የቫንኩቨሩ ውይይት በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ
Ethiopia Zare (እሁድ ታህሳስ 5 ቀን 2001 ዓ.ም. December 14, 2008)፦ ትላንት ቅዳሜ ዲሴምበር 13 ቀን 2008 እ.ኤ.አ. በቫንኩቨር ካናዳ "በመጭው ምርጫ ሀገር ቤት የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች ምን ማድረግ አለባቸው? በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያንስ ድርሻና ተሳትፎ ምን ድረስ ነው?" በሚል የተካሄደው ህዝባዊ ውይይት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ ታወቀ።
በዝግጅቱ ላይ ለረጅም ዓመታት በትግል እንቅስቃሴ ውስጥ የኢህአፓ አባል በመሆን ያሳለፉት አቶ አዛለ ደስታ "ሀቀኛ ተቃዋሚዎች በወያኔ ምርጫ መሳተፍ አይገባቸውም" በሚል ርዕስ የአገዛዙን ጠቅላላ እንቅስቃሴና በተለይ በዲሞክራሲ፣ በሰብዓዊ መብቶችና በሀገሪቱ ያለውን የኢኮኖሚ ቀውሶች በሰፊው አቅርበው፤ እነዚህ አፈናዎች ባሉበት ሁኔታ ወደ ምርጫ መግባት የአገዛዙን ዕድሜ ያራዝማል በማለት በግላቸው ያላቸውን ሃሳብ ለተሰብሳቢዎቹ አቅርበዋል።
የቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሕብረት ፕሬዝዳንት የነበረውና በአሁኑ ሰዓት በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ (UBC) በሕግ ትምህርቱን በመከታተል ላይ የሚገኘው ተክለሚካኤል አበበ ደግሞ "አንድ ዕይታ፣ አስራ አንድ አስተያየቶች፤ ስለቀጣይ “ምርጫ” እና ቀጣይ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች አካሄድ" በሚል ርዕስ ባቀረበው ጽሑፍ፤ "በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደምርጫ መግባት አለባቸው" ሲል በሀገር ቤት ያሉ ተቃዋሚዎችም ሆኑ በየትኛውም ሀገራት የሚገኙ ተቃዋሚዎች ዕድል የሚያገኙትና የአገዛዙን ባህርያት የሚያጋልጡበትም ሆነ ከህዝብ ጋር የመወያየት አጋጣሚ የሚኖራቸው በምርጫ ወቅት በመሆኑ፤ ምርጫ ካለመግባት ከሚገኘው ምርጫ መግባቱ ብዙ ዕድሎችን ያስገኛሉ፤ ለዚህም ምርጫ 97ትን ያስለውሏል በማለት ያዘጋጀውን ጽሑፍ አቅርቧል።
በስብሰባው ላይ የተገኙ ሰዎች የተለያዩ አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን በማንሳት ከሠላማዊ ትግሉ ባሻገር በትጥቅ ትግልም ሆነ በሁለገብ የትግል ስልት ዙሪያ ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ለማወቅ ችለናል።
የውይይቱ ዋና ዓላማ የተለያዩ ሃሳቦችን የያዙ የዲሞክራሲ ኃይላት ሃሳባቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ በመነጋገር ሲቻል መፍትሔ ማዘጋጀት ካልሆነም ተከባብረው የሚጓዙበትንና አንዱ ሌላውን ሳይወቅስ ሊጓዝ የሚቻልበትን መንገድ ለመጥረግና ሀገር ቤት የሚገኙ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጀቶችን በሃሳብ ለመርዳት የተደረገ ከመሆኑም በላይ፤ የዚህ አይነትና መሰል ውይይቶች በውጭ ሀገር በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ እንዲካሄድ በር ለመክፈትም ጭምር የታቀደ መሆኑን አዘጋጆቹ ገልጸዋል።



