የፀረ-ሽብር ረቂቅ አዋጁ በዜጐች ላይ ሽብር እየፈጠረ ነው
Ethiopia Zare (ሐሙስ ግንቦት 27 ቀን 2001 ዓ.ም. June 4, 2009)፦ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ለተወካዮች ምክር ቤት የተላከው የፀረ-ሽብር ረቂቅ አዋጅ የኢህአዲግ ደጋፊ ያልሆኑትን ነጥሎ የመምቻ የሕግ ሽፋን ይሆናል በሚል በዜጐች ላይ ሽብር እየፈጠረ መሆኑን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች አረጋገጡ።
ሰሞኑን በመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኤርሚያስ ለገሠ ማብራሪያ የተሰጠበት ይኸው ሕግ፤ በሕግ ባለሙያዎችና የፖለቲካ ሰዎች ዘንድ ጥርጣሬ የጫረ ሲሆን፣ “ዜጐችን ፀጥ ለጥ ብለው እንዲገዙ የሚያደርግ ነው” በማለት የሚፈጥረውን ሥጋት እየጠቀሱ ይገኛሉ።
አቶ ኃይሉ ጌታ በግል የጥብቅና ሙያ ላይ የተሰማሩ ግለሰብ በሕጉ ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ሲገልጹ “የፖሊስ መብት ያልተገደበ ነው፣ የጠረጠረውን ሰው መንገድ ላይ አቁሞ የመፈተሽ፣ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዛ ቤቱን የመበርበር፣ ስልኩን፣ ቢሮውን፣ ኢሜል አድራሻውን የመበርበር መብት መስጠቱ አሁን ካለንበት ኢህአዲግን በጥርጣሬ የማየት ሁኔታ አንፃር አደጋው የከፋ የሚሆን ይመስለኛል” ብለዋል።
ሌላዋ የሕግ ሰው ወ/ት ሠላማዊት እጅጉ በበኩላቸው “ሽብርተኝነት በኢትዮጵያ በመገናኛ ብዙኀን የሚጋነነውን ያህል አይደለም። ሕጉን ማውጣት የተለየ ጥቅም ለመንግሥት ከዓለም አቀፉ አካላት የሚያስገኝለት መንገድ ይኖራል። ሆኖም ግን መንግሥት እንደ መንግሥት ባያስበውም አንዳንድ የውንብድና ተግባር የሚሠሩ የመንግሥት ሰዎች ዜጐችን ማስፈራሪያና መጠቀሚያ ሊያደርጉት ይችላሉ” ብለዋል።
በሕጉ አንድ ተጠርጣሪ ተይዞ መረጃ ለመሰብሰብ የ28 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ የሚጠየቅበት ሲሆን፣ ምርመራው በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ይላል። ሕጉ ከፀደቀ የፌዴራል ፖሊሰ፣ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት እና ፍትሕ ሚኒስቴር የተቀናጀ ሥራ ለመሥራት ራሱን የቻለ የሥራ ክፍል ይኖራቸዋል።
ሚኒስቴር ዴኤታው እንዳመለከቱት የሽብርተኝነት ተግባር መፈጸም ብቻ ሳይሆን ማሰብ፣ መደገፍ፣ ማበረታታት ያስቀጣል። የሽብርተኝነትን ተግባር በሚዲያ መቀስቀስ፣ ማስተዋወቅና ማወደስ ወንጀል ይሆናል። መንግሥት ሽብርተኝነትን ለመቆጣጠር ስልክ፣ ኢንተርኔትና ሌሎች ማናቸውም የመገናኛ ዘዴዎች የመጥለፍ መብት አለው። ድንገተኛ ፍተሻ ማድረግ፣ በተጠርጣሪ ዜጐች ግቢ ውስጥ በስውር በመግባት መረጃ የሚሰበስቡ ኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች አስቀምጦ የመውጣት፣ ቤቱንም ሆነ ግለሰቡን መፈተሽ ለመንግሥት የተፈቀዱ ሆኗሉ። ማንም ሰው ቤት ካከራየ የተከራዩን ማንነት በ24 ሰዓት ለፖሊስ የማሳወቅ ግዴታም በሕጉ ተጠቅሷል። ይህ ሕግ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊና ሥርዓታቸው የሕጐች ሁሉ የበላይ ሕግ ነው የሚሉትን ሕገ-መንግሥት አተረጓጐም ሙሉ በሙሉ የሚፃረር እንደሚሆን ተጠቁሟል።
ሁኔታውን የተከታተሉ የፖለቲካ ተንታኝ እንዳሉት ከአሁን በፊት የኢህአዲግ አገዛዝ ለ18 ዓመታት ያለሕግ ትዕዛዝ ሰዎችን ሲያስር፣ ሲገድልና ሲያዋክብ መኖሩን አስታውሰው፤ ከ18 ዓመት በኋላ ያለውን ሂደት ደግሞ በሽብርተኝነት ምክንያት ከኃያላን መንግሥታት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጥበቅ ሕጋዊ በሆነ መልኩ ዜጎችን እያስፈራሩ ለመኖር የሚያስችለውን የዕድሜ ማቆያ ዘዴ እየተጠቀመ ነው ብለዋል። አያይዘውም ይህ አይነት የአገዛዝ ስልት በሠለጠነ ዘመን ላይ ሊሠራ የማይችልና ግለሰቦች የተጠላውን አገዛዝ ይበልጥ በጥርጣሬ እንዲያዩት የሚያደርግና መንግሥት ባላሰበው አቅጣጫ ደጋፊዎቹንም የሚያሳጣ አደገኛ አካሄድ መሆኑን አስምረውበታል። ተቃዋሚዎች ይህንን አካሄድ በጥልቅ እንዲመረምሩት ምክራቸውን ለግሰዋል።



