- ሁለት የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሠራተኞች ተጎድተዋል

Ethiopia Zare (እሁድ መጋቢት 27 ቀን 2001 ዓ.ም. April 5, 2009)፦ አራት ኪሎ የሚገኘውን ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት በመጠበቅ ላይ የሚገኙ ፌደራል ፖሊሶች ባደረጉት ግምገማ ያልተደሰተ አንድ አባላቸው ሦስቱ ላይ ተኩሶ ከጣላቸው በኋላ ራሱን አጠፋ። አንዱ ሲሞት አንዱ በሞት አፋፍ ላይ እንደሚገኙና አንዱ መቁሰሉ ታውቋል። ሁለት የማተሚያ ቤቱ ሠራተኞችም ጉዳት ደርሶባቸዋል።

 

ማተሚያ ቤቱ የመንግሥት በመሆኑ ጥበቃ የሚደረግለት በፌደራል ፖሊስ ሲሆን፣ ፖሊሶቹን የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ አለቃ አላቸው። ሰሞኑን በተከታታይ ባደረጉት ስብሰባ ግምገማ አካሂደው የነበረ ሲሆን፣ ይህ ፖሊስ ከተገመገሙት አንዱ እንደነበር ምንጮች ጠቁመዋል።

 

በትናንትናው ቅዳሜ መጋቢት 26 ቀን ጠዋት ተረኛ የነበረው ፖሊስ ደሞዙን ሊቀበል ሲሄድ የአምስት ቀን ደሞዝ ተቆርጦ ይሰጠዋል። በቀጥታ ወደ አለቃው በመሄድ ፍቃድ እንዲሰጠው ሲጠይቅ “ካንተ በፊት ፍቃድ የጠየቁ ስላሉ አይሰጥህም” ሲል ይከለክለዋል።

 

ከሰዓት በኋላ አለቅየው ከሌሎች ፖሊሶች ጋር በመሆን በግቢው ውስጥ በሚገኘው ክበብ ውስጥ ዳማ እየተጫወተ ባለበት ወቅት በድንገት በግምገማ ደሞዙን የተቀጣው የፌደራል ፖሊስ አባል ለጥበቃ ሥራ የሚገለገልበትን ክላሽንኮፍ ጠመንጃ ይዞ ወደ ክበቡ በመግባት በሥራ ባልደረበቹ ላይ ጥይት አርከፍክፎ በአጥር ዘሎ ማምለጡን በቦታው የነበሩ ምንጮች ገልጸውልናል።

 

ተኩሱ ድንገተኛና ድምፁ ከፍተኛ ስለነበር ግቢው በጩኸት መታመሱን የገለጹት ምንጮች፤ በተኩሱ ሹፌርና የመጋዘን ኃላፊ በድምሩ ሁለት የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሠራተኞች ተጎድተው በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል መተኛታቸው ታውቋል።

 

ፖሊሱ ባልደረቦቹ ላይ ከተኮሰና ከጣላቸው በኋላ በአጥር ዘሎ ከግቢው ጀርባ በሚገኘው ዳዋ ስር በያዘው መሣሪያ ራሱን መግደሉ ተረጋግጧል።

 

የተጎዱት ፖሊሶች ወዲያውኑ ወደ ፖሊስ ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን፣ አለቅየው እግሩ ላይ በመመታቱ ወዲያው ሕክምና አግኝቶ ሲወጣ ሁለቱ በሞት አፋፍ ላይ ስለነበሩ እንዲተኙ ተደርጓል። ከለሊቱ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ የአንደኛው ፖሊስ ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ ሁለተኛው እዛው ተኝቶ በመታከም ላይ ይገኛል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!