Ethiopia Zare (ሐሙስ ሐምሌ 23 ቀን 2001 ዓ.ም. July 30, 2009)፦ በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ከተማ የዝርፊያ፣ የቅሚያና የሥርቆት ወንጀል ተግባሮች በአስከፊ መልኩ የጨመረ ሲሆን መሠል ወንጀሎች አስቀድሞ በብዛት ይታዩባቸው ከነበሩት ሥፍራዎች ባልተናነሰ ሁኔታ በሌሎችም የከተማይቱ ክፍሎች በሰፊው እየተሰተዋሉ ናቸው፡፡

 

ከሰኔ ወር 2001 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሐምሌ ወር ድረስ በአዲስ አበባ የተፈጸሙት የዝርፊያና የቅሚያ ወንጀሎች ዘረፋውና ቅሚያው በተፈጸመባቸው ወገኖች ላይ ከአካል ጉዳት እስከ ሕይወት ማጥፋት ድረስ የዘለቀ ጠንቅ የነበራቸው እንደነበሩ የመዲናይቱ ፖሊስ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

 

ዘራፊዎቹ በተጠኑ አካባቢዎች ገንዘብና ንብረት ለመዝረፍ ሲነቃነቁ ድርጊታቸውን ለማስቆም ጥረት የሚያደርገውን ግለሰብ በፈለጉት ደረጃ ማጥቃት የሚችሉበትን ዘዴና ትጥቅ የሚታጠቁ በመሆናቸው፤ የዘራፊዎቹን ተደጋጋሚ ድርጊት ማስቆም እንዳልተቻለ የየካና የአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ፖሊስ የወንጀል ክትትል ቡድን ባልደረቦች አስረድተዋል፡፡

 

የቅሚያና የሥርቆት ወንጀሎችን የሚፈጽሙት የፖሊስና የጦር ሠራዊት ዩኒፎርሞችን በመልበስ ከመሆኑም ሌላ በጦር መሣሪያ የታገዘ የዝርፊያና የቤት ሠብሮ ስርቆት ወንጀል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማይቱ እየበረከተ መምጣቱን ያሳወቁት አንድ የፖሊስ ባልደረባ፤ ሐምሌ 14 ቀን 2001 ዓ.ም ለሐምሌ 15 ቀን አጥቢያ በአዲስ አበባ ከተማ ከምኒልክ ሐውልት ፊት ለፊት “እጅጋየሁ” በተሰኘው ፎቶ ቤት ውስጥ የተፈጸመው የስርቆት ወንጀል እንደ ምሳሌ መሆኑን በዋቢነት ጠቅሰዋል፡፡

 

መሰል ወንጀል ተግባራት በኳስ ሜዳ፣ በመሳለሚያ፣በገርጂ፣ በኮተቤ መሳለሚያ፣ በላፍቶ፣ በአየር ጤና እና በሌሎችም የአዲስ አበባ ንዑስ መንደሮች በተደጋጋሚ እንደሚፈጸም ያስታወቀው ፖሊስ፣ ከብሔራዊ ቤተ-መንግስት አቅራቢያ ባለው “ፊት በር” በተባለው መንደር አንድ ግለሰብ በሰኔ ወር መጨረሻ 2001 ዓ.ም በዘራፊዎች ጥቃት ንብረቱን የተቀማ ከመሆኑም ባሻገር ሕይወቱም ያለፈ መሆኑ ታውቋል።

 

ድርጊቱን የፈጸሙትንም ወንጀለኞች ለመያዝ ክትትል እያደረግን ነው ከማለት ውጭ ምንም አይነት እርምጃ የተወሰደበት አካል እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል። በከተማይቱ እየሠፋ ለመጣው የወንጀል ተግባር መንሰኤው የኑሮ ውድነት፣ የሥራ ዕጦትና ሥርዓት አልባኝነት መሆኑን የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ያሰመሩበት ሲሆን ዲሞክራሲ ይከበር፣ የሰው ልጆች መብት ይጠበቅ በማለት ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያለምንም ርህራሄ የጥይተወ ውርጅብኝ ያወረደ ሰራዊት እንዲህ አይነት አስከፊ ወንጀል ላይ በተሰማሩ ግለሰቦችን አድኖ የመያዝ አለመቻሉ አገዛዙን ትዝብት ላይ ይጥለዋል ሲሉ የፖለቲካ አዋቂዎች ተችተዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ