አንድነት ስብሰባ ለማካሄድ ችግር እንደገጠመው ገለጸ
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ግንቦት 15 ቀን 2001 ዓ.ም. May 23, 2009)፦ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ለማካሄድ በተደጋጋሚ ቢሞክርም የስብሰባ አዳራሽ አከራዮች ከአዲስ አበባ መስተዳደር ፈቃድ እንዲያመጡ እንደሚጠይቋቸውና ፓርቲው የህዝባዊ ስብሰባውን በመስቀል አደባባይ እንዲያደርግ መገደዱን የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር ኢንጅነር ግዛቸው በተለይ ለኢትዮጵያ ዛሬ ገለጹ።
በአሁኑ ሰዓት የተለያዩ ስብሰባዎችን ለማድረግ ከስምንት በላይ የስብሰባ ቦታዎችን ቢጠይቁም የተሰጣቸው ምላሽ ተመሳሳይ መሆኑን የገለጹት ም/ሊቀመንበሩ ሠላማዊ ትግል የሚጠይቀውን ማናቸውንም ሂደቶች ባገኙት ቀዳዳ በመጠቀም ትግላቸውን ከመግፋት የሚያግዳቸው እንደሌለ ገልጸዋል።
አንድነት ፓርቲ ሕገመንግሥቱ በሚያዘው መሰረት ህዝባዊ ሰልፉን በመስቀል አደባባይ ለማድረግ ለአዲስ አበባ መስተዳደር ቢያሳውቅም መስተዳደሩ “ኃላፊነታችንን ለመወጣት ስለማንችል ስብሰባውን በአዳራሽ አድርጉ” የሚል ደብዳቤ ለድርጅቱ መጻፉን ለማወቅ ችለናል።
ፓርቲው ስብሰባዎችን በአዳራሽም ሆነ በአደባባይ እንዲያደርግ ሕጉ የሚፈቅድ ቢሆንም ስብሰባ በማካሄድ ረገድ የሚደርስበትን ችግር የሚመለከታቸው ክፍል ጋር በፍርድ ቤት ሂደቱን ለማየት መገደዱን ለመረዳት ችለናል።
ሂደቱን በቅርበት የተከታተሉ የፖለቲካ ተንታኝ አንድነት የአገዛዙን ሕግ በማጣቀስ የሚያደርገው እልህ አስጨራሽ ሂደት የሚበረታታና ለሠላማዊ ትግል ሂደት መንግሥት በሩን ቢጠረቅምም የሠላማዊ ትግልን የመረጡ ኃይሎች ምንም ተስፋ ሳይቆርጡ ትግላቸውን መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸው፤ ወያኔ በቀጣዩ ምርጫ ብቻውን ለመሮጥ የሚያስችለውን ጥርጊያ መቋቋሚያው መንገድና ፓርቲዎች ራሳቸውን ከሚገጥሙዋቸው አፈና በማናቸውም መንገድ በማምለጥ አገዛዙን ማሳጣት እንደሚኖርባቸው አስምረውበታል።
አያይዘውም ፓርቲው ስብሰባውን በአዳራሽ ለማድረግ ቢጠይቅም ባለአዳራሾች በሚደርስባቸው ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ማስፈራራት የማይመለከታቸውን ከአዲስ አበባ መስተዳደር ፈቃድ አምጡ ማለታቸው፤ መስተዳድሩም አሳውቃችኋል ደብዳቤ አንጽፍም በማለቱ ፓርቲው ሕገመንግሥቱ በሚያዘው መሰረት ህዝባዊ ስብሰባ በመስቀል አደባባይ አደርጋለሁ ብሎ በሠላማዊ ትግል ዘዴ መጠየቁ፤ ለዚህም ደግሞ የአዲስ አበባ መስተዳድር በአደባባይ ስብሰባ እንድታደርጉ ኃላፊነታችንን መወጣት ስለማንችል ስብሰባችሁን በአዳራሽ አድርጉ የሚል ምላሽ እንዲሰጥ ማስገደዱ የሚያሳየው የሠላማዊ ትግል ምንም መድረኩ ቢጠብም የተገኘውን አጋጣሚ በመጠቀም በሮችን ማስከፈት እንደሚቻል ማረጋገጫ መንገድ መሆኑን ነው ሲሉ ተንታኙ አስተያየታቸውን ደምድመዋል።



