አንበሣ አውቶቡስ ዋጋ ጨመረ

Ethiopia Zare (ዓርብ የካቲት 7 ቀን 2000 ዓ.ም. February 15,2008)፦ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለውን የአዲስ አበባን ነዋሪን ገቢ ባላገናዘበ መልኩ የአንበሣ አውቶቡስ ከ25 እስከ 50 ሣንቲም የታሪፍ ጭማሪ በማድረጉ የከተማው ነዋሪ በከፍተኛ ሁኔታ መማረሩ ተደመጠ።

 

ከዚህም ሌላ በአዲስ አበባ ከተማና አካባቢዋ በከፍተኛ ሁኔታ የመጓጓዣ እጥረት የተከሰተ ሲሆን፣ በተለይ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓቶች ላይ የከተማው ነዋሪ ታክሲና አውቶቡስ ለመሣፈር ከ30 - 60 ደቂቃዎች መጋፋትና መራወጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለመደ እየሆነ መጥቷል።

 

አንዳንዶች እንደሚሉት ከሆነ እጅግ እየናረ ባለው የነዳጅ ዋጋ ምክንያት የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ራሳቸውን ከገበያው እያገለሉ ነው።

 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢህአዴግ መንግሥት የነዳጅ ዋጋን በየጊዜው እያሻቀበ እንዲሄድ በማድረጉ የተነሳ በመላው ሀገሪቱ የኑሮው ውድነት ከዕለት ዕለት እየጨመረ መምጣቱ ይታወቃል። በቅርቡም 30 በመቶ የነዳጅ ዋጋ መጨመሩን መዘገባችን አይዘነጋም

 

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን ያነጋገርናቸው አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያ "የነዳጅ ዋጋ መጨመርን አስከትሎ የትራንስፖርት ዋጋ ይንራል። በዚህም ሰበብ ከእህል ነጋዴው አንስቶ እያንዳንዱን ለዕለት ተዕለት ኑሮ የሚስፈልግ ጥቃቅን ቁሳቆሶችና ምርቶችን ለገበያ የሚያቀርበው ነጋዴ በሙሉ ቢያንስ በሣንቲም ደረጃ ዋጋ ይጨምራል። በእያንዳንዱ ቁሳቁስ፣ እህል፣ ትራንስፓርት፣ ... ላይ የተጨማመሩት ሣንቲሞች በወር ውስጥ ሲሰሉ ዳጎስ ይሉና ኅብረተሰቡን ለችግርና ለኑሮ ውድነት ይዳርጉታል። ምክንያቱም መጀመሪያውኑ አብዛኛው የኅብረተሰባችን ክፍል ከድኅነት ወለል በታች ነውና። እንኳን የተጨመሩትን አይደለም፤ ቀድሞውንም ኑሮው አቅቶት ችግር ላይ ነበርና።" ብለዋል።

 

አክለውም "ባለፈው ጊዜ የተደረገው የደሞዝ ጭማሪም ቢሆን እንኳን ለአሁኑ በወቅቱም ለኅብረተሰቡ የኑሮ ውድነትን ሊቀርፍለት ቀርቶ ሊያስታግስለት እንኳን እንዳልቻለ ለመረዳት ብዙ መመራመር አያስፈልገንም።" ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል።

 

የነዳጅ ውድነትን ተከትሎ የሚመጣውን የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ ምን መደረግ አለበት ይላሉ? ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄም ሲመልሱ "መንግሥት እንደቀድሞው በተለይም በደርግ ጊዜ እንደነበረው ነዳጅን መደጎም አለበት። የዓለም የነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ እንዳለ ሆኖ፤ በተለይ በሀገራችን በየጊዜው የነዳጅ ዋጋ እያሻቀበ የመጣው መንግሥት በነዳጅ ላይ ያደርገው የነበረው ድጎማ በማንሳቱ ነው። ስለዚህ መንግሥት ነዳጅን በመደጎም ዋጋውን ዝቅ ማድረግ ይገባዋል። ያም ካልሆነ ባለበት እንዲቆም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሊደጉመው ይገባል።" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!