የአንድነት ፓርቲ አመራሮች የአሜሪካ አምባሳደርን አነጋገሩ
‘የፖለቲካ እንቅስቃሴው አደጋ ላይ ነው’ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ
Ethiopia Zare (ሐሙስ መጋቢት 10 ቀን 2001 ዓ.ም. March 19, 2009)፦ አራት የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደርና የፖለቲካ ክፍል ኃላፊ ጋር ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ሪፖርተር ዘገበ።
የህዝብ ግንኙነት ኃላፊውን ዶ/ር ኃይሉ አርኣያን ጨምሮ ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም፣ ኢንጂንየር ግዛቸው እና ዋና ጸሐፊው አቶ አስራት ጣሴ በውይይቱ ላይ ተገኝተው የሀገሪቱን ጠቅላላ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ ሰፊ ውይይት ያካሄዱ ሲሆን፣ በእስር ላይ የምትገኘውን የድርጅቱን ሊቀመንበር በሚመለከትም ሰፊ ውይይት እንዳካሄዱ የህዝብ ግንኙነቱን ዋቢ ያደረገው ዘጋቢያችን አስታውቋል።
አመራሮቹ በየክልሉ ያሉ አባላቶቻቸው በአገዛዙ አካላት ይደርስባቸዋል ያላቸውን የእስርና የወከባ ሂደቶችና የፓርቲው ጽሕፈት ቤቶች በትክክል ሥራቸውን እንዳይሠሩ የሚደረገውን ጫናና ግፊት በሚመለከት ከአምባሳደሩና ከፖለቲካ ኃላፊው ጋር ውይይት ያካሄዱ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።
ውይይቱን በሚመለከት ያነጋገርናቸው የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ በተለይ ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ፤ "የሀገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አደጋ ላይ ነው፣ ይህንን ችግር ለመታደግ አስፈላጊውን እንቅስቃሴ እያደረግን ነው" ብለዋል። ከኤምባሲው ባለሥልጣናት ጋር የተሳካ ውይይት ማድረጋቸውን የሚናገሩት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፣ "ያቀረብናቸውን ሃሳቦች ለማሳካትም ሆነ ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴው በአግባቡ እንዲቀጥል አምባሳደሩና የፖለቲካ ክፍል ኃላፊው ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በአጭር ጊዜ ውስጥ ውይይት እንደሚያደርጉበት አሳውቀውናል" ብለዋል።
በተያያዘ ዜና በክልል የሚገኙ በተለይ ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት አባላቶች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ወከባና እስር ከመድረሱም በላይ የየክልሉ ባለሥልጣናት ተቃዋሚ ድርጅቶች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴዎች በጥንቃቄ እንዲከታተሉ ትዕዛዝ መሰጠቱን የኢትዮጵያ ዛሬ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ጠቁመው፤ "ቢሮ ከፍተው እንዲንቀሳቀሱ ከፈቀዳችሁ ምን እስቲያደርጉ ነው የምትጠብቁት" የሚል ዛቻና ማስፈራሪያ ለክልል ትናንሽ ባለሥልጣናት እየተሰጠ መሆኑን እነዚሁ ውስጥ አዋቂዎች አስረድተዋል።
አገዛዙ መጭውን ምርጫ በሚመለከት ሰፊ ዘመቻ የጀመረ ሲሆን፣ በአንጻሩ ተቃዋሚዎች ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ከፍተኛ ውጥረት እየፈጠረ መሆኑ ያሳሰባቸው የኢትዮጵያ ዛሬ ተባባሪ የፖለቲካ ተንታኝ እንደሚሉት፣ ተቃዋሚዎች ከፍተኛና እልህ አስጨራሽ ፈተና ከፊታቸው ቢደቀንም፤ ያለፉትን የትግል ትምህርቶች ግንዛቤ ውስጥ በማስገባትና አገዛዙን እልህ በሚያስጨርስ መልኩ መጓዝ እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል። አክለውም "ምርጫው ከተካሄደ በምንም አይነት መልኩ ወያኔ ብቻውን ሮጦ ብቻውን የሚያሸንፍበትን በር መክፈት የለባቸውም" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አያይዘውም "ኢህአዴግ እስከምርጫው መባቻ ድረስ ያለውን ማናቸውንም ኃይል ተጠቅሞ ተቃዋሚዎች ወደምርጫ እንዳይገቡ የሚያደርገውን ውጥረት የሚቀጥል ቢሆንም፤ ዓለማቀፍ ድጋፍ ለማግኘትና ህዝቡን ለማደናገር በምርጫው የመጨረሻ ጊዜያት መገናኛ ብዙኀንን ነፃ አድርጎና ታዛቢዎችን በነፃነት ለቆ 'ነፃ ምርጫ' አካሂጃለሁ የሚያስብሉ ማወናበጃ ዘዴዎችን ሊጠቀም ይችላል" ሲሉ ግምታቸውን ገልፀዋል። "የዚህን አይነት ቁማሮችን ተቃዋሚዎች ሊወጡት የሚችሉት ኢህአዴግ በቅድመ ምርጫ የሚያደርገውን ወከባ፣ እስራትና እንግልት በመወጣት ትግላቸውን በጽናት መወጣት ሲችሉ ብቻ ነው።" ሲሉ አስተያየታቸውን ደምድመዋል።



