የሕግ ባለሙያዎች እያወገዙት ነው

Ethiopia Zare (እሁድ የካቲት 16 ቀን 2000 ዓ.ም. February 24,2008) በተለያዩ ድረ-ገጾች ላይ ሰሞኑን የተለቀቀው የሲቪል ማኅበረሰብ ረቂቅ አዋጅ አፋኝ ይዘት ያለው ነው ሲሉ አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች አስተያየት ሰጡ።

የሕግ  ባለሞያና የሲቪል ማኅበረሰብ አባል እንደገለጹት፤ በሕግ ማርቀቅ ሂደት የሲቪል ማኅበረሰቡና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እንዲሳተፉ በመንግሥት በኩል ፈቃደኝነት እንዳልነበረ ገልጸው፤ አሁንም ቢሆን ወጣ የተባለውን ረቂቅ አዋጅ ከድረ-ገጽ ላይ ወስዶ ከማየት ውጭ በመንግስት በኩል የተገለጸ ምንም ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

ነገር ግን ወጣ ከተባለበት ድረ-ገጽ ላይ ወስደው ረቂቅ አዋጁን እንደተመለከቱት፣ ረቂቅ አዋጅ አፋኝና የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ሂደት ከፍተኛ መሰናክል ውስጥ የሚከት ነው ብለውታል።

ረቂቅ አዋጁን «አፋኝ ነው» ያሉበትን ምክንያቶች ሲገልጹም፤ የሲቪል ማኅበራት ምዝገባን በተመለከተ፣ የሲቪል አስተዳደርና ነፃነትን በተመለከተ፣ የሲቪል ማኅበረሰብን ማፍረስ በተመለከተ የወጡት ድንጋጌዎች አፋኝ ናቸው ብለዋል።

ምዝገባን በተመለከተ፣ በረቂቅ ህጉ ላይ «ኤጀንሲ» የተባለው የመንግስት ተቋም፤ አንድን መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ለሕዝብ ጥቅምና ለብሔራዊ ደህንነት በሚል ምክንያቶች እንዳይመዘገብ ወይም እንዲፈርሱ ያደርጋል በሚል የተቀመጠው ድንጋጌ ለሲቪል ማኅበረሰቡ አደጋ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በረቂቅ ሕጉ ላይ የተጠቀሰው አወዛጋቢ ወይም አከራካሪ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምንም ዓይነት አስተያየት መስጠት እንዳይችሉ የሚከለክለው ረቂቅ አዋጅ በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብት እና የሲቪል ጉዳዮች እንቅስቃሴዎች እንዳይራመዱ ይከለክላል ሲሉ እኚሁ ባለሞያ አስተያየት ሰጥተዋል።

የዚህ ረቂቅ አዋጅ ምንጭም በሲቪክ ማኅበራት አፋኝ እንዳላት ከምትታወቀው ከሲንጋፖር ሕግ ነው የሚሉ አስተያየቶች እንዳሉ የገለጹት እኚሁ ባለሞያ እሳቸው እንደተመለከቱት ግን ሕጉ ከሲንጋፖርም የባሰ እንደሆነ ተናግረዋል። 

መንግሥት ይህንንም ረቂቅ አዋጅ ከማጽደቁ በፊትም የሲቪል ማኅበረሰቡን አባላትም ሆነ የሕግ ባለሞያዎችን ሰብስቦ ማወያየት አለበት ይላሉ። 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!