የሳምንቱ አንኳር ወሬዎች

ከጥቅምት 3 - 9 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የኢትዮጵያ የአየር ኃይል ጄት መከስከስ

ኢዛ (ከጥቅምት 3 - 9 ቀን 2012 ዓ.ም.) ከሰሞናዊ ክስተቶች ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተዋጊ ጀት ተከስክሶ ሁለት የተዋጊ ጄቱ አብራሪዎች ሕይወት አልፏል።

ተዋጊ ጀቱ የተከሰከሰው መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ከደብረዘይት የአየር ኃይል ጣቢያ በመነሣት በረራ ከጀመረ በኋላ ነው። በውስጡ አንድ አሠልጣኝና ሠልጣኝ የነበሩ ሲሆን፣ ሁለቱም ሕይወታቸው ማለፉ ተነግሯል።

የምገባ ፕሮግራሙ

የአዲስ አበባ አስተዳደር በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ ከ300 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች ምገባ የጀመረው በዚሁ ሰሞን ነበር።

የምገባ ፕሮግራሙን የከተማዋ ም/ከንቲባ ኢንጂንየር ታከለ ኡማ ተማሪዎቹ የሚመገቡትን ምግብ በመቅመስ አስጀምረዋል።

ከዚህ የምገባ ፕሮግራም ቀደም ብሎ በአዲስ አበባ ውስጥ ላሉ ለ600 ሺሕ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ለ2012 የትምህርት ዘመን የትምህርት መገልገያ መሣሪያዎች በነፃ የተበረከተ ሲሆን፣ ለእያንዳንዱ ተማሪም ዩኒፎርም በማሰፋት አስረክቧል። አስተዳደሩ ይህንን ያደረገው ከተለያዩ ተቋማት እና ግለሰቦች ባሰባሰበው ድጋፍ ነው።

የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ የዓለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚነት

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የዓለም የሰላም የኖቬል ሽልማት ከተሰማ በኋላ ሁሉም በየፊናው ስሜቱን ከገለፀባቸው ትዕይንቶች አንዱ ነው።

ከዱባይ መንግሥት ጀምሮ የተለያዩ ተቋማት ደስታቸውን የገለጹበት መንገድ ግን ከሌላው በተለየ ሊያስገርም ይችላል። በስደት በዱባይ ያሉ ወገኖች በከተማዋ ግዙፍ ሕንፃ ላይ የተመለከቱት የአገራቸውን ባንዲራ የእነርሱ ስለመሆኑ ስለአገራቸው በኩራት ለመግለጽ እድል ያገኙበትን አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል። በዱባይ ኢትዮጵያውያን ኤርትራውያን ደስታቸው በተለየ መንገድ መግለጻቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል፤ በጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የኖቤል ሽልማት ዙሪያ ሰፋ ያለ ጥንክር ለማስነበብ ቃል በገባው መሠረት፣ ጥንክሩን እዚህ በመጫን እንዲያነቡ ይጋብዛል!

የአፋምቦ ጥቃትና እስካሁን ያልጠራው መረጃ

ከፀጥታ ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ ብዙ የመገናኛ ሽፋን ካገኙት ክስተቶች አንዱ በአፋር ክልል በአፋምቦ ወረዳ የተፈፀመው ጥቃት ነው። እስካሁን በጥቃት አድራሾቹ ማንነት ላይ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ቢሆንም፤ በጥቃቱ 18 ሰዎች ሞተዋል።

ሕፃናትን ጭምር ሰለባ ባደረገው በዚህ ግጭት የቆሰሉት 36 እንደሆኑ ተጠቅሷል።

የጥቃቱ አድራሾች ድንበር ተሻግረው በመጡ ታጣቂዎች የተፈፀመ ነው የሚለው መረጃ ጐልቶ የተሰማ ቢሆንም፤ መከላከያ ከዚህ የተለየ ነው ብሏል። ይህ መረጃ ግን የአፋር ክልል ነዋሪዎች ዘንድ እምነት ስላሳደረ፤ ባለፈው ሳምንት በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ውስጥ ተከታታይ ሰላማዊ ሠልፍ እንዲካሄዱ ምክንያት ሆኗል።

“የሕፃናት ሞት ይቁም!” ከሚሉ መፈክሮች ጀምሮ የተለያዩ መልእክቶችን የያዙ መፈክሮችን የያዙ ሠልፈኞች የአፋር ክልል ላይ በውጭ ኃይሎች፤ በተለይም በአልሸባብ የሚፈፀሙ ጥቃቶች እንዲቆምና የፌዴራል መንግሥት ሉአላዊነትን እንዲያስከብር የጠየቁበትም ነበር።

ይህ ሰፊ ተቃውሞ የተስተናገደበትንና ሠላማዊ ሠልፍ ጭምር የተደረገበት ጥቃትን በሚመለከት ለማጣራት የሰላም ሚንስቴር መሥሪያ ቤት አንድ አጣሪ ቡድን ወደዚያው ልኳል።

የደረሰበት ውጤት ይፋ ባይደረግም፤ በአፋምቦ የደረሰው ጥቃት በማን እንደተፈፀመ፣ ለምን እንደተፈፀመ እስካሁን በተጨባጭ በይፋ አለመገለፁ ግን ሁኔታውን እንቆቅልሽ አድርጐታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከጥቃቱ በኋላ የአፋርና የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንቶችን ጥቅምት 7 ቀን 2012 ዓ.ም. በማሥጠራት አነጋግረዋቸዋል። ንግግራቸው በአፋር ክልል ከተደረገው ጥቃት ጋር በተያያዘ የመከሩበት እንደሆነ የሚያመላክት ጭምር ነበር።

ፈጣኖቹ የባንክ አክሲዮን ሽያጮች በኢትዮጵያ

ከሰሞኑ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ውስጥ የአገሪቱን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ለመቀላቀል አክሲዮን ሽያጭ ላይ የነበሩ ሁለት በምሥረታ ሒደት ላይ የሚገኙ ባንኮች፤ ባንክ ለማቋቋም የሚያስችላቸውን ካፒታል ማሟላት መቻላቸው ነው።

በአገሪቱ የባንክ ምሥረታ ሒደት በፍጥነት ባንክ ለማቋቋም የሚያስችል ካፒታል በማሰባሰብም ቀዳሚ አድርጓቸዋል። እነዚህ አክሲዮን ሽያጭ በጀመሩ በወራት ውስጥ ባንክ ለማቋቋም ከሚያስፈልገው 500 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ የቻሉት አማራና ዘምዘም ባንኮች ናቸው።

በቀድሞ የገቢዎች ሚንስትርና በእስር ላይ ከቆዩ በኋላ በተፈቱት አቶ መላኩ ፈንታ የአደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢነት የሚመራው፤ አማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር ባንክ ለመመሥረት የሚያስችለው ካፒታል ማሟላት የቻለው አክሲዮን ሽያጩን በጀመረ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ የተከፈለ አክሲዮኖችን የገዙት ከ15 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖች ናቸው።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመሥጠት የሚችል ባንክ ለመመሥረት የሚያስችለውን ካፒታል ማሰባሰብ መቻሉን ያስታወቀው ዘምዘም ባንክ ደግሞ፤ አክሲዮን መሸጥ በጀመረ በአራት ወር ውስጥ ከ650 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል አሰባስቧል።

ከሁለቱ ባንኮች ከተሰጡ መግለጫዎች መረዳት እንደሚችለው፤ አሁን ባንክ ለማቋቋም የሚያስችላቸውን ካፒታል በማግኘታቸው ባንኮቻቸውን ከ3 እስከ 6 ወሮች ውስጥ ሥራ የሚያሥጀምሩ መሆኑን ነው።

እነዚህ ባንኮች ወደ ገበያ ውስጥ ሲገቡ በኢትዮጵያ የሚገኙ የግል ባንኮችን ቁጥር ወደ 18 ከፍ ያደርጋል። በአሁኑ ወቅት ሁለት መንግሥታዊ ባንኮች ያሉ መሆኑ ይታወቃል። በሌላ በኩል አሁን ገበያ ውስጥ ለመግባት መጨረሻ ምዕራፍ ላይ ከደረሱት ሁለቱ ባንኮች ሌላ፤ ከወለድ ነፃ ባንክ ለመክፈት ሦስት ባንኮች አክሲዮን ሽያጭ ላይ ሲሆኑ፤ ጐሕ የተባለ በቤቶች ኢንቨስትመንት ላይ የሚሠራ ባንክም በአክሲዮን ሽያጭ ላይ ነው። ገዳ የሚል ስያሜ ያለው ባንክም የአክሲዮን ሽያጭ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።

የትግራይ ትምህርት ቢሮ በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ምደባ ላይ ወሰድኩ ያለው አስደማሚ አቋም

ከሰሞኑ አነጋጋሪ ክስተቶች ውስጥ የትግራይ ትምህርት ቢሮ አወጣ የተባለው መግለጫ ነው። በአስደማሚነቱ ብዙ ያነጋገረው ይህ መረጃ በ2012 የትምህርት ዘመን በፌዴራል ደረጃ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከተደረገው ምደባ ጋር ተያይዞ፤ በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡ 600 ተማሪዎችን የትግራይ ክልል አልክም ማለቱ ነው። የትግራይ ክልል ከዚህ ውሳኔ ደረሰ የተባለው ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃቶች በትግራይ ተወላጆች ላይ ይደርሳል በሚል ነው።

አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአማራ ክልል የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡት የትግራይ ተማሪዎች ቁጥር ሁለት ሺሕ የነበረ ሲሆን፣ ከመንግሥት ጋር በተደረገ ድርድር ወደ 1400 የሚሆኑት ወደተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው 600 መቅረታቸውን ነው። እነዚህ ተማሪዎች ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል የሚለው ጉዳይ ግን አሁንም ውይይት እየተደረገበት ነው ተብሏል።

የትግራይ ክልል 600 ተማሪዎች አማራ ክልል ውስጥ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳይሔዱ የወሰደው አቋም ግን በትግራይ ተወላጆች ሳይቀር ተቃውሞ የቀረበበት ሆኗል።

ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር በበኩሉ የትግራይ ክልል የወሰደው አቋም ተገቢ ባይሆንም፤ በጉዳዩ ላይ ከክልሉ አመራሮች ጋር ይነጋገራሉ ተብሏል።

ክልሉ 600 አዲስ ገቢዎችን አልክም የሚለው አቋሙ አነጋጋሪ የሚያደርገው ሌላው ገጽታው፤ ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚገኙ ነባር የትግራይ ክልል ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆኑ የሚታወቅ በመሆኑ ነው።

የክልሉ ዕርምጃ ከፌዴራል ዩኒቨርሲቲዎች አሠራር ያፈነገጠ በመሆኑ፤ ምን ዐይነት መፍትሔ እንደሚሰጠው ግራ ሊያጋባ ቢችልም፤ ሚንስትር መሥሪያ ቤቱ ውሳኔ ይሠጣል ተብሎ እየተጠበቀም ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በፌደራል መንግሥት የሚተዳደሩ እንደሆነ ይታወቃል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!