የዲ.ኤች. ገዳ ባለቤት በድንገት አረፉ
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ጥር 2 ቀን 2001 ዓ.ም. January 10, 2009)፦ በተለያዩ የንግድ ዘርፍ በመሰማራት የታወቁትና የዲ.ኤች. ገዳ ባለቤት የሆኑት አቶ ደጉማ ሁንዴ በድንገት ትናንት (ዓርብ ጥር 1 ቀን) ከዚህ ዓለም መለየታቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች አረጋገጡ።
አቶ ደጉማ ሁንዴ በተለይ በዱቄት በቆርቆሮና የተለያዩ የንግድ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ከመሆኑም በላይ፤ በአዲስ አበባ አውሮፕላን ጣቢያ አካባቢ ትልቅ ፎቅ በመገንባትና የገበያ አዳራሽ በማሠራት ላይ የነበሩ መሆናቸው ታውቋል።
አቶ ደጉማ ሁንዴ በአካባቢያቸው የሚገኙ አቅመ ደካማዎችን በመርዳት የሚታወቁ ሲሆን፣ በኪሳራ ምክንያት ከንግዱ ዘርፍ የወጡ ግለሰቦችንም በመርዳት የሚታወቁ መሆናቸውን ምንጮቻችን አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም ቀሽት በተባለ የጉራጌ አካባቢ ውስጥ ትልቅ ቤተክርስቲያን ያሰሩ ሲሆን፣ አቶ ደጉማ ከምንም ነገር ተነስተው ጠንክረው በመሥራት የተትረፈረፈ ንብረት ለማካበት የበቁ ከመሆናቸውም ሌላ በአሜሪካን ሀገር ኖረው እንደነበር ለማወቅ ችለናል።
አቶ ደጉማ የ11 ልጆች አባት ነበሩ።



