Ethiopia Zare (ዓርብ ሐምሌ 17 ቀን 2001 ዓ.ም. July 24, 2009)፦ በምሥራቅ ኢትዮጵያ ግዛት ድርቅ ተባብሶ ቀጥሏል። ከመስከረም ወር 2001 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሐምሌ 12 ቀን 2001 ዓ.ም. ድረስ ከአስቦት እስከ ካራሚሌ ባለው 130 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ የዝናብ ዘር አለመታየቱን የሜኤሶ የበሮዳ እና የአጎራባች ቀበሌ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

 

በማሽላ ሰብል፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንደዚሁም በቡና አምራችነታቸው በሚታወቁት እና ከፍተኛ የገቢ ምንጫቸውም ጫት እና የከብቶች ተዋጽኦ መሆኑ በሚታወቀው የምሥራቅ ኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች በርካታ ወረዳዎችን ያካለለው ድርቅ በቤት እንሰሳት በተለይም በቀንድ ከብቶች ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት ማስከተሉን ለማወቅ ተችሏል።

 

ማዕከላዊውና የክልሉ ኦሮሚያ፣ ሐረሪና ሶማሊያ “መንግሥታት” የአደጋውን መከሰት ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ግብር ሰናይ ድርጅቶች ይፋ ያድርጉት እንጂ፤ ድርቅ በፀናባቸው ሥፍራዎች የሚገኙ ገበሬዎች የመኖሪያ ቀያቸውን ለቀው ለም ሊሆን ይችላል ወዳሉት ሥፍራዎች መሰደድ ጀምረዋል።

 

ለአንድ ዓመት የዘለቀው የዝናብ መንጠፍ የአሰቦት፣ የሜኤሶ፣ የሂርና የበሮዳ ቀበሌ ገበሬ ማኅበሮችን ብቻ ሳይሆን፤ ጅጅጋን ጨምሮ የደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያን የታወቁ በድርቅ ተጠቂ ዞኖችንም አካሏል። ይኸው የድርቅ አደጋ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የቀንድና የጋማ ከብቶችን በፌደራል መንግሥቱ የሶማሊያና የኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ሊፈጅ እንደሚችል ቅደመ ሁኔታው አመልክቷል።

 

ከሥፍራው የተገኘው ተጨማሪ መረጃ እንዳመለከተው በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የድርቅ አደጋ በተስተዋለባቸው አካባቢዎች ቅጽበታዊና ከባድ ዝናብ የሚጥል ከሆነ፤ በአሁኑ ወቅት አጥንታቸው ገጦና ከቆዳቸው ተጣብቆ የሚታዩት በሺህ የሚቆጠሩ የቀንድ ከብቶች በሕይወት የመሰንበት ዕድላቸው የተመናመነ ነው። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ቀውስ ምክንያት ለወጪ ገበያ ከምታቀርባቸው ቡና፣ የእንሰሳት ተዋጽኦ፣ ጫት እና ሌሎች የእርሻ ሰብል ውጤቶች የምታገኘው ገቢ በእጅጉ የቀነሰባት ሲሆን፣ ከቀናት በፊት ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅት እንደስታወቀው የምጽዋት ጠባቂ እጆች ቁጥር ከ4 ሚሊዮን ወደ 6 ሚሊዮን አሻቅቧል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ