Ethiopia Zare (አርብ ሚያዝያ 23 ቀን 2001 ዓ.ም. May 1, 2009)፦ “የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ” (ኢራፓ) የተባለ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ኢትዮጵያ ውስጥ ተመስርቶ ወደ ሥራ መግባቱን የድርጅቱ አመራር አባላት በአዲስ አበባ ላይ አስታውቀዋል።

 

የፖለቲካ ድርጅቱ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ አባላቱ ባለፈው ቅዳሜ ሚያዝያ 17 ቀን 2001 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተግባረዕድ ኢንዱስትሪያል ቴክኖሎጂ ኮሌጅ የስብሰባ አዳራሽ ባካሄዱት መስራች ጉባዔ የድርጅቱን መመስረቻ ሰነዶች ተቀብለው ፓርቲውን በይፋ ማቋቋማቸውን አመራሮቹ ዕሁድ ሚያዝያ 18 ቀን 2001 ዓ.ም. በራስ ሆቴል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

 

ፓርቲውን በመወከል መግለጫውን የሰጡት ሊቀመንበሩ አቶ አስፋው ጌታቸው ሲሆኑ፣ በዕለቱ ከተገኙት ጋዜጠኞችም የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ምላሻቸውን ሰጥተዋል። ፓርቲው አዲስ እንደመሆኑ መጠን በአብዛኛው ለአመራሮቹ ከገዢውም ሆነ ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምን መሠረታዊ አቋሞች እንደሚለይ እንዲያብራሩ የሚጠይቁ ነበሩ። አመራሮቹም በዕለቱ በሰጡት ምላሽ ከገዢውም ሆነ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች እንለይባቸዋለን ያሏቸውን አቋሞች ዘርዝረዋል።

 

በዕለቱ የድርጅቱ አመራር አባላት ከሰጡት ማብራሪያ መረዳት እንደተቻለው ፓርቲው በሀገሪቱ በተቃዋሚነት እየተንቀሳቀሱ ዓላማቸውን በሠላማዊ መንገድ እያራመዱ ካሉት ሕብረብሐራዊ ፓርቲዎች መሠረታዊ አቋሞች ብዙም የራቀ አቋም የሌለው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። ሆኖም በአካሄድ ደረጃ ከሌሎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለየ ሁኔታ የተለየ የትግል ስልትን እንደሚከተሉ በአፅንኦት ተገልጿል።

 

ቀደም ካሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንለይባቸዋልን ካሏቸው የትግል ስልቶች መካከል አንዱ፣ በትግል ሂደት የሚያጋጥማቸውን ድሎች በመጠበቅ የሚገኘውን ቀዳዳ እያሰፉ የሚሄዱ መሆናቸውን ነው የገለፁት። ባለፉት ጊዜያት በትግሉ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በውጤቱ ያገኟቸውን ድሎች ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል የሚሉት አመራሮቹ፣ በዚህ በኩል በቀጣይ ፓርቲያቸው መሰል ስህተትን እንደማይደግም ገልፀዋል።

 

ከዚህ ውጪም አመራሮቹ ከሌሎች ተቃዋሚዎች እንለይባቸዋለን በማለት የገለፁት “ከስሜት የፀዳ” ፖለቲካን እናራምዳለን በማለት ነው። እንደ አመራሮቹ አባባል ከሆነ ባለፉት ጊዜያት ስሜትና ፖለቲካ ያልተለዩበት ሁኔታ ስለነበር በውጤቱም ትግሉ ወደ ጥላቻ የማዘንበል አቅጣጫን ይዞ የነበረ መሆኑን በመግለፅ፤ አዲሱ ፓርቲያቸው ግን ይህንን መሰል የፖለቲካ አካሄድ ፈፅሞ እንደማይከተል ገልፀዋል። በመሆኑም ፓርቲያቸው ከዚሁ ጋርም በተያያዘ ‘ተቃዋሚ’ ተብሎ መጠራቱን እንደሚመርጥ አስታውቀዋል።

 

የተሠሩትን መልካም ሥራዎች እያበረታታና ድክመቶችን ነቀሶ እያሳየ የሚታገል ፓርቲ ነው ያሉት አመራሮቹ፤ በሂደትም በዚህ አቋሙ በርካታ ደጋፊዎችን በማፍራት በቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫም በመሳተፍ የተሻለ ውጤትን ለማስመዝገብ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልፀዋል። ከዚህ ውጪም አመራሮቹ ከገዢው ፓርቲ የሚለዩባቸውን መሠረታዊ አቋሞች የዘረዘሩ ሲሆን፣ ከዘረዘሯቸው አቋሞችም መካከል በዋነኝነት የሚከተሉት ይገኙባቸዋል።

 

የመሬት ይዞታ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገመንግሥት አንቀፅ 40 ንዑስ አንቀፅ 4 መሬት የህዝብና የመንግሥት ብቻ ነው በማለት የማይሸጥና የማይለወጥ መሆኑን በግልፅ ያትታል። ይህንንም አሠራር ገዢው ፓርቲ እየሠራበት የሚገኝ ሲሆን፣ በአንፃሩ በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመሬት ይዞታ ሕጉ መለወጥ አለበት የሚል አቋምን የያዙ ናቸው። የኢራፓ አመራር አባላትም በሰጡት ጋዜጣዊ መገለጫ ገዢው ፓርቲ መሬት የማይሸጥና የማይለወጥ ብሎም በመንግሥት ንብረትነት እንዲያዝ ማድረጉን እንደማይደግፉት ገልፀዋል። እንደ ፓርቲው አቋም ከሆነ የመሬት ባለቤትነት የሚወሰነው እንደ አስፈላጊነቱ እየታየ ነው። በዚህም መሠረት መሬት በተጠና ሁኔታ ባለቤትነቱ በመንግሥት፣ በግል ብሎም በውል ሊያዝ የሚችልበት አሠራር ሊፈጠር ይገባል ብለዋል። በመሆኑም መሬትን ግለሰቦች ሲፈልጉ ሊያወርሱ፣ ሊሸጡ፣ ሊያከራዩ የሚችሉበት ዕድል መፈጠር መቻል አለበት ብሎ ፓርቲያቸው እንደሚያምን ገልፀዋል።

 

ኢኮኖሚ

በበርካታ ዓመታት መንግሥት ግብርና መር የኢንደስትሪያላይዜሽን አካሄድ ነው እየተከተለ ያለው ያሉት አመራሮቹ፣ ሆኖም እስከዛሬ ለሁለት አስርት ዓመታት ለሚጠጉ ጊዜያት በአሠራሩ የታየው ውጤት እጅግ ደካማ ነው ካሉ በኋላ፤ አሠራሩ በአዲስ መልክ መቃኘት አለበት የሚል አቋም ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል። አሠራሩ ወደ ኢንደስትሪ ሊያሸጋግር አይደለም፣ ገበሬው የራሱን የምግብ ዋስትና እንኳን እንዲያረጋግጥ ማድረግ አልቻለም፤ ያሉት የኢራፓ አመራር አባላቱ፤ በመሆኑም ፓርቲያችን ፖሊሲውን እንደየ አስፈላጊነቱ ግብርና መር ኢንደስትሪ ወይም ኢንደስትሪ መር ግብርና አሠራር እየተፈራረቁ የሚደጋገፉበት የሆነ አሠራር መኖር አለበት ብሎ እንደሚያምን ገልፀዋል።

 

ይህንንም ሲያብራሩ የግብርና ግብዓት ባሉባቸው አካባቢዎች ፋብሪካዎች ሊቋቋሙ ይችላሉ፤ ፋብሪካዎች ባሉበት አካባቢ ደግሞ ገበሬው ለፋብሪካ ግብዓትነት የሚያገለግሉ የግብርና ምርቶችን ሊያመርት ይችላል ብለዋል። ይህም በመሆኑ ሁለቱን እያስተሳሰሩ የተሻለ ኢኮኖሚን መፍጠር እንደሚቻል እናምናለን በማለት ነው ያብራሩት።

 

የብሔር ብሔረሰቦች መብት

በሀገሪቱ የሚገኙ ማናቸውም ብሔሮች ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ሙሉ መብት አላቸው የሚል ጠንካራ አቋም ፓርቲያቸው እንዳለው ከገለፁ በኋላ ሆኖም “እስከመገንጠል” የሚለውን አቋም ግን እንደማይደግፉት ገልፀዋል። ብሔረሰቦች ለመገንጠል ጥያቄ እንዲያነሱ የሚያደርጋቸው ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ እስከሆነ ድረስ በሚኖረው ዲሞክራሲያዊ አሠራር ሙሉ ጥያቄያቸው የሚከበር ከሆነ ወደዚህ አይነት ጥያቄ አያመሩም የሚል እምነት ያላቸው መሆኑን ነው የገለፁት።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ