Prof. Ephraim Issac ፕ/ር ኤፍሬም ይስኃቅመግለጫው ስለይቅርታው ሂደት ዝርዝር የለውም

Ethiopia Zare (አርብ ሚያዝያ 23 ቀን 2001 ዓ.ም. May 1, 2009)፦ ከወ/ት ብርቱካን መታሰር በኋላ ድምፁን አጥፍቶ የነበረው የሀገር ሽማግሌዎች ሕብረት መሪ ፕሮፌሠር ኤፍሬም ይስኃቅ ኢትዮጵያ በመሆናቸው በዛሬው ዕለት በ10 ሰዓት በሸራተን ሆቴል መግለጫ እንደሚሰጡ ለጋዜጠኞች ጥሪ ያስተላለፉ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የቅንጅት አመራሮች የተፈቱበትን የይቅርታ ሂደት በሚገባ የማያብራራ መግለጫ ትናንት ኀሙስ ሚያዝያ 22 ቀን 2001 ዓ.ም. ለተወሰኑ ጋዜጠኞች በጽሑፍ ሰጥተዋል። የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

 

በፕሮፌሠር ኤፍሬም ከሚመራው የሀገር ሽማግሌዎች ሕብረት የቀረበ መግለጫ

 

የተወደዳችሁና የተከበራችሁ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ያላቸሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ሁሉ፦

 

ሽምግልና ማለት በተወደደችው ሀገራችን ለብዙ ጊዜ የታወቀና በጣም የተከበረ ባህል ነው። በሁለት በኩል ማስማማት ስለሆነ ከሁሉም ወገን ትዕግስትንና ጊዜን የሚጠይቅ አሠራር ነው።

 

እንደሚታወቀው ምርጫ 97ትን ተከትሎ የነበረው ችግር ሠላማዊ እልባት እንዲያገኝ እኛ የሀገር ሽማግሌዎች በራስ ተነሳሽነትና በሀገር ፍቅር ስሜት ችግሩን ለመፍታት ጥረት ማድረጋችን የሚታወስ ነው። ይህንን የሠላም ጥረት የጀመርነው ማንም ሳይጠይቀን እንደዜጋ የሀገር ሽማግሌ የተከሰቱትን ችግሮች ሠላማዊ መፍትሔ ተበጅቶላቸው አዲሱን ምዕተ ዓመት በሠላም እንድንጀምረውና በሀገራችን የሠላም የፍቅር የልማት የዕድገትና አብሮ መኖር ባህል በይበልጥ እንዲዳብርና በአንድ መንፈሥ የሀገራችንን ኅዳሴ ለማምጣት በማሰብ ነው።

 

በዚሁ መሰረት ከበርካታ ጥረቶች በኋላ በእግዚያብሔር ቸርነት፣ በመንግሥት በጎ ፈቃድ እንዲሁም በቀድሞ የቅንጅት አመራሮች ትብብር ጥረታችን ውጤታማ ሊሆን በቅቷል። ችግሩ በይቅርታ እንዲፈታ በተደረሰው መግባባት መሰረት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የይቅርታውን ማመልከቻውን በበጎ ፍቃድ ተቀብለው በሀገሪቷ ሕገመንግሥት ስርዓት መሠረት እንዲፈጸም ወደ ይቅርታ ቦርድ መርተዋል። ቦርዱም በዚሁ መሠረት ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ክቡር ፕሬዝዳንት ተቀብለው የይቅርታውን የውሳኔ ሃሳብ አጽድቀዋል።

 

በዚሁ የሀገር ሽማግሌዎች ተማፅኖ ግንዛቤ አግኝቶ እስረኞቹ ከነሙሉ መብታቸው ከእስራት በይቅርታ እንዲፈቱ ሆነዋል። እግዚያብሔር ይመስገን! መንግሥት የሀገራችንን ባህልና ሥርዓት ተቀብሎ፤ ይህንን የሽምግልና ተግባር እንዲፈጸም በማድረጉ በሀገር ሽማግሌዎችና በሀገሪቱ ስም ከፍ ያለ ምስጋና እናቀርባለን።እንዲሁም ለወንድሞቻችንና እህቶቻችን የቅንጅት አባላቶች እስረኞች በነበሩበት ወቅት ለሽምግልና ለሰጡን ክብር በጣም እናመሰግናለን።

 

ከፍ ሲል እንደተገለጸው እና የሀገር ሽማግሌዎች የሠላም ጥረቱን ስንጀምር የተከሰቱትን ችግሮች ለመፍታ ካለን መልካም ምኞትና ሀገራዊ ፍቅር እንዲሁም ለሀገራችን ለሽምግልና ከምሰጠው ክብርና ክብደት በመነሳት ብቻ እንጂ ውክልናም ሆነ ሥልጣኑ ኖሮን አይደለም።

 

የተከበራችሁ የተወደዳችሁ ወገኖቻን፦

 

የእኛ የሀገር ሽማግሌዎች ጽኑ ፍላጎትና ምኞት እንዲሁም ጥረት የተከፈተው የሠላም በር ሰፍቶ የይቅርታ መንፈሥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ነበር፤ ሆኖም ግን በዜና አውታሮች እንደተዘገበው ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በውጨው ሀገር ቆይታቸው ወቅት የተፈቱት ይቅርታ ጠይቀው እንዳልሆነ ተናግረዋል፤ ብለው ይህን በሦስት ቀን ውስጥ እንዲያስተባብሉ ከመንግሥት ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸውና ይህ ባይደረግ ግን ቀደም ሲል የተሳጣቸው ይቅርታ ተነስቶ እስራቱን እንዲቀጥሉ እንደተነገራቸው ሰምተናል። እኛም ቀደም ብለን በበኩላችን ወ/ት ብርቱካንን እንዲያስተባሉ ለምነናቸው ነበር፤ አሁን እስር ቤት መመለሳቸው በጣም አሳዝኖናል። የሀገር ሽማግሌዎች ይህን ተከሰተውን አዲስ ችግር ለመፍታት የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ጥረቱ በውጤት አልባነት ተደምድሞ ወ/ት ብርቱካን እስራቱን እንዲቀጥሉ ተይዘው ወደ ማረሚያ ቤት ገብተዋል።

 

ጉዳዩ አስቸጋሪ ቢሆንም ወ/ት ብርቱካን እስር ቤት ከገቡ ቀን ጀምሮ አንዳንድ ሰዎች በግምት እንደሚያስቡት ዝም አላልንም። በበኩላችን እንዲፈቱ በጎ ምኞታንን፣ ፀሎታችንን የመፍትሔ አቅጣጫዎች መፈለጋችንን አላቋረጥንም።

 

ይህ የይቅርታና የመቻቻል መልካም ጅምር ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚመለከታቸው ክፍሎች ሁሉ ነገሩን በሆደ ሰፊነት ተመልክተው ሠላማዊ መፍትሔ እንዲሰጡትና የተጀመረው የሠላም፣ የዲሞክራሲና የዕድገት ጥረት ይበልጥ እንዲሰምር የተቻላቸው ሁሉ እንዲያደርጉ እንማጸናለን።

 

ሠላም በምድራችን ይስፈን!

እግዚያብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

ሚያዝያ 22 ቀን 2001 ዓ.ም.

አዲስ አበባ

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ