PM Abiy Ahmed and President Isaias Afwerki

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድና ፕ/ት ኢሳይያስ አፈወርቂ ሐምሌ ፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም. (July 15, 2018) በአዲስ አበባ ለሕዝብ ሰላምታ ሲሠጡ

“የአረንጓዴ ብቅ አለ። የተስፋ ጮራ ፈነጠቀ፣ እሾሁ ጠወለገ፣ ኢትዮጵያ ዐቢይን ይዛ ቦግ አለች” ፕ/ር መስፍን

ኢዛ (ማክሰኞ ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. October 22, 2019):- ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ክስተቶች ተስተናግደዋል። የዶክተር ዐቢይ አሕመድ የዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማት ከአገር አልፎ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ቀዳሚ ወሬ ሆኖ የተስተናገደበት ነበር። አሁንም ድረስ ወሬው በተለያየ መንገድ እየተተነተነና አስተያየቶች እየተሠጠበትም ይገኛል። ከዚሁ ጐን ለጐን የሚኒሊክ ቤተመንግሥት እድሳት ተጠናቅቆ ለሕዝብ ክፍት የሆነበት ሳምንት ነው። ይህም ብዙ አስተያየቶች ያስተናገደ ነበር።

በተለይ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ በየዕለቱ አደነቃቃፊ ችግሮች እየገጠማቸው ቢሆኑም፤ ይህንን በፅናት እንወጣለን ያሉበትን ንግግር ያሰሙት በዚሁ የታላቁ ቤተ መንግሥት የምረቃ ፕሮግራም ላይ ነበር። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ሥራውን የጀመረው ባሳለፍነው ሳምንት ሲሆን፤ የሰንደቅ ዓላማ ቀንም ተከብሯል።

የዶክተር ዐቢይ የኖቤል ሽልማት ማግኘት በተሰማ ማግሥት ራሱን የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት በማለት የሚንቀሳቀሰውና በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መሪነት የተቋቋመው ቡድን በአዲስ አበባ ከተማ ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. የጠራው ስብሰባ ፍቃድ ባለማግኘት፤ መቅረቱም ያሳለፍነውን ሳምንት ለየት ያለ የፖለቲካ ጡዘት የተስተናገደበት ነበር። “ከባላደራ ምክር ቤቱ” የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ጋር ተያይዞ ከዓባይ ወዲህ መንገድ መዘጋቱ እና ወደ አዲስ አበባ ይመጡ የነበሩ የሕዝብ ማመላለሻዎች የመታገድ ነገር ብዙ ያነጋገረ ጉዳይ ነበር።

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግብጽ ይዛ የመጣችው አዲስ አጀንዳ አሁንም ትኩስ ወሬ ሆኖ ቀጥሏል። በዚህ ጉዳይ እሰጥአገባው ቀጥሏል። በዚህ በግብጽ አዲስ አጀንዳ በኢትዮጵያ በኩል የተሠጠው የጠነከረ አቋም ከሳምንቱ አንኳር ዜናዎች አንዱ ነበር። በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል በተሠጡት ተከታታይ መረጃዎች፤ የግብጽ አዳዲስ ጥያቄዎች ሕዝብ እንዲያውቃቸው የተብራሩበትም ነበር።

ጉዳዩ ቀላል አለመሆኑን የሚያመለክተው ክንውን ደግሞ፤ ጥቅምት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሚንስትሮችና ሚንስትር ዴኤታዎች በወቅታዊው የህዳሴ ግድብ እና የግብጽ አቋም ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው መደረጉ ነው። ይህንንም ማብራሪያ የሰጡት የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሽ በቀለ ናቸው። ጉዳዩ የግብጽ ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ሞስኮ ላይ እንዲወያዩ ቀጠሮ ያስያዘ ጉዳይ ሆኗል።

ኢሕአዴግ ወደ ውሕድ ፓርቲ ለማሸጋገር እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴና ለአራት ቀናት የከተመው የሕወሓት ስብሰባ መቋጫ ምን ይሆን ተብሎ የተጠበቀው ባሳለፍነው ሳምንት ሲሆን፣ ከሕወሓት የወጣው መግለጫ ውሕደት አንሻም ሆኗል።

ከሰኔ 15ቱ ግድያ ጋር ተያይዞ እስር ላይ የነበሩ የአማራ ክልል ከፍተኛ የፀጥታና የደኅንነት ኃላፊዎች በዋስ የተለቀቁበት ሳምንት ነበር።

በአፋር ክልል በታጣዝቀዎች የተፈፀመ ጥቃት ሕይወት የጠፋበት ሲሆን፣ የጥቃቱ ሁኔታም በተለያዩ ወገኖች የተለያየ አስተያየት እየተሰጠበት ነው። ኢዜማ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ማውጣቱ፣ 70 ፓርቲዎች የረሃብ አድማቸውን ለአንድ ሳምንት ማራዘማቸው የመሳሰሉት ጉዳዮች ሲታዩ በሳምንቱ ውስጥ በርካታ ክንውኖች እንደነበሩ ያሳያል። ከእነዚህ ዐበይት ክንውኖች የተወሰኑትን እንደሚከተለው ይቀርባሉ።

ኖቤል ሽልማቱና አንደምታው

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ኖቤል ሽልማት ለጠቅላይ ሚንስትሩ ተበርክቷል። ይህ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም የመገናኛ ብዙኃን ቀዳሚ ዜና ሆኖ ለቀናት ዘልቋል። አገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ሰበር ዜና ሆኖም ተስተጋብቷል።

በርካታ የዓለም መንግሥታት ለጠቅላይ ሚንስትሩ የደስታ መግለጫ አስተላልፈዋል። በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች በተለይ በኦሮሚያ ክልል ደስታቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ገልፀዋል። ከሁሉም በተለየ ግን በዱባይ ታዋቂ ሕንፃዎች በኢትዮጵያ ባንዲራ ያሸበረቁበት ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ደስታቸውን በተለያዩ መንገዶች የገለጹበት አጋጣሚ ይለያል። የካቢኔ አባላት ሰብሰብ ብለው ለጠቅላይ ሚንስትሩ ስጦታ የተበረከተበት ነው።

ይህንን ሽልማት በተመለከተ የተለያዩ ታዋቂ ሰዎች አስተያየቶች የሰጡበት ሲሆን፣ አብዛኛው “ሰውዬው ይገባቸዋል!” የሚል ነው። ታዋቂው ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ሽልማቱን በተመለከተ በማኅበራዊ ገጽ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ “ኢትዮጵያና ዐቢይ” የሚል ርዕስ በመሥጠት ነበር አስተያየታቸውን የሠጡት።

“የገናና ጥንታዊ ታሪክ ባለቤት ኩራትና ክብርን የኑሮው መሠረትና መለያው አድርጐ የኖረ ሕዝብ፣ ቃር ቃር በሚል የባዕድ የአገዛዝ ፍልስፍና ለ50 ዓመታት ያህል በውርጋጦች ተገዛ። የታላቅ አገር ድንክዬዎች አገር ሆነ፣ ችጋር፣ ውርደት፣ ውድቀት፣ የሕዝቡ ማስታወቂያ ሆነ።

እግዚአብሔር የኢትዮጵያን ሕዝብ ፀሎት ሰማ፣ ዐቢይ አሕመድንና ለማ መገርሳን ኮርኩሮ ቀሰቀሰ፣ ቀስቅሶ አሠማራ፣ አሠማርቶ ከውጭም ከውስጥም አቀጣጠለ፣ ትንሳኤ አቆጠቆጠ፣ የአረንጓዴ ብቅ አለ። የተስፋ ጮራ ፈነጠቀ፣ እሾሁ ጠወለገ፣ ኢትዮጵያ ዐቢይን ይዛ ቦግ አለች። ጥያቄው ዓለም አቀፍ ሽልማቱ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያስከትል ይሆን ወይስ ለዐቢይ ዝና ምንጣፍ ይሆናል? ለማንኛውም ከዐቢይ ጋር በክብር ቆመን ስናጅበው ደስታ ይሰማናል፣ የሚተክዙ የኢትዮጵያ ፀበኞች ናቸው። ዶ/ር ዐቢይ ያበርታህ!” ሲሉ ፕ/ር መስፍን ያላቸውን ሐሳብ ገልፀዋል።

በኦሮሚያ ክልል በተደረጉ ሰላማዊ ሠልፎች ላይ ንግግር ካደረጉ ታዋቂ ፖለቲከኞች ውስጥ የቀድሞ የኦነግ አባላት በተለየ የሚታዩ ናቸው። አቶ ሌንጮ ለታና አቶ ዲማ ነገዎ በኦሮሚያ ክልል በሁለት ከተሞች ላይ በተደረገ ሰላማዊ ሠልፍ ላይ ተገኝተው ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድን የኖቤል ሽልማት በማወደስ ንግግር አድርገዋል።

ሌላኛው የቀድሞ የኦነግ አባል አቶ ሌንጮ ለታ ደግሞ “የዶክተር ዐቢይ የሰላም ኖቤል ሽልማት ማግኘት አንዱ ክፍል ሲደሰት አንዱ ክፍል አኩራፊ ነበር። ይሄ አኩራፊ ክፍል ኢትዮጵያን አንድነት የማይወድ ክፍል ነው። ሽልማቱ የዶክተር ዐቢይ ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ነው” ብለዋል አያይዘውም፤ ዶ/ር ዐቢይ ከዚህ በኋላ ብዙ ሥራ ይጠበቅበታልም በማለት አክለዋል።

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ደግሞ ከግራና ከቀኝ የሚወረወረውን እያሳለፉ ፀንቶ መሥራት ምን ዋጋ እንዳለው የዛሬው ሽልማት ይነግረናል፣ እዚህም እዚያም በሚከሰቱ ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች ሳይታወኩ ወደፊት እያዩ የአገርን ጥቅምና ታላቅነት በማስቀደም መሥራት ክብርና ሽልማት እንዳለው ያስተምረናል ብለዋል።

ከታዋቂ ሰዎች መካከል አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ “እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል። የሚያስደንቅ የዓለም አቀፍ ደረጃ የኖቤል ተሸላሚ መሆን አይደለም፤ መታጨት በራሱ ወርቃማ ገድል ነው። በዚህ ሽልማት አሸናፊው ዶ/ር ዐቢይ ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያ ናት።” በማለት፤ የሰላም ዋጋ ምን ያህል አስከባሪ እንደሆነም ጠቅሷል።

ለየት ባለ መንገድ ስለ ሽልማቱ አስተያየት የሰጡት ከመከላከያ ሚንስትሩ አቶ ለማ መገርሣ ናቸው። አቶ ለማ በኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስም ለጠቅላይ ሚንስትሩ ሽልማት ባበረከቱበት ወቅት የተናገሩት፡ “ለጠቅላይ ሚንስትሩ ዐቢይ አሕመድ የተበረከተው ሽልማት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል እውቅና የሰጠ ነው” በማለት ነበር፣ አያይዘውም አቶ ለማ “ኢትዮጵያ ከነበረችበት አንድ ደረጃ ከፍ ብላ ተቀባይነት ያገኘችበት ሽልማት ነው። የሽልማቱን እውቅና ማቆየት የሁላችንም ኃላፊነት ነው” በማለትም ሽልማቱን አወድሰዋል።

የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሙፍቲ ሐጂ እንድሪስ፤ “የጠቅላይ ሚንስትሩ የኖቤል ሽልማት የማያስደስተው እሳቸውን ብቻ አይደለም። መሸለማቸው የሚያስደስት ከአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለውን ኢትዮጵያዊ በሙሉ ነው። እሳቸው ከዚህም በላይ የሚገባቸው ሰው ናቸው። እየሠሩ ያሉት ሥራ ቢቆጠር እያንዳንዱ ሥራ የሚያሸልማቸው ነውም” ብለዋል። ሌሎች የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል።

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ደግሞ “በግልም ሆነ በአገር ደረጃ ደስ ይላል። ደስ የማይለው ሰው መኖር የለበትም። በጣም ጥሩ ነው። ደስ ብሎናል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ከአገራት ጋር ስለሰላም ትልቅ ሥራ ሠርተዋል። በአጠቃላይ በአፍሪካ ቀንድ የተጫወቱት ሚና ሽልማቱን የሚያስገኝና መስፈርቱን የሚያሟሉ ናቸው። በሠሩት ሥራ ሽልማቱን እንደሚያገኙ እጠብቅ ነበር” ያሉት ፕሮፌሰር በየነ፤ ለብዙ ዓመታት አይነኬና አጨቃጫቂ አከራካሪ የነበረውን ጉዳይ ኤርትራ ድረስ ሄደው ሁኔታዎችን ያረገቡትና ያደረጉት ነገር ቀላል ነገር አይደለም። በመሪ ደረጃ እንዲህ ያደረገ የለም ብለዋል።

ፕሮፌሰር በየነ አያይዘውም የኢትዮጵያውያን ትብብር ባይኖር ይህ ሽልማት አይገኝም ነበርም ብለዋል። ለዚህ ንግግራቸው ማሳያ አድርገው የገለፁት ምሳሌ ደግሞ ከኤርትራ ጋር የነበረውን ፍጥጫ ለማርገብ የተደረገውን ጥረት ሕዝብ ቢቃወም ሽልማቱ አይገኝም ነበር። ስለዚህ ሽልማቱ በኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ ጭምር የተገኘ በመሆኑ ሽልማቱ የሕዝብም ነው ብለዋል።

የሰላም ሚንስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ጠቅላይ ሚንስትር፣ ሽልማቱ በአገራችንና በቀጠናችን ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ማኅበራዊ መስተጋብር እንዲፈጥር ላበረከቱት አስተዋጽኦ እንደሆነ ከልብ ተረድተን በተሠማራንበት የሥራ ዘርፍ አሁን ከተገኘው የበለጠ ውጤታማ ክንውን ለመፈፀም በላቀ ዝግጅት ከጐንዎ እንደምንቆምና ያላሰለሰ ድጋፍም እንደምናደርግ ልገልጽልዎት እወዳለሁ ብለዋል።

የኖቤል ሽልማቱ እንደታወቀ ቀድሞ በግልና በሚመሩት ፓርቲ ስም የእንኳን ደስ ያለዎት የሚል መግለጫና አስተያየት የሰጡት ሌላው የፖለቲካ ሰው የኢዜማ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ናቸው። ፕሮፌሰሩ የጠቅላይ ሚንስትሩ የኖቤል ተሸላሚነት ያስደሰታቸውና የሚገባቸው ስለመሆኑ ጠቅሰው፤ እየሠሩ ላለው ሥራ እውቅና የሚሠጥ እንዲሁም በቀጣይ ብዙ ሥራ የሚጠብቃቸው ስለመሆኑም አክለዋል።

ፕሮፌሰሩ የሚመሩት ኢዜማ በበኩሉ “የ2019 የኖቤል ተሸላሚ በመሆንዎ እንኳን ደስ አለዎት። የኢትዮጵያ ዜጐች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አባላት እና ደጋፊዎች የተሰጠዎት እውቅና አገራችን ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሸጋገር በምናደርገው የጋራ ርብርብ ውስጥ ለሚጠብቅዎት ትልቅ ሥራ ጉልበት እንደሚሆንዎ ሙሉ እምነት አለን” የሚል መግለጫ አስነብቧል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም በጠቅላይ ሚንስትሩ የኖቤል ተሸላሚ መሆን ደስታቸውን ከገለፁ አንዱ ነበሩ።

ከኤርትራ ጋር ሰላም ለማምጣት ስለሠሩት ሥራ በማሸነፍዎ እንኳን ደስ አለዎት! በኢትዮጵያዊነቴም ኮራሁ! በማለት ዶ/ር ቴዎድሮስ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።

ከዚህ ሽልማት ጋር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊን ጨምሮ የተለያዩ አገራት የደስታ መግለጫ አስተላልፈዋል። የግብጽ ፕሬዝዳንት አልሲሲም የደስታ መግለጫ በመላክ ከቀዳሚዎቹ አንዱ ነበሩ። የክልል መንግሥታት በሽልማቱ ማግስት የእንኳን ደስ ያለዎት መልእክት አስተላልፈዋል። የድጋፍ ሰላማዊ ሠልፎችም እየተደረገ ነው።

ይህ የኖቤል ሽልማት አሁን እየተሠራ ያለው ሥራ ተስፋ ሰጪ መሆኑ ታይቶ የተሰጠ ሲሆን ቀጣይ ሥራዎች ላይ መትጋት የሚጠይቅም ነው። የብዙዎች አስተያየት መቋጫም ይኸው ነው። በተለይም ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የበዛ ሥራ ይጠብቃቸዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!