ወ/ት ብርቱካን ቅዳሜ እንድትጎበኝ ተፈቅዶ በማግስቱ እሁድ ተከለከለ
አንድነት አዳራሽ ለመሥራት ከ4 - 7 ሺህ ዶላር ያስፈልገዋል ተባለ
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሰኔ 2 ቀን 2001 ዓ.ም. June 9, 2009)፦ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከአምስት ወራት የእስር ጊዜ በኋላ ቅዳሜ ዕለት ከተመደቡላት የዘወትር ጠያቂዎቿ በተጨማሪ ሌሎች ሰዎች የጎበኟት ሲሆን፤ በተቃራኒው እሁድ ዕለት በድጋሚ ከዘወትር ጠያቂዎቿ ውጭ ማንንም ሰው ማስገባት አይቻልም ተብሎ፤ በተለይ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር አባላቶች እስከመግፋት በደረሰ ማመናጨቅ እንዳባረሩዋቸው ለማወቅ ተችሏል።
በዘመድ፣ በጓደኞች፣ በጠበቃ፣ በኃይማኖት አባት፣ ... የመጎብኘት መብቷ በፍርድ ቤት ተወስኖ በማረሚያ ቤቱ ግን ተፈጻሚ ሳይሆን በመቅረቱ ማረሚያ ቤቱም ለሦስት ጊዜያት ፍርድ ቤት ቀርቦ ውሳኔውን ተፈጻሚ ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆነበት የወ/ት ብርቱካን የመጎብኘት ጥያቄ ሂደት፤ ባሳለፍነው ቅዳሜ ከቅርብ ቤተሰቦቿ ውጭ አንዳንድ የፓርቲው አመራርና ሌሎች ወዳጆቿ እንዲጎበኟት ተደርጎ የተለወጠ ቢመስልም፤ እሁድ ቀን ግን ከቅዳሜ በፊት ከተመደቡት ሰዎች ውጭ ማንም ሊጎበኛት እንደማይችል የእስር ቤቱ አስተዳደር ከልክሏል።
በተያያዘም ፓርቲው እስከ አሁን የአደባባይ ሰልፍ እንዳያደርግ የተከለከለ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባው ከንቲባ ጋር በተደረጉ ውይይቶች አዲስ አበባ አስተዳደር ሰልፉን መከልከል እንደማይችል ከንቲባው ከማሳሰባቸውም በላይ ከአስተዳደሩ ጋር በመወያየትና አንድነት ፓርቲ ሰልፉን ማድረግ ሕገ-መንግሥታዊ መብቱ መሆኑን ከንቲባው አቶ ኩማ ደመቅሳ ለአስተዳደሩ ማሳሰባቸውን ለመረዳት ችለናል። በአስተዳደሩና በከንቲባው መካከል ያለውን ልዩነት ለማጣራት ያቀረብነው ጥያቄ መልስ አላገኘም።
በዚሁ በሰልፍና ህዝባዊ ስብሰባ ጉዳይ ላይ ለማነጋገር ስልክ የደወልንላቸው የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ፤ ፓርቲው በአዳራሽ ሊያካሂድ ያሰበውን ህዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ በተለይ አዳራሽ ለማግኘት ባለመቻሉ ተፈጻሚ ማድረግ አለመቻሉንና ባለአዳራሾች ካለባቸው ፍራቻ ተጨማሪ በግንቦት ወር በነበረው ሠርግ አዳራሾች በመያዛቸው ቦታ ለማግኘት አለመቻላቸውን ገልጸዋል።
ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት ሰፊ በሆነው ጽሕፈት ቤቱ ቅጥር ግቢ አንድ ሰፊ የመሰብሰቢያ አዳራሽ መሥራት እንደሚቻልና እንዲህ አይነቱን የመሰብሰብ ችግር መፍታት እንደሚቻል የጠቆሙ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ፤ ሠላማዊ ትግል እልህ አስጨራሽ ከመሆኑ የተነሳ እንዲህ የሚከሰቱ ችግሮችን እየፈቱ ማለፍ አስፈላጊና ጥንቃቄ የሚገባው ጉዳይ ነው ብለዋል። አክለውም በብረት የሚገጣጠም ጥሩ የድንኩዋን አዳራሽ ለመሥራት ከ50 ሺህ እስከ 100 ሺህ የኢትዮጵያ ብር በቂ መሆኑን ገልጸው፤ ይህንን ለማሳካት ደግሞ በሠላማዊ ትግል በፅናት የሚያምኑ ሰዎች ግለሰባዊና ሀገራዊ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ሠላማዊ ትግል የሚፈጠሩ አፈናዎችን ለማለፍ ከመጋፈጥ መብለጥን፤ ከመግደል መሞትን፤ከመጣላትና ከማጣላት ማስታረቅን የሚጠይቅ ታላቅ ፈተና ያለው አካሄድ ነው ያሉት እኝሁ ተንታኝ፤ አንድ ግለሰብ ሊያወጣው በሚችለው ከ4 ሺህ እስከ 7 ሺህ የሚደርስ የአሜሪካን ዶላር አዳራሽ በመሥራት ቁርጠኛ ታጋይ መሆንን ለአገዛዙ ማሳየት ግድ ነው ብለዋል።
ሁኔታውን በሚመለከት ያነጋገርናቸው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ የጽሕፈት ቤቱ ግቢ ሰፊ መሆኑንና አዳራሽ ሊያሠራ የሚያስችል መሆኑን አውስተው፤ አዳራሽ ከተሠራ በየክፍለ ከተማው በመከፋፈል ህዝቡን ለመሰብሰብ ቀላል መንገድ እንደሚሆንላቸው አስምረውበታል።



