"ኢ/ር ኃይሉ በሌሉበት መነጋገር አንችልም" የአቶ አባይነህ ቡድን

"ኢ/ር ኃይሉ ሻውል የሚመጡበትን ቁርጥ ቀን ንገሩንና እናራዝመው ..." እነ ወ/ት ብርቱካን

"ኢ/ር ኃይሉ ሻውል በሦስት ምክንያቶች ቶሎ ወደ ኢትዮጵያ አይመለሱም፤ አንደኛው የጤናቸው ሁኔታ ነው፣ ሁለተኛው ደግሞ አሜሪካን ሀገር ባሉት አባላት መካከል ብዙ የተበላሹ ነገሮች ስላሉ እሱን ለማስተካከል ሲሆን ሦስተኛው ከግል ሕይወታቸው ጋር የተያያዘ መሆኑ ..." የኢንጂንየር ኃይሉ ባለቤት

ሪፖርታዥ

Ethiopia Zare (ዓርብ የካቲት 14 ቀን 2000 ዓ.ም. February 22, 2008)፦ ከእስር የተፈቱት የቀድሞው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሮችን በጋራ አሰባስቦ እንዲነጋገሩ ለማድረግና ድርጅቱን እንደ ድርጅት ለማስቀጠል ጥረት ሲያደርግ የነበረው 17 አባላት ያሉት የሽማግሌዎች ስብስብ በመጨረሻ ባወጣው መግለጫ ሁለት ለ 15 ልዩነት የፈጠሩ መሆናቸውንና አብዛኞቹ ለሽምግልናው አለመሳካት መንስኤው ኢ/ር ኃይሉ ሻወል መሆናቸውን ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ አስረዳ።

 

ለዘገባው የኮሚቴው ቅርብ የሆኑ ምንጮች እንደገለጹት፤ የመጀመሪያዎቹ ወጣቶች የተገናኙት የቅንጅት አመራሮች ቃሊት እስር ቤት እያሉ ለመጠየቅ በሚሄዱበት ጊዜ ነው። አመራሮቹ ከእስር ሲፈቱ እነዚህ ወጣቶች ከእያንዳንዳቸው ኪስ 100 ብር በማዋጣት ዝግጅት አዘጋጅተው ለአመራሮቹ ሽልማት ለመስጠት የዶ/ር ብርሃኑ ነጋን ቤት መረጡ፤ ፍቃደኝነታቸው ተገልጾላቸውና ለሁሉም የቅንጅት አመራሮች ማስታወሻ እንዲሆን ዋንጫ ገዝተው በተያዘላቸው ቀጠሮ መሠረት በቦታው የተገኙ ቢሆንም ዶ/ር ብርሃኑ ቤት ሲደርሱ ግን እንኳን ሁሉም አመራሮች ቀርቶ ዶ/ር ብርሃኑም በቦታው አልነበሩም።

 

ምክንያቱን ሲጠይቁ ሁሉም እንዳልተመቻቸው ተነገራቸው። ዶ/ር ብርሃኑ ደግሞ በስልክ ተጠርተው የመጡ ሲሆን ሌሎች ሁለት አመራሮችም ተገኙና የዋንጫ ሽልማታቸውን ሰጥተው ወደቤታቸው ተመለሱ።

 

የፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ነዋሪዎች ለወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እና ለሌሎች አመራሮች ላዘጋጁት የምሳ ግብዣም ትኬት በመሸጥ እግዛ ከመስጠት አልፈው እርስ በእርስ ተዋወቁ። ከዚህ ዝግጅት በኋላ የቅንጅት አመራሮች ልዩነት እየሰፋ ሲመጣና በአደባባይ መወቃቀስ ሲጀምሩ ይህ ኮሚቴ እንደገና 20 ሆነው ተሰባሰበ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ወደ ውጭ አገር ሲሄድ አንደኛው ወደ ተቀጣጠሩበት የስብሰባ ቦታ ሲመጣ በድንገት ሕይወቱ አለፈ። አንዱ ደግሞ ስብሰባ መምጣትም አቆመ።

 

የስብሰባቸው ዓላማ፣ ቅንጅቱ ይዞት የተነሳው ዓላማና የዴሞክራሲያዊ መርህ በኢትዮጵያ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሕዝቡን ያሳተፈ ነበር። ግን ብዙም ሳይራመድ ግለሰቦች እርስ በእርሳቸው በፈጠሩት አለመግባባት ፓርቲው ተዳክሞ ሁሉም ተበታተኑ።

 

የኮሚቴ ስብስብ በኢትዮጵያ ውስጥ አንድም ይሁን ከዛ በላይ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ መፈጠር አለበት ብሎ ያምናል። ለዚህም ቅንጅቱ ይዞት በተነሳው ዓላማ ዙሪያ ሰዎች ተስማምተው ከተሰባሰቡና ከሠሩ ጥንካሬው ይመጣል ፓርቲውም የሕዝብ ይሆናል ብለው ያምናሉ።

 

ከዚያም ፓርቲው እንደፓርቲ በስምምነት መቀጠል ያልቻለበትን ምክንያት ቀረብ ብለው ለማጥናት ይሞክራሉ። በዋናነት ስምምነት ላይ ሊደርሱ ያልቻሉት በኢ/ር ኃይሉ ሻውልና በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራ በሚል እንደሆነና ሁለቱ ወገኖች ስምምነት ላይ መድረስ ያለመቻላቸውን በማመናቸው ሁለቱም በጋራ ቁጭ ብለው በመነጋገር ፓርቲውን አጠንክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ሥራ ይጀምራሉ።

 

ይህን ሥራ የጀመሩት ከመስከረም ወር 2000 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ሁሉንም ወገን ማነጋገራቸውን ባለፈው ሳምንት በጽሑፍ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

 

እንደምንጮቻችን ገለፃ ከሆነ ኮሚቴው በጉዳዩ ላይ ያገባቸዋል ያሏቸውን በርካታ ሰዎች ካነጋገሩ በኋላ አንድ ርምጃ ላይ የደረሱበትንም ለህዝብ ማሳወቅ ዝግጅት እያደረጉ ባሉበት ወቅት በመካከላቸው ልዩነት ይፈጠራል።

 

መግለጫውን ለማውጣት ሲሰባሰቡ፣ ስምምነቱ ተፈፃሚ፣ እንዳይሆን ምክንያት የሆነው የኢ/ር ኃይሉ ሻውል ወደ ኢትዮጵያ አለመምጣት ሲሆን፤ እንዲመጡ ሲጠየቁም ፈቃደኛ አለመሆናቸው ነው። ፓርላማ እንግባ/አንግባ በሚል በተደረገው ውይይት ላይ "እስክመጣ እንዳይወሰን" ብለው ሕክምናቸውን አቋርጠው መጥተው ለእስር እስከመዳረግ የደረሰ መስዋዕትነት ለከፈሉለት ፓርቲ አሁን ግን ኅልውናን ለማስጠበቅ ሲጠሩ ቁርጥ ያለ ቀን አለመስጠታቸው ስህተት ነው የሚል አቋም መጣ።

 

ከመካከላቸው አንዱ ግለሰብ ደግሞ "እነ ወ/ት ብርቱካንም ቢሆኑ ሽምግልናው ከተጀመረ በኋላ የማሟያ ምርጫ አድርገዋል። ይህ መደረግ አልነበረበትም፣ መወቀስ አለባቸው" ሲሉ ሃሳብ ማንሳታቸውን ይህ ሃሳብ የእነ ኢ/ር ኃይሉ ሻውል ቡድን ሃሳብ ጭምር በመሆኑና ኮሚቴው የታመነበት በመሆኑ ተቀባይነት ማግኘቱን ምንጫችን ጠቁመዋል። "እነ ወ/ት ብርቱካን 'ኢ/ር ኃይሉ ሻውል የሚመጡበትን ቁርጥ ቀን ንገሩንና እናራዝመው አለበለዚያ የፓርቲው ሕጋዊነት ተጠብቆ መቀጠል ስላለበት ብዙ ልንታገስ ስለማንችል ሕጋዊነቱን ጠብቀን እንሠራለን' ብለውናል። ስለዚህ ልንወቅሳቸው አይገባም" የሚል አስተያየትም ቀርቦ እንደነበር ጠቁመዋል።

 

ኮሚቴውን ከመጀመሪያው ጀምሮ ያሰባሰበው አንድ ወጣት ደግሞ ስሙ ተጠቅሶ በሃሳቡ እንዳልተስማማ የሚገልጽ ጽሑፍ ከመግለጫው ጋር ተካቶ እንዲወጣለት ይጠይቃል። ኮሚቴው በዚህ ሃሳብ ሳይስማማ ይቀራል። እሱም ኮሚቴውን ጥሎ መውጣቱን ምንጮቻችን ጠቁመዋል። የሃሳብ ልዩነቱ እየሰፋ ሲመጣ በሃሳቡ እንደማይስማሙ ገልጸው ጥለው ይወጣሉ። ኮሚቴው ስምምነት ላይ ሳይደርስ ሁለት ለ15 እየተነጋገረ ባለበት ሁኔታ 15 አባላት ያሉት ኮሚቴ መግለጫውን አውጥቷል።

 

ኮሚቴው በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጠን ጠየቅን፣ መልስ ሊሰጡን ፈቃደኛ ቢሆኑም ስማቸውም ሆነ ማንነታቸው እንዲገለጽ ግን አልፈለጉም። "በነበረው ሂደት ብዙ ጥረት አድርገናል" ይላሉ።

 

"በእነ ወ/ት ብርቱካን በኩል ያነጋገርናቸው አባላት ቁጭ ብሎ ለመነጋገር ፍቃደኝነታቸውን አሳይተዋል። በእነ ኢ/ር ኃይሉ ሻውል በኩል ያሉት ግን እሳቸው በሌሉበት ምንም መነጋገር እንደማይቻል ስለተገለጸልን ፊታችንን አዙረን በመመለስ እሳቸውን ለማነጋገር ጥረት ማድረግ ጀመርን" ይላሉ።

 

ባደረጉት ጥረትም ስድስት ጊዜ ማነጋገራቸውን የስብሰባው ቀን ቆርጠው በኢ-ሜይል ደብዳቤ መላካቸውን ተጨማሪም የመነሻ ሃሳብ ማቅረባቸውን ገልጸዋል። ነገር ግን በመጨረሻ ከባለቤታቸው ጋር በስልክ ባደረጉት ውይይት እንደተገለጸላቸው ኢ/ር ኃይሉ ሻውል በሦስት ምክንያቶች ቶሎ ወደ ኢትዮጵያ እንደማይመለሱ ነው፤ አንደኛው የጤናቸው ሁኔታ ነው፣ ሁለተኛው ደግሞ አሜሪካን ሀገር ባሉት አባላት መካከል ብዙ የተበላሹ ነገሮች ስላሉ እሱን ለማስተካከል ሲሆን ሦስተኛው ከግል ሕይወታቸው ጋር የተያያዘ መሆኑ እንደተነገራቸው ተናግረዋል።

 

"መልሱ ቁጥር ያለ በመሆኑና እኛም እንደ ሕዝብ ፓርቲው ያገባናል ብለን እስከገባንበት ድረስ የደረስንበትን ለሕዝብ ማሳወቅ አለብን" ከሚል ተነስተው መግለጫ መስጠታቸውን ይናገራሉ።

 

በመግለጫቸውም አመራሮቹ ተቀራርበው ለመነጋገር ላለመቻላቸው ምክንያቱ የኢ/ር ኃይሉ ሻውል በተጠበቁበት ሰዓት ሊገኙ አለመቻላቸው፣ የድርጅቱ ጽ.ቤቶች በተዘጉበት፣ አባላት በተሰደዱበትና እንዲሁም የድርጅቱ ስምና ዓርማ ለሌሎች በተሰጠበት ሁኔታ የተወሰኑ የላዕላይ ምክር ቤት አባላትን ብቻ በመያዝ ጉባዔ እጠራለሁ ማለታቸው ከተጨባጭ ሁኔታው አንፃር ሲታይ ተቀባይነት የሌለው መሆኑ ቢገለጽላቸውም አለመቀበላቸው እና በአቶ አባይነህ ብርሃኑ በኩል ያሉት በኢንጅነር ኃይሉ ወገን የተሰለፉ አካላት የውይይት እና እርቅ ሀሳቡን ቢደግፉትም ሊቀመንበሩ በሌሉበት ማካሄድ እንደማይቻል እንደገለጹላቸው የሚገልጽ መግለጫ አውጥተዋል። በወ/ት ብርቱካን በኩል ያለው ወገን በተጓደሉ የላዕላይ ም/ቤት አባላት ምትክ ምርጫ ማካሄዳቸው እንደ አንድ ምክንያት ተጠቅሷል።

 

እንደምንጮቻችን ገለፃ ከሆነ ከሚቴው መግለጫውን ቢያወጣም ሁለት ለ15 በልዩነት የተለያየ ሲሆን፣ በቀጣይ ምን መደረግ አለበት በሚለው ላይ ገና ተወያይቶ አለመወሰኑ ታውቋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ