ሰኔ አንድ ቀን የዲሞክራሲ ሰማዕታት ቀን ታስቦ ዋለ
አንድነት ‘ፅናት’ መጽሔትን አስመረቀ
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሰኔ 2 ቀን 2001 ዓ.ም. June 9, 2009)፦ ሰኔ አንድ ቀን 2001 ዓ.ም. የዲሞክራሲ ሰማዕታት ቀን በማለት አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በዋና ጽሕፈት ቤቱ ቅጥር ግቢ ከምርጫ 97 በኋላ በግፈኛው የአጋዚ ጦር የተጨፈጨፉትን ሰማዕታት አስቦ መዋሉን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ዘገቡ።
በሥነሥርዓቱ ላይ ሥነ ጽሑፎች፣ ግጥሞችና የተለያዩ ሰማዕታቱን የሚያስታውሱ መጣጥፎች የቀረቡ ሲሆን፣ በአንዳንድ ጋዜጦችና በሸገር ራዲዮ ማስታወቂያውን የሰሙ ብዛት ያላቸው ሰዎችም የአንድነት ፓርቲ ቅጥር ግቢ ተሰብስበው ሰማዕታቶችን ዘክረው ማሳለፋቸውን ለማወቅ ችለናል።
ትናንት ተከብሮ በዋለው በዚሁ የሰማዕታት መታሰቢያ ቀንም አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ‘ፅናት’ የተሰኘውን ወርሃዊ መጽሔቱን የመጀመሪያ ዕትም ያስተዋወቀ ሲሆን፤ ‘ሰሙናይ’ የተባለውን ሣምንታዊ ኒውስ ሌተርም ማሣተም ጀመሩንም አስተዋውቋል።
ወርሃዊ መጽሔቱና ሣምንታዊ ኒውስ ሌተሩ ፓርቲው የሚያከናውናቸውን ማናቸውንም ክንውኖች ለህዝቡ ይፋ የሚያደርግበትና ከህዝብ ጋር ለመገናኘት ጥሩ ድልድይ ሊሆን እንደሚችል የተገመተ ሲሆን፤ በመጭው ምርጫ ድርጅቱ ለሚያከናውናቸው ዝግጅቶችም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ለማወቅ ተችሏል።



