አርቲስት ዓለሙ ገብረአብ Alemu Gebreabዛሬ አርብ ሥርዓተ ቀብሩ ተፈጸመ

Ethiopia Zare (አርብ ሐምሌ 3 ቀን 2001 ዓ.ም. July 10, 2009)፦ አንጋፋው ከዚህ አለም በሞት መለየቱንና ዛሬ ዕለተ አርብ ሐምሌ 3 ቀን 2001 ዓ.ም. ከቀኑ 6 ሰዓት ከ30 በየካ ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን መካነ-መቃብር ሥርዓት ቀብሩ መፈጸሙን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች አረጋገጡ።

 

በ1948 ተወልዶ ትናንት ሐሙስ ሐምሌ 2 ቀን ማለዳ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ዓለሙ ገብረአብ፤ በትወና ሙያ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ እንደነበር በቀብር ሥርዓቱ የተነበበው የሕይወት ታሪኩ ያስረዳል።

 

በ1967 በእጩ ተዋናይነት በብሔራዊ ቴአትር ሲሠራ የቆየው ዓለሙ፤ ትምህርቱን ለማሻሻል ወደ ሶቭየት ህብረት በማምራት በቴአትር የማስተርስ ዲግሪውን ይዞ በመመለስ፤ ከ1975 ጀምሮ በቲያትር ቤቱ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ሲሠራ ቆይቷል። በቴአትር እና በሙዚቃዊ ተውኔት ዝግጅት፣ በተዋናይነት፣ በፊልም ሥራዎች ከ25 ዓመታት በላይ ያገለገለው ዓለሙ ባደረበት ሕመም ከዓመት በላይ አልጋ ላይ ውሎ ነበር።

 

በ1993 ዓ.ም. መንግሥት ለአንድ ዓመት ከሥራ አግዶት የነበረ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊውን አርቲስት “ኤርትራዊ ነው” በማለት በወቅቱ ከሀገር እንዲወጣ የሚል ምክንያት ቀርቦበት እንደነበር አርቲስቱ በወቅቱ መግለጹ ታውቋል።

 

ሆኖም በኤርትራ መገንጠል ወቅት አንዳችም ዓይነት እንቅስቃሴ ያላደረገ በመሆኑ፣ እንዲያውም በወቅቱ ለሠላምና መረጋጋት ተመርጦ ኅብረተሰቡን ያገለግል እንደነበር አርቲስቱ ገልጾ ነበር። ለዓመት ያህል ከሥራና ከደሞዝ የታገደው ዓለሙ፤ ጉዳዩ ተጣርቶ ወደ ሥራው ሲመለስ ውዝፍ የዓመት ደሞዝ ተከፍሎት ነበር። በዚህም የተነሳ በኢትዮጵያዊነቱ መኩራቱን ደጋግሞ ለወዳጆቹ ይናገር ነበር።

 

በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሲራክ ታደሰን ሞት በምሽት የሁለት ሰዓት ዜና ላይ “አርቲስት ዓለሙ ገብረአብ አረፈ” በማለት በመዘገቡ ከፍተኛ ኀዘን ተስምቶት የነበር ሲሆን፤ በወቅቱ በሆስፒታል አልጋ ላይ እንደነበርም ታውቋል። አርቲስት ዓለሙ ባለትዳርና የሦስት ወንድ ልጆች አባት ሲሆን፣ ሥርዓተ ቀብሩ በርካታ የሙያ አጋሮቹና አድናቂዎቹ በተገኙበት ነው ዛሬ የተፈጸመው።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ