለቱ ክሶች ”ጥፋተኛ” ተብለውና 18 ዓመት ተፈርዶባቸው፤ ቃሊቲ መውረዳቸው ይታወሳል።

 

እንደምንጮቻችን ገለፃ አቶ ታምራት በዚህ ወር የመጀመሪያ ሣምንት፤ ከተፈረደባቸው 18 ዓመት ውስጥ ሦስት አራተኛ የሚሆነውን የእስር ጊዜ በማጠናቀቃቸው በአመክሮ እንዲለቀቁ ለማረሚያ ቤት አስተዳደር ጥያቄ ማቅረባቸውንና ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ እስከመጪው ሣምንት ድረስ ከእስር ነፃ እንደሚሆኑ ገልፀውልናል።

 

በተያያዘ ምንጮች እንደገለጹት የአቶ ታምራት ላይኔ ባለቤት ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ባለቤታቸው እንዲፈቱላቸው የሚጠይቅ ደብዳቤ ጽፈው፤ በፕሮፌሠር ኤፍሬም ይስኃቅ አማካኝነት ልከው እንደነበር ገልፀውልናል።

 

የደብዳቤው ይዘትም፣ ስለ ትግል ሁኔታ የሚያስታውሱ ፊልሞችን በቴሌቭዥን ባዩ ቁጥር፤ የጓደኝነታቸው ትውስታ እንደሚመጣባቸው ጠቅሰው ልጆች ያለ አባት ማሳደግ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በደብዳቤው ለጠ/ሚሩ አብራርተዋል።

 

ባለቤታቸው እስከ አሁን የታሰሩት በቂ እንደሆነ በመግለጽና፤ አቶ ታምራት ለልጆቻቸው ምን ያህል እንስፍስፍ አባት እንደሆኑ አቶ መለስም ጭምር እንደሚያውቁ የሚያስታውስ ነበር።

 

በሚያሳዝኑ ቃላት የተሞላውን ይህን የአቶ ታምራት ላይኔ ባለቤት ደብዳቤ፤ ፕሮፌሠር ኤፍሬም ይስኃቅ ተቀብለው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሰጡም ጉዳዩ እሳቸውን እንደማይመለከታቸው በመግለፅ ከወራት በፊት ተመላሽ አድርገውላቸው እንደነበር ምንጮች ጠቁመዋል።

 

በተያያዘም ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ የ15 ዓመቷ ልጃቸው ብሌን ታምራት፤ አባቷ ከእስር እንዲለቀቁ የሚማፀን ደብዳቤ ለኢትዮጵያ መንግሥት መፃፏ ይታወሳል።

 

Blen Tamerat”ለተከበረው የኢትዮጵያ መንግሥት” በሚል ርዕስ ስር ብሌን ታምራት የፃፈችው ደብዳቤ ከሞላ ጐደል የሚከተለውን ይመስላል።

 

”ይሄን ደብዳቤ የምፅፈው በእኔና በቤተሰቦቼ ስም ነው። አባቴ ታምራት ላይኔ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ላለፉት 11 ዓመታት በእስር ላይ ይገኛል። አባቴ የታሰረው ገና የአራት ዓመት ልጅ እያለሁ ነበር። ታናሽ እህቴ ደግሞ የሁለት ወር ዕድሜ ነበራት። ሁለታችንም ያለ አባት ለመኖር ተገደናል። በተለይ ትንሿ እህቴ አባቴ በታሰረበት ጊዜ በመወለዷ ከአባቷ ጋር ምንም ግንኙነት ሊኖራት አልቻለም። ስለዚህ ያለአባት የማደግን ሕመም በቀላሉ ለመግለፅ እቸገራለሁ። ሌሎች ሕፃናት ከእናታቸውና ከአባታቸው ጋር ሲሆኑ ማየት ለእኛ ከባድ ነገር ነው። ታናሽ እህቴም ሆነች እኔ የአባታችን ድምፅ ምን እንደሚመስል እንኳ ለማስታወስ አንችልም። ከአባታችን ጋር አብረን ለብዙ ዓመት መኖር ስላልቻልን በጣም ናፍቆናል። ታናሽ እህቴ ስምንት ዓመት ሲሞላት አባታችን እስር ቤት እንደሚገኝ ነግረናት ስለነበር በሁኔታው በጣም ደንግጣ ለብዙ ጊዜ ታለቅስ ነበር።

 

“እናታችን አባታችን በቅርቡ ተፈቶ ወደ ቤቱ እንደሚመለስ ትነግረናለች። እኛም አባታችን ለቤቱ እንዲበቃ ተስፋ በማድረግ እንፀልያለን። ልጅ እያለሁ አባታችን ለምን ከቤት እንደማይኖርና የት እንዳለ እናታችንን እንጠይቃት ነበር። በመጨረሻ አባቴን ማግኘት እንደማንችል ስረዳ ልቤ በኀዘን ተሰብሮ ነበር።

 

“እናቴ ስታዝን እመለከት ነበር። በዚህ ምክንያት ”አባቴን ለምን ወሰዱት?” ስል እራሴን እጠይቅ ነበር። አባታችን መታሰሩን እንዳወቅን እኔን ጨምሮ ታናሽ እህቴ ቤተሰቦቻችንን ጥለን ወደ ውጪ በመውጣታችን በጣም አዝና ነበር። መከራና ችግርን ለመሸሽ ከቤታችን ብንወጣም አንድ ቀን ወደ ቤታችን እንደምንመለስ ተስፋ እናደርጋለን። ከሀገር ርቀን ብንኖርም አባታችንን አንረሳውም። አንድ ቀን አባታችን ከእስር ተለቆ አብረን እንደምንኖር ተስፋ አደርጋለሁ። አንድ ቀን እኔ በምወደው የቅርጫት ኳስ ግጥሚያ ለማየት አብሮኝ ይሄዳል። እጅግ ተወዳጅ ተፈቃሪ አባት እንደሚሆነኝም ተስፋ አደርጋለሁ።

 

“ታናሽ እህቴ እርሷ የአባታችን ትንሿ ልዕልት ሆና ከአባቴ ጋር እንደምትጫወት ነግራኛለች። አባቴን እንደምትወደው እንደምትነግረውና እርሱም በበኩሉ እንደሚወዳት ሲነግራት መስማት እንደምትፈልግ ነግራኛለች።

 

“ልጆች ያላችሁ ወላጆች ልጆቻችሁን እንዴት አድርጋችሁ እንደምትንከባከቡ አውቃለሁ። ነገር ግን ያለአባት ማደግ በልጆች ላይ ስለሚያሳድረው ተፅዕኖ አስቡት። እንዲሁም ባለቤቷ የታሰረባት ሚስት በመሸ ቁጥር ስታዝን ማየትስ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ አስቡት። ከሥራ ወደ ቤታችሁ ስትመለሱ ልጆቻችሁን አቅፋችሁ መውደዳችሁን ስትገልፁላቸው እንዴት እንደምትደሰቱም አስቡት። እኛ ግን ይሄንን ዕድል ማግኘት አልቻልንም።

 

“እኔና እህቴም ለረጅም ጊዜ ከአባታችን ተለይተን በመኖራችን ከበቂ በላይ ተቸግረናል። ከአባታችን ተነጥለን ለመኖር የተገደድንበት ነገር ሊገባን አልቻለም። ሌሎች ወላጆች እንደሚያደርጉት አባታችንን ማግኘት እንፈልጋለን። ፍቅርና እንክብካቤ እንዲሰጠን እንሻለን። ስለዚህ ይህንን ደብዳቤ የፃፍኩልዎት የምንወደውን አባታችንን ከእስር ቤት እንዲፈቱልን ነው። የኢትዮጵያ ሚሊኒየም በተከበረበት ወቅት ብዙ እስረኞች እንደሚለቀቁ ሰምተን ነበር። አባታችንም ከሚፈቱት እስረኞች ውስጥ አንዱ ይሆናል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር። ነገር ግን እንደማይፈታ ስናውቅ አዝነንና ግራ ተጋብተን ነበር። ስለዚህ አባታችን እስከ አሁን የተሰቃየው ይበቃዋል። እኛም የተሰቃየነው ይብቃንና እባካችሁ ፍቱት። አባቴ በወጣትነቱ ከናንተ ጋር በትግል ማሳለፉን አወቃለሁ። ነገር ግን ላለፉት 11 ዓመታት በእስር ቤት ይገኛል። ኑሮውን ሳስብ እጅግ በጣም አዝናለሁ። ስለዚህ እባካችሁ አንድ ቤተሰብ ውስጥ አብረን እንድንኖር ፍቱልን።

 

አመሰግናለሁ!

 

ብሌን ታምራት ላይኔ

 

ለአቶ መለስ

 

እንደምንጮች ጥቆማ በመጨረሻ ከ12 ዓመት እስር በኋላ የአመክሮ መብታቸው ተጠብቆ በመጪው ሣምንት ይለቀቃሉ ብሎ እንደሚጠበቅ ታውቋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ