Ethiopia Zare (ዓርብ የካቲት 21 ቀን 2000 ዓ.ም. February 29, 2008)፦ ከአዲስ አበባ ከተማ በስተደቡብ በምትገኘው ዲላ ከተማ ባለው «ዲላ ዩኒቨርስቲ» በተገደለ አንድ ተማሪ ምክንያት ዩኒቨርስቲው ተረበሸ። ተማሪውን ገድሎታል በሚል የተጠረጠረው ተማሪም በቁጥጥር ስር ውሏል።

 

በዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ በረብሻው ወቅት ነበርን፤ ያሉ ተማሪዎች ለእንቢልታ ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ዓርብ የካቲት 14 ቀን 2000 ዓ.ም ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ሲሆን ዘውዱ አባተ የተባለ ተማሪ ከዶርሙ አካባቢ ደሙን እያዘራ ተማሪዎች ወደቆሙበት አስፓልት ላይ ወጥቶ ይወድቃል።

 

የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች የዘውዱን መውደቅና በደም መለወስ ሲመለከቱ፤ ጩኸት በግቢው ይበረክታል አፋፍሰው ወደ ሆስፒታል ቢወስዱትም ስለት ባለው ነገር የተወጋ በመሆኑና ጉዳቱ ከፍተኛ ስለነበር ህይወቱ ያልፋል።

 

የሞተው ተማሪና ገዳይ ነው ተብሎ የተጠረጠረው ተማሪ ብሔር የተለያየ በመሆኑ ረብሻው ወዲያውኑ ወደ ብሔር ብጥብጥ የማምራት አዝማሚያ አሳይቷል። ተማሪዎቹ እርስ በእርሳቸው መደባደብ ይጀምራሉ የቻለ በአጥር እየዘለለ፣ ያልቻለም እዛው ቀርቶ የድብድቡ ተሳታፊ ሆኗል። አንዳንዶች ደግሞ ዶርማቸውን ዘግተው ውስጥ በመደበቅ ረብሻውን አምልጠዋል።

 

ከቆይታ በኋላ ፖሊስ ወደ ግቢው ይገባና ለማረጋጋት ጥረት ያደርጋል፣ ረብሻው ጋብ ሊል ባለመቻሉም የፌደራል ፖሊስ ገብቶ ለማረጋጋት ይሞክራል።

 

ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ከ30 ደቂቃ ሲሆን መረጋጋት የታየ ቢሆንም በግርግሩ የተጐዱ ወደ 20 የሚጠጉ ተማሪዎች ወደ ሆስፒታል ሄደው አነስተኛ ህክምና ተደርጎላቸዋል፤ ሲሉ የአይን እማኞች ይገልፃሉ።

 

ተማሪዎቹን ለማረጋጋት የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ሊያስመሰግናቸው የሚገባ ርምጃ እንደወሰዱ የሚገልጹት እነኚህ ምንጮች አብዛኛው ተማሪ ግቢውን ጥሎ በመውጣት ወደ ቤተክርስቲያን እና መስጅድ በመሄድ ሲጠለሉ፣ የተወሰኑት ደግሞ በግቢው ይቀራሉ።

 

በግቢው የቀሩት ተማሪዎች እዚህ አናድርም በማለት ግቢውን ጥለው ለመውጣት ግብ ግብ ሲገጥሙ "እኔም ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር አብሬአችሁ አድራለሁ" በማለትና እዛው በማደር እንዲረጋጋ አድርገዋል ብለውናል።

 

በማግስቱም ከግቢው ውጭ ያሉ ተማሪዎችን በማግባባት ወደ ግቢው እንዲመለሱ ማድረጋቸውን እኚሁ ምንጮች ጠቁመዋል።

 

ተማሪዎቹ ግን ለቤተሰቦቻቸው ስልክ በመደወል ገንዘብ እንዲላክላቸው ካደረጉ በኋላ፤ በቅርብ ቤተሰብ ያላቸው ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲሄዱ ቤተሰብ በቅርብ የሌላቸው ደግሞ እዛው ከተማ ውስጥ ቆይተዋል።

 

እንደ ተማሪዎቹ ገለፃ ከሆነ የተወሰኑ ተማሪዎች ወደ ግቢው የተመለሱ ሲሆን ወቅቱ የተማሪዎች ፈተና በመሆኑ ወደ ግቢው የገቡ ተማሪዎች ፈተና ላይ እንደሆኑ ጠቁመዋል። ነገር ግን መንግስትም ሆነ የዩኒቨርስቲው አስተዳደሮች በጉዳዩ ላይ ጠንካራ ርምጃ ካልወሰዱ እንደማይገቡ በመግለጽ በከተማው ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸውልናል።

 

በዩኒቨርስቲው የሚገኙ ምንጮች እንደገለጹት ረብሻው በተፈጠረ ማግስት 21 ተማሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ ከተደረገባቸው በኋላ አምስቱ በጣቢያ እንዲቆዩ ሲደረግ ሌሎቹ እንዲለቀቁ ተደርገዋል።

 

ከትናንት በስቲያ ደግሞ የተማሪው ገዳይ እንደሆነ የተጠረጠረው ሌላው የዩኒቨርስቲው የ3ኛ አመት ተማሪ ገናና ጥሩነህ እና አንድ ሌላ ተማሪ በእስር እንዲቆዩ ተደርገው ሌሎቹ ሶስት ተማሪዎች መለቀቃቸውን ምንጮች ጠቁመዋል።

 

ዘውዱ አባተ የተባለውን ተማሪ በስለት ወግቶ ገሎታል የተባለው ተጠርጣሪ ገናና ጥሩነህ ከዲላ ከተማ ወደ ጠረፍ በሚወስደው መንገድ ወደ 36 ኪሎ ሜትር ርቀት ያህል ከተጓዘ በኋላ ፎቶግራፉ ተበትኖ ስለነበር በቁጥጥር ስር መዋሉ የፖሊስ ምንጮቻችን ጠቁመዋል።

 

የዲላ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት አቶ ታሪኩ በራሱ ለእንቢልታ ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የተነሳው ረብሻ በተማሪው ሕይወት ማለፍ የተደናገጡ ተማሪዎች በተፈጠረባቸው የረብሻ ስሜት እንደሆነ ገልፀው፤ በአሁኑ ሰአት ግን ተማሪዎቹ ተረጋግተው ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 

አያይዘውም ጉዳዩ በፍፁም ከብሔር ፀብ ጋር ያልተያያዘ መሆኑን ገልጸው ድርጊቱን ፈጽመዋል በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ የሚደረገው ምርመራ ሲጠናቀቅ በህግ የሚጠየቁ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

 

ሟች ተማሪ ዘውዱ አባተ በዩኒቨርስቲው የሶስተኛ አመት ተማሪ ሲሆን የትውልድ ቦታው በደቡብ ክልል ሆሳእና ከተማ ነው። ዩኒቨርስቲው ቅዳሜ የካቲት 15 ቀን 2000 ዓ.ም፤ የተማሪው አስክሬን ካረፈበት የምርመራ ቦታ በሳጥን በመረከብ እና 60 ሰዎችን የሚይዝ መኪና በማዘጋጀት በተማሪዎች ታጅቦ ቤተሰቦቹ ወደሚገኙበት ሆሳእና ከተማ እንዲሄድ መደረጉን ዩኒቨርስቲው ገልጿል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ