የማተማያ ቤቱ ሥራ አስኪያጅም ተከሰዋል

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ታህሳስ 18 ቀን 2001 ዓ.ም. December 27, 2008)፦ የቡና ተክል ልማት ድርጅት ለሚሊኒየም ላሳተመው የእንኳን አደረሳችሁ፣ የአዲስ ዓመት መልካም ምኞት መግለጫ ፖስት ካርድ ላይ፣ ከድርጅቱ ስምና ዓርማ ጋር የኢትዮጵያ ባንዲራ ያለ ዓርማ በመታተሙ፣ ሦስት የድርጅቱ ኃላፊዎችና ፖስት ካርዱን ያሳተመው ማተሚያ ቤት ሥራ አስኪያጅ ክስ ቀረበባቸው።

 

ባለፈው ሣምንት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 11ኛው ወንጀል ችሎት ክስ የቀረበባቸው፣ የቡና ተክል ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ተረፈ በድሉ፣ የአስተዳደርና የሰው ኃይል ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ግርማ፣ የዕቃ ግዢ ሠራተኛ ወ/ሮ አበራሽ ተስፋዬ እና የኢትካና ማተሚያ ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፋሲል ደበበ ናቸው።

 

የዓቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳውም፤ ተከሳሾች በነኀሴ ወር 1999 ዓ.ም. በቡና ተክል ልማት ድርጅት ስም የድርጅቱ ዓርማና፣ የኢትዮጵያ ባንዲራ ያለበት፣ በ2000 ሚሊኒየም የእንኳን አደረሳችሁ የአዲስ ዓመት መልካም ምኞት መግለጫ ፖስት ካርድ ላይ፣ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ያለበት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጎተራ አካባቢ በሚገኘው 4ኛ ተከሳሽ ድርጅት በኢትካና ማተማያ ቤት ሲያሳትሙ፣ በሕግ በታዘዘው መሠረት በኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ላይ ሊኖር የሚገባው፣ የብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦችና ኃይማኖቶች የእኩልነትና በአንድነት የመኖር ተስፋቸውን የሚያንፀባርቀውን የኮከብ ምልክት፣ ብሔራዊ ዓርማ በባንድራው ላይ እንዲታተም የማድረግ፣ ክብር የመስጠትና በአግባቡ ሥራ ላይ የሚውል የሕግ ግዴታ እያለባቸው፣ ሕግን በሚቃረን አኳኋን በተለይም የኢፌዲሪ ፌደሬሽን ምክር ቤት፣ የብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማችን ዓርማ በሕግ በታዘዘው መሠረት ሥራ ላይ እንዲውል በመገናኛ ብዙኃን ብርቱ ማስገንዘቢያ እየሰጠ ባለበት ወቅት፣ ለጉዳዩ ተገቢውን አክብሮት ባለመስጠታቸው ሲል ክሱን አቅርቧል።

 

“ዋና ሥራ አስኪያጁ ዶ/ር ተረፈ በድሉ ባለባቸው ከፍተኛ ኃላፊነት፣ የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ የማክበርና የማስከበር የተለየ ኃላፊነት እያለባቸው፣ በፖስት ካርዱ ላይ የታተመው ሠንደቅ ዓላማ ብሔራዊ ዓርማ የሌለበት መሆኑን እያወቁ፣ ይልቁንም ጉድለት አለበት በሕግ በታዘዘው መሠረት አልታተመም ተብሎ እየተነገራቸው፣ አድራጎቱን በተቃወሙ ሠራተኛ ላይ ጫና ፈጥረው ከሕግ አፈፃጸም ውጭ ሥራ ላይ እንዲውል አድርገዋል።

 

“በመሆኑም ሠንደቅ ዓላማው በሕግ በታዘዘው መሠረት፣ አለመሠራቱን እያወቁ፣ ለፌደራሉ ባንዲራ ተገቢውን ክብር ባለመስጠት፣ ከሕግ ውጭ አገልግሎት ላይ እንዲውል፣ በተጨማሪም ሥራ ላይ ባላዋሉት ሠራተኞች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው አድርገዋል” ሲል ክሱ ይዘረዝራል።

 

ሁለተኛዋ ተከሳሽም ብሔራዊ ዓርማ የሌለበት ሠንደቅ ዓላማ፣ እንዲታተም ማድረግ ሕገወጥ መሆኑን እያወቀች፣ ታትሞ እንዲወጣ ያለሥልጣኗ ለማተሚያ ቤቱ ናሙናውን አፅድቃ ትዕዛዝ መስጠቷ፣ እንዲሁም የማተሚያ ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፋሲል የቀረበለት ትዕዛዝ፣ ሕገወጥ መሆኑን እያወቀ፣ ሕጋዊ ይዘቱን ያልጠበቀ ባንዲራ አላትምም ማለት ሲገባቸው አትመው ሰጥተዋል በማለት ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቷል።

 

ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ “ጥፋተተኛ አይደለንም” ሲሉ የእምነት ክህደት ቃላቸውን የሰጡ ሲሆን፣ ዓቃቤ ሕግ የዋስትና መብታቸውን ባለመቃወሙ የግዢ ሠራተኛዋ በ2 ሺህ ብር፣ ሌሎች ሦስቱ ተከሳሾች በ5 ሺህ ብር እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱ ወስኗል። የዓቃቤ ሕግን ምስክር ለመስማትም ቀጠሮ ተሰጥቷል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!