Bashir Mukhtal, አቶ በሽር ሙኽታልEthiopia Zare (ሰኞ ሐምሌ 27 ቀን 2001 ዓ.ም. August 3, 2009)፦ የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆነውና የካናዳ ዜግነት ያለው አቶ በሽር ሙኽታል በኦብነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነትና በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ ክስ ተመስርቶበት ሲከራከር ከቆየ በኋላ፤ ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 27 ቀን 2001 ዓ.ም. የዋለው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንደፈረደበት የኢትዮጵያ ዛሬ ሪፖርተር ከአዲስ አበባ ዘገበ።

 

እ.ኤ.አ. 2006 የኬንያ መንግሥት በቁጥጥር ስር ካዋለው በኋላ፤ ለኢትዮጵያ መንግሥት አሳልፎ የተሰጠው አቶ በሽር ሙኽታልን ዓቃቤ ሕግ በአራት የተለያዩ ክሶች ከስሶት የሞት ቅጣት ይፈረድበት በማለት ሲከራከር ቆይቷል። ዛሬ የዋለው ችሎት የዓቃቤ ሕግን የሞት ቅጣት ክርክር ውድቅ በማድረግ የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ቅጣት ወስኖበታል። ዓቃቤ ሕግ የሞት ቅጣት እንዲፈረድለት ይግባኝ ሊል እንደሚችል የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገልፀዋል።

 

ባለፈው ሐምሌ 20 ቀን 2001 ዓ.ም. በዋለው ችሎት፤ ፍርድ ቤቱ ካናዳዊው በሽር ሙኽታልን ”ጥፋተኛ” ያለው በአራቱም የዓቃቤ ሕግ ክሶች መሆኑ ታውቋል። ክስ አንድ - እ.ኤ.አ ከ1999 - 2006 የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በመሆኑ፣ ክስ ሁለት - የኦብነግ ሚሊሺያዎችን ኤርትራ ውስጥ በሚገኝ ካምፕ ውስጥ ወታደራዊ ሥልጠና በመስጠትና በማስታጠቅ፣ ክስ - ሦስት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ ጦርነት በማወጅ፣ ክስ - አራት ከኤርትራ መንግሥትና ከሶማሊያ እስልምና ምክር ቤቶች ሕብረት አማጽያን ጋር በመተባበር ሕገመንግሥቱን ለማፍረስ ሙከራ አድርጓል የሚሉት ናቸው የዓቃቤ ሕግ ክሶች።

 

በዚሁ የክስ ሂደት ላይ ዓቃቤ ሕግ ስድስት ግለሰቦችን በምስክርነት አቅርቦ ማስመስከሩ ታውቋል። በተጨማሪም ከመከላከያ ፍርድ ቤት የተሰጠ የውሳኔ ግልባጭ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት ዓቃቤ ሕግ በሰነድ ማስረጃነት አቅርቧል።

 

አማርኛ ቋንቋ የማይናገረው አቶ በሽር በተደጋጋሚ የኦብነግ አባል አለመሆኑንና የተከሰሰውም አያቱ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባርን (ኦብነግ) ከበርካታ ዓመታት በፊት ስለመሠረቱ ነው መሆኑን በተደጋጋሚ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል። ኦብነግ በ1976 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1985) እንደተቋቋመ ይታወቃል።

 

በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራው ካናዳዊ ዜግነቱን እ.ኤ.አ. በ1994 ያገኘው አቶ በሽር ሙኽታል፤ የሶማሌ ጎሣ ካላቸው ቤተሰቦቹ ኢትዮጵያ ውስጥ በኦጋዴን የተወለደው የዛሬ 40 ዓመት ነው። በ11 ዓመቱ ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ ሶማሊያ ከገባ በኋላ እ.ኤ.አ. 1991 ወደ ካናዳ ጠቅልሎ ገብቷል። ነዋሪነቱም በካናዳ ዋና ከተማ ቶሮንቶ እንደሆነ ታውቋል።

 

እ.ኤ.አ. 2006 መጨረሻ ላይ የሶማሊያንና የኬንያን ድንበር በመሻገር ላይ እንዳለ በእስልምና አክራሪነት ተጠርጥሮ በኬንያ መንግሥት ነበር የተያዘው። የኬንያ መንግሥትም ለወር ያህል ካሰረው በኋላ ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ለኢትዮጵያ አሳልፎ ሰጥቶታል። የኢትዮጵያ መንግሥትም ከጠበቃው፣ ከካናዳ ኤምባሲ ባለሥልጣናት እና ከቤተሰቦቹ ጋር እንዳይገናኝ አድርጎ ሁለት ዓመት ካለምንም ክስ አስሮታል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ