የእነ ዳንኤል የይግባኝ አቤቱታ ለመጋቢት ተቀጠረ
Ethiopia Zare (ዓርብ የካቲት 28 ቀን 2000 ዓ.ም. March 07,2008)፦ ከቅንጅት አመራሮች ጋር ታስረው እስከ አሁን በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ የሚገኙት ሁለት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት አባላት አቶ ዳንኤል በቀለና አቶ ነፃነት ደምሴ "ጥፋተኛ ተብለን ልንቀጣ" አይገባም በሚል ያቀረቡት አቤቱታና ዐቃቤ ሕግ ደግሞ "ጥፋተኛ ተብለው የተቀጡበት አንቀፅ አንሷል፤ በዕድሜ ልክ እስራት ሊቀጡልኝ ይገባል" በሚል ያቀረበው የይግባኝ ማመልከቻ በተለያየ መዝገብ ለመጋቢት ወር ተቀጠረ።
አቶ ዳንኤል በቀለና አቶ ነፃነት ደምሴ፤ ፍርድ ቤት ቀርበው የመሰከሩባቸው ሰዎች የሀሰት ምስክሮች መሆናቸውን በመግለፅ "ምስክርነታቸው ውድቅ ሆኖ ወንጀሉን ያልፈፀምን መሆኑ ታውቆ በነፃ ልንለቀቅ ይገባል" ሲሉ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረቡት የይግባኝ ማመልከቻ ለመጋቢት 16 ቀን 2000 ዓ.ም. ተቀጥሯል።
ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ተከሳሾቹ ጥፋተኛ ሊባሉ የሚገባው ሕገመንግሥቱንና ሕገመንግሥታዊ ስርዓቱን በኃይል በማፍረስ ሞክረዋል በሚለው በማስረጃ ተረጋግጦባቸው እያለ ፍርድ ቤቱ ያለአግባብ ዝቅተኛ ቅጣት በሚያሰጠው አንቀፅ ጥፋተኛ ማለቱ አግባብ አይደለም ብሏል።
ተከሳሾቹ የቅንጅት አመራሮች በተቀጡበት አንቀፅ ሊቀጡ ይገባል ሲልም ጠይቋል። ይህም የዐቃቤ ሕግ የይግባኝ ማመልከቻ ለመጋቢት 25 ቀን 2000 ዓ.ም. ተቀጥሯል።



