አንድነት በደብረማርቆስ የተሳካ ስብሰባ አካሄደ
“አቶ ስዬ አብርሃ አንድነትን ለመቀላቀል ጥያቄ አላቀረቡም፤ ማመልከቻም አላስገቡም” ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ
Ethiopia Zare (አርብ ሰኔ 26 ቀን 2001 ዓ.ም. July 3, 2009)፦ አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ባለፈው እሁድ በደብረ ማርቆስ ከተማ ያካሄደው ስብሰባ ብዙ ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ ተገለጸ።
በስብሰባው አካባቢ ህዝብ እንዳይገኝ የአካባቢው ባለሥልጣናት ጥረቶችን ቢያደርጉም ህዝቡ በብዛት በመውጣት በድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር ኢንጅነር ግዛቸው የተመራው የልዑካን ቡድን በጠራው ስብሰባ ላይ መሳተፉን ለመረዳት ችለናል።
ፓርቲው ከህዝብ ጋር በአሁኑ ሰዓት በሀገሪቱ ስላለው ጠቅላላ ሁኔታ የተወያየ ሲሆን፣ ከአካባቢው ነዋሪዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች ላይ ምላሽ መስጠቱ ታውቋል። በቀጣይም በተለያዩ ክልሎች ተመሳሳይ ህዝባዊ ስብሰባዎችን እንደሚያካሂድ የድርጅቱ ህዝብ ግንኙነት ቢሮ አስታውቋል።
በተያያዘም አቶ ስዬ አብርሃ አንድነት ፓርቲን ተቀላቀሉ የሚለውን ዘገባ በሚመለከት ያነጋገርናቸው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ አቶ ስዬ እስካሁን የፓርቲውን የምዝገባ ቅጽ እንዳልሞሉና ፓርቲውን ለመቀላቀል ምንም አይነት ጥያቄ እንዳላቀረቡ ገልጸው፤ ፓርቲያቸው ምንም አይነት የሚሸፋፍነው ነገር እንደሌለና የሆነውን ሆነ ከማለት ወደኋላ እንደማይል አስረድተዋል።
የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በፓሊሶች ታፍና ወደ ቃሊቲ እስር ቤት ከተጣለች 186ኛ ቀኗ መሆኑ ይታወቃል።