የፖሊስ ሠራዊት አባላት በመንግሥት ድርጊት ተማረዋል
Ethiopia Zare (ሐሙስ ሚያዝያ 8 ቀን 2001 ዓ.ም. April 16, 2009)፦ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ አያሌ የፌደራሉ መንግሥት እና የመዲናይቱ ፖሊስ አባላት ከደምወዝ ክፍያ ማነስ ጋር በተያያዘ ሥርዓቱን እያማረሩ መሆናቸው ታወቀ። ከመካከላቸውም "በኢትዮጵያ የሥርዓት ለውጥ ያስፈልጋል፣ በወገናችን እየተጠላን መኖሩ ታክቶናል፣ የእኛም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ሕይወት በቃላት ድርደራ ካልሆነ በቀር በተግባር አልተለወጠም" በማለት መንግሥቱን የሚያማርሩ እንዳሉም ምንጮች አረጋግጠዋል።
"ሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስመዝግባለች ቢባልም የእኛን ኑሮ ሊለውጥ የማይችል ወርሃዊ ደምወዝ እየተከፈለን አይደለም" የሚሉት የፖሊስ ሠራዊት አባላቱ፤ ቤተሰባቸውን መደጐም ቀርቶ ለራሳቸው በቂ ባልሆነ ደምወዝ ሥርዓቱን ማገለገል እንደማይቻላቸው በግልጽ እየተናገሩ ነው። የሥራ ዘርፍ የሚለውጡና ሠራዊቱን የሚከዱ እንደሚገኙበትም የሚጠቁሙት የፖሊስ ምንጮች፤ የኢህአዲግ መንግሥት በመጋቢት ወር አጋማሽ 2001 ዓ.ም. በሁርሶና በተለያዩ የሥልጠና ማዕከሎች አሰልጥኖ ካስመረቃቸው በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች በተጨማሪ አዳዲስ ሠልጣኞችን ለመመልመል በዝግጅት ላይ ነው ብለዋል።
በመጋቢት ወር አጋማሽ በሁርሶ የፖሊስ አባላት ሲመርቁ የፌዴራሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ወርቅነህ ገበየሁ "ተመራቂዎች በመጪው ዓመት የሚካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ከፀረ-ሠላም ኃይሎችና ከሁከተኞች የመጠበቅ አደራ አለባችሁ" የሚል መልዕክት ማስተላለፋቸው አይዘነጋም።
በደምወዝ መዘግየትና ካለው የኑሮ ሁኔታ ጋር ያልተመጣጠነ መሆን ምክንያት ብዛት ያላቸው የመንግሥት መስሪያ ቤት ሠራተኞች ምሬታቸውን እያሰሙ ሲሆን፣ በሕክምና ሙያ የተሰማሩና መምህራኖች የዚህ ችግር ከፍተኛ ተጠቂዎች ከመሆናቸውም በላይ በተለይ በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሠራተኞች ሥራቸውን በመተው ወደ ከተማ መሰደድ የዕለት ተዕለት ትዕይንት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
የአርሲ ነገሌ ነዋሪ የሆኑ ሁለት መምህራን የድርጅት አባል ካልሆናችሁ በሚል የሚደርስባቸውን ወከባና እንግልት መቋቋም ባለመቻላቸው አንዱ አዲስ አበባ የሀብታም ቤተሰቦችን ልጆች በግል እያስተማሪ መሆኑን ምንጮቻችን ገልጸው፤ ሌላኛው ሀገሩን ጥሎ ወደጎረቤት ሀገር መሰደዱን ለምወቅ ችለናል።



