Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሰኔ 6 ቀን 2001 ዓ.ም. June 13, 2009)፦ የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ተመስገን ዘውዴ ማክሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2001 ዓ.ም. ሲያሰቃያቸው ለከረመው የአከርካሪ ሕመም መፍትሔ ለመፈለግ ወደ ታይላንድ መዲና ባንኮክ ሊያመሩ ነው።

 

በአሜሪካ ሀገር ለረዥም ዓመታት ሲኖሩ ቆይተው “በነፃ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ምርጫ” ተሳትፎ በማድረግ የህዝብ ወኪል ለመሆንና በሠላማዊ ትግል በሀገሪቱ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አምነው የሃሳብ ፍልሚያቸውን ለማካሄድ በምርጫ 97 ሰሞን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በቅንጅት ስም ወደ ፓርላማ የገቡትና በፓርላማ ሃሳባቸውን ያለፍራቻ በመግለጽ ብዙ ደጋፊዎችን ያፈሩት አቶ ተመስገን በጠና ታመው ለወራት ሲሰቃዩ የሰነበቱ መሆኑ ይታወቃል።

 

የድርጅታቸው አባልና ለእሳቸው የሚሆን የሕክምና ወጪ አፈላላጊ ቡድን ተጠሪ የሆኑት አቶ መሐመድ ዓሊ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል፤ አቶ ተመስገን ወደ ባንኮክ የሚያመሩ መሆናቸው የታወቀ ሲሆን፣ ምንም እንኳ የአቶ ተመስገንን የሕክምና ወጪ መሸፈን የሚችል ሙሉ ገንዘብ ለህዝብ ይፋ በሆነው የእርዳታ ጥሪ የተገኘ ባይሆንም፤ በአብዛኛው ለህክምና የሚያስፈልገው ገንዘብ ኢትዮጵያና ውጭ ሀገር ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም ከኢምባሲዎች የተገኘ ነው። ቀሪውን ገንዘቡን እያፈላለጉ ግለሰቡን ሕክምና ወደሚያገኙበት ሀገር መላክ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

 

ተያይዞ የመጣው ዜና፤ አቶ ተመስገን ወደ ባንኮክ ለሕክምና መብረር የሚስችላቸውን ነፃ የአየር ትኬት ያገኙ ዘንድ አፈ-ጉባዔ ተሾመ ቶጋ የበኩላቸውን ጥረት ያደረጉ መሆናቸውን ይጠቁሟል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ