• የሟች ቤተሰቦች ስጋት ላይ ወድቀዋል

• አንድ የክልል ባለሥልጣን ለገዳዩ ከለላ ሰጥቶታል ተብሏል

በሸዋዬ ካሳሁን

Ethiopia Zare (አርብ የካቲት 21 ቀን 2000 ዓ.ም. February 29, 2008) ከአዲስ አበባ በስተሰሜን ራያ ቆቦ በተባለው ከተማ በቂም በቀል በመነሳሳት የሰው ሕይወት ያጠፋው ግለሰብ እስካሁን ድረስ በቁጥጥር ሥር ሊውል ባለመቻሉ በየሟች ቤተሰቦች ስጋት ላይ ወድቀዋል።

 

 

ባለፈው ሣምንት ለሥራ ጉዳይ ወደ ራያ ቆቦ ከተማ ለሥራ ተጉዤ ነበር። በአንድ ቤተሰብ ላይ ስለተፈጸመ እና እየተፈጸመ ስላለው ወንጀል ለቤተሰቦቹ የቅርብ የሆኑ ምንጮች ጠቁመውኝ ወደ ሥፍራው አመራሁ። ባደረኩት የማጣራት ሙከራም የሚከተለውን መረጃ አገኘሁ። ጉዳዩ እንዲህ ነው፤ በቆቦ ከተማ ነዋሪ የሆኑ አቶ አማኑኤል ጌታነህ እና አቶ ዓለም ተስፋ ለረጅም ዓመታት በጉርብትና ኖረዋል። እነርሱ በጉርብትና እንደኖሩት ሁሉ ልጆቻውም በአንድ ሰፈር ተቀራርበው ያደጉ ናቸው። በአንድ ባልታሰበ ቀንም የአቶ አማኑኤል ጌታነህ ልጅ ሕይወቱ ያልፋል።

 

የቤተሰቡ ቅርብ ምንጮች እንደሚሉት ልጁ የሞተው በሰው እጅ ሲሆን፣ መንስኤው ደግሞ ከሰፈር ልጆች ጋር ባለመስማማት ነው። ልጃቸውን በሞት የተነጠቁት አቶ አማኑኤል የልጃቸውን ሕይወት ያጠፋው የአቶ ዓለም ልጅ እንደሆነ ሰው እንደነገራቸው በመግለጽ እሱኑ አምነው ”ልጅህ የልጄን ሕይወት በአጭሩ እንዳስቀረው የገባበት ገብቼ በአጭሩ አስቀርልሃለሁ፤ እሱን ካላገኘሁ ደግሞ በምትኩ አንተን እደፋሃለሁ” በማለት በተደጋጋሚ ሲዝቱ እንደነበር የገለጹት ምንጮች ጥር 8 ቀን 2000 ዓ.ም. አቶ ዓለም ተስፋ ባላሰቡት መንገድ በአቶ አማኑኤል ጌታነህ እጅ ሕወታቸው አልፏል።

 

ያነጋርኳቸው ሰዎች እንዳረጋገጡልኝ አቶ አማኑኤል ጌታነህ ግድያውን ከፈጸሙ በኋላ በቀላሉ በቁጥጥር ሥራ ማዋል ይቻል የነበረ ቢሆንም፤ በጋብቻ የሚዛመዳቸው በክልሉ ፍትሕ ቢሮ የሚገኝ ዘመዳቸው በሰጣቸው ከለላ ሊያመልጡ ችለዋል። የሟች ዘመዶች ገዳይ በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳዩ በሕግ አግባብ ታይቶ እልባት እንዲያገኝ ለሚመለከታቸው የፍትህ አካላት ቢወተውቱም ገዳይን በቁጥጥር ስር የሚያውል ወይም አየሁ የሚል እንዳልተገኘ ታውቋል።

 

በተቃራኒም ገዳይ በተለያየ መንገድ ለሟች ቤተሰቦች ”ገዳይ ይያዝልን” የሚል ጥያቄያቸውን እንዲያቆሙ በተደጋጋሚ መልክት ሲልኩ ቆይተው ጥያቄአቸው ተቀባይነትን ባለማግኘቱ ቤተ ዓለም በተባለችው የሟች ልጅ ላይ ተደጋጋሚ የመግደል ሙከራ ስለተደገረባት ሰላሟን እና ጤንነቷን በማጣቷ አካባቢውን ለቃ መጥፋቷን ወላጅ እናቷ ወ/ሮ ሀረጓ ቀነኒ በእንባ እየታጠቡ አጫውተውኛል።

 

ጉዳዩ የሚመለከተው አካል አቤቱታቸውን ሰምቶ መፍትሔ እንዲሰጣቸው እና ወንጀለኛው ግለሰብ በቁጥር ሥር ውሎ ቤተሰቦቻቸው በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲገቡ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ