Ethiopia Zare's weekly news digest, week 15, 2012 Ethiopian calendar

ከታኅሣሥ 6 - 12 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ አሥራ አራተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከታኅሣሥ 6 - 12 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ የሳምንቱ ቀዳሚ ዜና በመኾን ሰፊ ሽፋን ከተሠጣቸው ዘገባዎች ውስጥ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሳተላይቷን ማምጠቋን የሚመለከት ነው። ዘገባውን ከአገር ውስጥ አልፎ የውጭ የዜና አውታሮች የዘገቡት ጉዳይ ኾኗል። ሌላው ተጠቃሽ ክስተት ደግሞ የቻይና ባለሥልጣናትንና ባለሀብቶችን የያዘ ቡድን ወደ ትግራይ እንዳይጓዙ ክልከላ ተደርጓል ተብሎ የክልሉ መንግሥት ክስ ማቅረቡ ነው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ተከስተ አብረሃ የሠጡት መግለጫ አነጋጋሪ በመኾን የሚጠቀስ ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ ግን ከፌዴራል መንግሥት የተሠጠ ምላሽ የለም። የምክትል ርዕሰ መስተዳድሩን አንደበት አነጋጋሪ ያደረገው በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል ሰፊ የሆነ ልዩነት ስለመፈጠሩ መግለጻቸው ነበር።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እየተስተዋለ ካለው “ክልል እንሁን” ጥያቄ አሁን ደግሞ በወላይታ ዞን እየተቀነቀነ ነው። ጥያቄያችን ይመለስ የሚሉ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሒደዋል። ይህ ጥያቄ በሰላማዊ ሠልፍ ከመገለጹ ባሻገር ለግጭት ምክንያት እስከመኾን መድረሱ ከሰሞናዊ ዜናዎች ውስጥ የሚካተት ነው።

ከኢትዮጵያ በተለያዩ መንገዶች የሸሸን ሀብት ወይም የተመዘበረ ሀብት ለማስመለስ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንቅስቃሴ እያደረገ መኾኑን ያስታወቀውም ባሳለፍነው ሳምንት ነው። ኢትዮጵያ በተለያዩ መንገዶች በርካታ ሀብቷ ተመዝብሮ ወደ ውጭ ሸሽተውባቸዋል ከሚባሉ አገሮች መካከል አንዷ መኾኗ በተደጋጋሚ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህን ወደ ውጭ የሸሸ ሀብት ለማስመለስ ጥረቶች እንደሚደረጉ፣ ለዚህም የተጀመሩ ሥራዎች ስለመኖራቸው ከዚህ ቀደም ተነግሯል። የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ እየሠራ ያለውን ሥራ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ የሠጠው በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት ነው።

በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የሚገኙት የቀድሞ የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው አዲስ በተመሠረተባቸው ክስ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሠጥተዋል። ጥፋተኛ ያለመኾናቸውንም የገለጹት ባሳለፍነው ሳምንት ፍ/ቤት በቀረቡበት ወቅት ነው። ሌላው የሳምንቱ ዜና የአዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ጉዳይ ነው። ሰሞነኛ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ በተለይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እስከ 400 በመቶ የሚደርስ ታክስ የሚጥል ነው። ረቂቁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ ሲሆን፣ ቀጣይ ውይይት ተደርጐበት ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። ነገር ግን ከአዋጁ መጽደቅ በፊት ከወዲሁ ያገለገሉ መኪኖች ዋጋ ጨመረ መባሉ አስገራሚ ሆኗል።

የሳምንቱ አሳዛኝ ዜና ደግሞ በአማራ ክልል በምሥራቅ ጐጃም ዞን ሞጣ ውስጥ በቤተ እምነቶች ላይ የደረሰ ጥቃት ነው። እንደ ቀደሙት ሳምንታት ሁሉ በዚህም ሳምንት የፋይናንስ ሪፖርት የአምስት ባንኮችን የ2011 በጀት ዓመት ክንውን የተመለከተ ዘገባ ቀርቧል። በዚህ ዘገባ ውስጥ ከ16ቱ የግል ባንኮች አንዱ የሆነው ወጋገን ባንክ ከሁሉም ባንኮች በተለየ የ2011 በጀት ዓመት ትርፉ መቀነሱ ትኩረት የሳበ ሆኗል።

ከወጋገን ባንክ ሌላ ሁሉም የአገሪቱ ባንኮች ዓመታዊ ትርፋቸውን ሲያሳድጉ ወጋገን ግን ባልተለመደ ሁኔታ ትርፉ ቀንሷል። በአጠቃላይ እንዲህ ያሉ ዘገባዎችንና አንኳን አንኳር ከኾኑት ውስጥ በተወሰኑ ወሬዎች ላይ የሚያተኩረው የሳምንቱ ቅኝት እንደሚከተለው ይቀርባል።

የሳተላይቷ ነገር

ታኅሣሥ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በታሪክ አንድ ሊታወስ የሚችል አገራዊ ተግባር የተፈጸመበት ሊባል የሚችል ቀን ኾኗል። ይህ ክስተት ኢትዮጵያ ምድር ቃኝ ሳተላይት ወደሕዋ ማስወንጨፏ እውን መኾን መቻሉ የተበሰረበት ዕለት ነው።

ታኅሣሥ 10 ቀን ማለዳ ላይ 12 ሰዓት ከ21 ደቂቃ ትወነጨፋለች የተባለችው ሳተላይት በአንድ ሰዓት ዘግይታ ከቤጂንግ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው የቻይና ሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አንግባ ወደ ሕዋ ተመነጠቀች። “ኢትዮጵያ ወደ ሕዋ ሳተላይት ላከች” የሚለው የሳምንቱ ርዕሰ ዜና በራሱ የኢትዮጵያውያንን ልብ የሞላ እንደነበር ስለክስተቱ በዕለቱ በተለያዩ ሚዲያዎች ሲሠጡ የነበሩ አስተያየቶች ይመሰክራሉ።

አዲስ ነገር ነውና የመጀመሪያዋን የኢትዮጵያ ሳተላይት ለማሰብ 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሶላታል። ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ስም የተመዘገበችው ETRSS-1 ሳተላይት ወደ 200 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የጠየቀችና ለአራት ዓመታት ሲለፋባት ነበር። ሳተላይቷ ስትተኮስ በቀጥታ የቴሌቪዥን መስኮት እንዲተላለፍ ተደርጐ ነበርና አዲስ አበባ እንጦጦ አናት ላይ ይቺን ሳተላይት ለመቆጣጠርና ከሕዋ የምትልካቸውን መረጃዎች በመቀበል ትንተኔ በመሥጠት ለሚፈልገው ዓላማ ለማዋል በተገነባው ማዕከል ተገኝተው ብስራቱን ለማሰማት በቦታው የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ነበሩ።

ከአዲስ አበባ እንጦጦ ጫፍ ላይ በወቅቱ የነበረውን ቀዝቃዛ የአየር ፀባይ ለመቋቋም የሚያስችል አልባሳት ደራርበው በተገኙ ታዳሚዎች የተሳካውን ጉዞ በጭብጨባ ሲገልጹ ታይተዋል። እንጦጦ ላይ የኢትዮጵያ ሳተላይት ስለመምጠቋ አቶ ደመቀ ሲገልጹ፣ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑካን ደግሞ ከቻይና የሳተላይት ማምጠቂያ ማዕከል ኾነው ሳተላይቷን ሸኝተዋል።

ከዚሁ ጐን ለጐን ዕለቱን ለማሰብ በመስቀል አደባባይ የተሰናዳ ልዩ የጥበብ ትዕይንትም ነበር። እንዲህ ባሉ ዝግጅቶች የታጀበችው ETRSS-1 ሳተላይት የምጥቀት ፕሮግራም በቀጥታ በቴሌቪዥን ይተላለፍ ነበርና ከሁሉም የአገሪቱ ክልሎች አስተያየቶችም ሲደመጡ ነበር። ይቺን ሳተላይት ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው አንፃር ሊኖራት ይገባል የሚለውን መስመር ለመያዝ አንድ ብላ የጀመረችበት ስለመኾኑ የሚያመላክቱ ከባህርዳር፣ ሐዋሳ፣ መቀሌ፣ ጅግጅጋና ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የተሠጡ አስተያየቶች እንኳንም ለዚህ በቃን የሚሉ ነበሩ። ከእንጣጦ ማዕከል ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ የዕለቱን ክስተት፣ “እኛ ኢትዮጵያውያን ጨለማን እየፈራን ብርሃን የምንናፍቅ ሕዝቦች እንዳልኾንን በተግባር የተረጋገጠበት ታሪካዊ እርምጃ ነው” በማለት ገልጸውለታል።

የዚህች ሳተላይት ወደ ሕዋ መላክ ተግባራዊ እንቅስቃሴው አራት ዓመት የፈጀ ነው ቢባልም፤ ግን ጥንስሱ ከአሥር ዓመታት ይሻገራል። ታሪካዊ አጋጣሚ ኾኖ የዚህ ጥንስስ ውስጥ የዛሬው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ አሻራ እንደነበረበት የበለጠ ማወቅ የተቻለው ሳተላይቷ በተመነጠቀች ዕለት አመሻሽ ላይ በአንድ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ስለሳተላይቷ የተናገሩት ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳተላይት ማምጠቅ ይኖርብናል በማለት ለካቢኔ ፕሮፖዛሉን ከ12 ዓመት በፊት ሲያቀርቡ የተመለሰላቸው ምላሽ ቀና እንዳልነበር፤ ከዚያ በኋላ ግን በራሳቸው መንገድ ሔደው አሁን ላለበት ደረጃ መደረሱን የሚያስታውስ ነው።

ኢትዮጵያ ይቺን ሳተላይት በመላኳ ምን ታገኛለች የሚለው ነገር በተለያዩ መልኮች ተገልጿል። በዋናነት ግን ግብርናን ለማዘመንና በእውቀት በመረጃ ላይ የተመሠረተ ሥራ ለመሥራት የሚያስችሉ መረጃዎችን በማቃለል እገዛ ታደርጋለች። የሳተላይቷ ስለምትሠጠው ጥቅም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌስቡክ ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት ላይ እስካሁን የእኛ የምንለው ሳተላይት ስላልነበረን የተለያዩ ምስሎች ከተለያዩ አገሮች በግዥ የምናገኝ ሲሆን፣ አሁን ግን በድንበር አካባቢ ያሉ እንቅስቃሴዎች፣ ትላልቅ ፕሮጀክቶች የምንከታተልበት፣ የአየር ፀባይ የምናይበት፣ የግብርና ሁኔታዎቻችንን የምናዘምንበት በቂ መረጃ የምንሰበስብበትና በመረጃ ላይ ተንተርሰን ሥራችንን እንድንሠራ ለውድድር የሚያበቃ መሠረት ኾና የምትገለገል ይኾናል ብለዋል።

ለኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ የኾነችው ሳተላይት ሌሎች ሳተላይቶችን ታስከትላለች ተብሏል። ሁለተኛዋን ሳተላይት ለተለየ አገልግሎት ለማምጠቅ ስለመታቀዱም ታውቋል።

በETRSS-1 ሳተላይት ጋር በተያያዘ በተለየ የሚታየው ነገር ሳተላይቷን ለመገንባት ከዲዛይን ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ እንዲያደርጉ መደረጉ ነው። ከቻይና ትምጠቅ እንጂ የሳተላይቷ ማዘዣ ጣቢያ አዲስ አበባ ላይ ነውና፤ ከመጠቀች በኋላ በዕለቱ መረጃ መሥጠት የጀመረችውን ሳተላይት ቀጣይ ሥራዎች ከአዲስ አበባ ኾነው የሚቆጣጠሩት ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያውያን የሚረከቡት መኾኑን ነው።

የዚህች ሳተላይት አብዛኛው ወጪ የተሸፈነው በቻይና መንግሥት ነው። ሳተላይት በማምጠቅ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ 10ኛዋ አገር ናት። ግብጽ፣ ሞሮኮና ደቡብ አፍሪካ ከአንድ እስከ አምስት ሳተላይቶች አምጥቀዋል። (ኢዛ)

የወጋገን ያለፈው ዓመት ትርፍ ከታሰበው በላይ ቀነሰ

የፋይናንስ ተቋማት ዓመታዊ ሪፖርታቸው የሚያቀርቡት ወቅት ነው። ከሰሞኑም የ2011 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸማቸውን ሪፖርት ካቀረቡ ባንኮች መካከል ዳሸን ባንክ ተጠቃሽ ነው። ባንኩ ከ16ቱ የግል ባንኮች ውስጥ ቀድመው ከተቋቋሙት 6ኛ ሲሆን፣ ከ23 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው ነው። በ2011 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 1.3 ቢሊዮን ብር ማትረፍ ችሏል። ከሪፖርቱ መረዳት እንደተቻለው ከታክስ በፊት ያስመዘገበው ትርፍ በ2010 አስመዝግቦት ከነበረው አንፃር 12 በመቶ ብልጫ ያለው መኾኑ ነው።

ባንኩ ከታክስ በፊት ያስመዘገበው ትርፍ ከግል ባንኮች ከአዋሽ ባንክ ቀጥሎ ከፍተኛ የሚባለውን ትርፍ ያስመዘገበ መኾኑን ያሳያል። ዳሸን ባንክ በ2011 በጀት ዓመት የሀብት መጠኑ 56.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል።

በአንድ ዓመት ውስጥ ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ ብድር የሠጠ ሲሆን፣ ይህም ከግል ባንኮች ከፍተኛ ብድር ከሠጡ ባንኮች መካከል አንዱ ያደርገዋል። ዳሸን ባንክ ከ2.2 ሚሊዮን በላይ በባንኩ አካውንት የከፈቱ ደንበኞች እንዳሉት ሪፖርቱ ያሳያል።

አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ደግሞ 2011 በጀት ዓመትን 695.5 ሚሊዮን ብር አትርፌበታለሁ ብሏል። በ2011 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ ከ2010 በጀት ዓመት ካገኘሁት በ45 በመቶ በልጦልኛል ብሏል።

በ2010 ከግብር በፊት አግኝቶ የነበረው ትርፍ 480 ሚሊዮን ብር ነበር። በባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት መሠረት በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የሀብት መጠኑ 20.4 ቢሊዮን ብር ደርሷል።

በ2011 ወደ 2.32 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱን ያመለከተው አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ፤ በባንኩ አካውንት የከፈቱ ደንበኞቹ ቁጥር 794,057 መድረሱን አስታውቋል። የተከፈለ ካፒታሉም 1.6 ቢሊዮን እንደደረሰለትም ገልጿል። በመላ አገሪቱ 229 ቅርንጫፎች ያሉት አንበሳ ባንክ 4,599 ሠራተኞች አሉት።

በ2011 የሒሳብ ዓመት ከግብር በፊት 767 ሚሊዮን ብር በማትረፍ በጀት ዓመቱን ያጠናቀቀ መኾኑን ያሳወቀው የኦሮሚያ የሕብረት ሥራ ባንክ ነው። የባንኩን ዓመታዊ ሥራ የሚያመላክተው ሪፖርቱ በበጀት ዓመት ከግብር በፊት ያስመዘገበው ትርፍ በ14 በመቶ የሚበልጥ ነው። በበጀት ዓመቱ በባንኩ ታሪክ ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ በአንድ ዓመት ማበደር መቻሉንም አስታውቋል። ከዚህም ሌላ የኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ ከ16ቱ የግል ባንኮች በአንደኛ ደረጃ ሊያስቀምጠው የሚችለው በባንኩ አካውንት የከፈቱ ደንበኞቹ ቁጥር 5.3 ሚሊዮን መድረሱ ነው።

አካውንት የከፈቱ ደንበኞቹን ለማሳደግ አድርጌያለሁ ባለው ጥረት፤ በአንድ ዓመት (በ2011) በጀት ዓመት ብቻ 1.3 ሚሊዮን ደንበኞች በማፍራት አጠቃላይ አካውንት ያላቸው ደንበኞችን 5.3 ሚሊዮን አድርሷል። ይህም ከግል ባንኮች ብዙ አካውንት በከፈቱ ደንበኞች አንደኛ አድርጐታል።

የኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ በአሁኑ ወቅት ያለው አጠቃላይ የሀብት መጠኑ 41.7 ቢሊዮን ደርሷል። ባንኩ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች 389 ቅርንጫፎች አሉት።

በ2011 በጀት ዓመት በአገሪቱ ካሉ 16ቱ ባንካች የተለየ አፈጻጸም የታየበት ባንክ ቢኖር ወጋገን ባንክ ነው። ጠንካራ ከሚባሉት የግል ባንኮች ውስጥ አንዱ የኾነው ወጋገን ባንክ በ2011 በጀት ዓመት የተለየ ያደገው ዐቢይ ጉዳይ፤ ከግብር በፊት ያገኘው የትርፍ መጠን ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ መቀነሱ ነው። በበጀት ዓመቱ ሁሉም ባንኮች የትርፍ መጠናቸውን በተለያዩ መጠኖች የጨመረ ቢኾንም ወጋገን ባንክ ግን የትርፍ መጠኑ ቀንሷል።

ባንኩ የ2011 በጀት ዓመት ሪፖርቱ እንደሚጠቁመው በ2011 በጀት ዓመት ከግብር በፊት ያተረፈው 735 ሚሊዮን ብር ነው። ይህ የባንኩ የትርፍ መጠን በ2010 አትርፎ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ከ30 በመቶ በላይ የቀነሰ ነው። በ2010 በጀት ዓመት አትርፎ የነበረው ትርፍ 1.05 ቢሊዮን ብር ነበር።

ባንኩ የትርፍ መጠኑ ከሌሎች ባንኮች በተለየ መቀነሱ የባንኩ ባለአክሲዮኖች ጥያቄ እንዲያቀርቡ ያስገደደ ነበር ተብሏል። ወጋገን ባንክ የ2011 በጀት ዓመት የትርፍ መጠን ቢቀንስም አጠቃላይ የሀብት መጠኑ 29.8 ቢሊዮን ብር ነው። በ2011 በጀት ዓመት የባንኩ አፈጻጸም ዝቅተኛ እንደነበር የሚያመለክተው የሠጠው የብድር መጠን 1.6 ቢሊዮን ብር ብቻ መኾኑ ነው። በ2010 ዓ.ም. ግን ሠጥቶት የነበረው የብድር መጠን ከ4.5 ቢሊዮን ብር በላይ ነበር። ስለዚህ የብድር መጠኑ መቀነሱን ያሳያል። ወጋገን ባንክ 361 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፣ የካፒታል መጠኑም 4.2 ቢሊዮን ብር ነው።

በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የግል ባንኮች በሙሉ ዓመታዊ ትርፋቸውን በተለያዩ መጠኖች ማሳደጋቸው እየተገለጠ ባለበት ወቅት ወጋገን ባንክ የትርፍ መጠኑ መቀነሱ የባንኩን ባለአክሲዮኖች ጥያቄ እንዲያነሱና ለምን እንዲህ ኾነ ብለው የባንኩን ቦርድ እስከ መሞገት የደረሱበት ኾኗል።

ቦርዱም ያጋጠመውን ችግር ቢገልጽም፤ ባለአክሲዮኖች ይህ ሁሉ ችግር የተፈጠረው ቦርዱና ማኔጅመንቱ ተናብበው ባለመሥራታቸው እንደኾነ በመግለጽ እርምት እንዲወሰድ ሁሉ ጠይቀዋል። (ኢዛ)

ፌዴራል መንግሥትና የትግራይ ክልል

ከአንድ ሳምንት በፊት ዋልታ በትግራይ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዙሪያ በፌስቡክ ገጹ ላይ ለደቂቃዎች አኑሮት የነበረው ዜና ብዙ የተባለበት ነበር። ዋልታ ከእኔ እውቅና ውጭ የተደረገ ነው ብሎ ለዚህም ይቅርታ ጠይቆበታል። ትግራይ ክልል ግን ኾን ብሎ የተደረገ መሆኑን ጠቅሶ፤ ወደ ሕግ እሔዳለሁ የሚለው አቋሙንም በማንጸባረቅ ጉዳዩ እንዲጦዝ ተደርጐ ሰንብቷል።

ከሰሞኑ እንደተሰማው ደግሞ ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ ሊኖሩበት ይችላሉ የተባሉ አራት ሠራተኞቹን ከሥራ ማገዱ ተሰምቷል። በዚህ ዙሪያ ያለው እሰጥ አገባ ቀዝቀዝ እንዳለ ሌላ አሟጋች የኾነ ክስተት ተፈጠረ። ይህም የዋልታ ጉዳይ ረገብ ብሎ ወደ አዲሱ ዜና ተሸጋገረ።

አዲሱና ሰሞነኛው ጉዳይ ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ ሲጓዙ በነበሩ የቻይና ዜጐች ክልከላ ጋር በተያያዘ ተፈጠረ የተባለው ነው። የቻይና ባለሀብቶችንና ባለሥልጣናትን የያዘ ቡድን ወደ ትግራይ እንዳይሔድ ተከልክሏል በሚል ከትግራይ ክልል የቀረበው ክስ ጉዳዩን ከፌዴራል መንግሥት ጋር አያይዞታል።

የቻይናውያኑን ቡድን ወደ ትግራይ ክልል እንዳይጓዝ ክልከላውን ያደረገው የፌዴራል መንግሥት አካል ማን እንደሆነ ባይገለጽም፤ ተደረገ የተባለውን የጉዞ ክልከለ ትግራይን በኢኮኖሚ የማዳከም አንድ ማሳያ እንደኾነ የክልሉ መንግሥት እስከ መግለጽ ደርሷል።

በዚሁ ጉዳይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሠጡት በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የክልል የንግድና ኢንቨስትመንተ ኃላፊ የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጋር ያለው ግንኙነት በጣም አሳሳቢ ወደ መኾን ደረጃ እየደረሰ መሆኑን ነው።

ዶ/ር አብረሃም አክለው እንደገለጹት የቻይናው ልዑክ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ከመጡባቸው ጉዳዮች አንዱ ከትግራይ ክልል ጋር በልማትና አቅም ግንባታ ዙሪያ ለመተባበር የሚያስችል ስምምነት ለመፈራረም ነው።

ለጉዞ አውሮፕላን ውስጥ ከገቡ በኋላ የሚናገሩት ዶ/ር አብረሃም ይህ ድርጊት በክልሉ ላይ ጫና ለማሳደር መኾኑን ስለመናገራቸው ይኸው ዘገባ ያስረዳል።

ኾኖም መቀሌ ያልተካሔደው ስምምነት ዶክተር አብረሃም ወደ አዲስ አበባ ወጥተው መፈራረማቸውን ይገልጻል። በዚህ ጉዳይ ላይ የፌዴራል መንግሥት ምንም ምላሽ አልሠጠም።

ቻይናውያኑ በትግራይ ክልል ሊያደርጉት የነበረውን ጉብኝት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚያውቀውና ዝግጅት ሲደረግበት የቆየ መኾኑን የትግራይ ክልል ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ይገልጻል። (ኢዛ)

የወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄ

የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያገኝ ከተደረገ በኋላ የወላይታ ዞን ቀጣይ ጥያቄ አቅራቢ ኾኗል። ሰሞኑንም የክልል እንሁን የሚለው ጥያቄ እንደ አዲስ ከፍ ብሎ መሰማት ጀምሯል። በሕጋዊ መንገድ ያቀረብነው ጥያቄ አንድ ዓመት ሞልቶታልና ሕጋዊ ምላሽ ይሠጠን በሚል ሰሞኑን በወላይታ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች ሰላማዊ ሰልፍ ተካሒዷል።

በተለይ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በከተማው መደበኛ እንቅስቃሴዎች መስተጓጐል ደርሶባቸው ነበር። የአገልግሎት መስጫዎችና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የማይታይባቸው አካባቢዎች ተፈጥረዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኹከት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት ያሳደረ ቢሆንም፤ ሁኔታው እንዲረጋጋ እየተደረገ ነው ተብሏል። ወላይታ ዞን ምክር ቤት በክልል ለመደራጀት የማያስችለውን ውሳኔ በማስተላለፍ ጥያቄውን ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ካቀረበ ታኅሣሥ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. አንድ ዓመቱን የያዘ ሲሆን፣ ሰሞኑንም እየታየ ያለው እንቅስቃሴ ጥያቄያችን ሳይመለስ አንድ ዓመት ሞላው በማለት ነው።

በሕገ መንግሥቱ መሠረት ጥያቄያችን ምላሽ እንዲያገኝ ብንጠይቅም፤ ምላሽ አልተገኘም በማለት የዞን ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባዔ በመጥራት፤ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ለጥያቄው በአሥር ቀናት ውስጥ ምላሽ እንዲሠጥ የሚጠይቅ ውሳኔ ማሳለፉም አይዘነጋም።

የደቡብ ክልል ለጥያቄው መልስ ስለሠጠ ጉዳዩን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን የወላይታ ዞን አስታውቋል። ምናልባትም ከዛሬ (ሰኞ ታኅሣሥ 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ) ባሉት ተከታታይ ቀናት ጥያቄውን ለፌዴሬሽኑ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። (ኢዛ)

የሀብት ሽሽት

በርካታ ሀብት ከአገር ሸሽቶባቸዋል ተብለው ከሚጠቀሱ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት። ባለፉት 27 ዓመታት ከኢትዮጵያ በተለያዩ መንገዶች ከአገር ሸሽቷል ተብሎ የሚገመተው ከ30 ቢልዮን ዶላር በላይ ነው።

ከአገር በተለያዩ መንገዶች የሸሸን ሀብት ለማስመለስ እንቅስቃሴ እየተደረገ መኾኑን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ። ባለፉት ዓመታት ከአገሪቱ በተለያየ መንገድ በርካታ ሀብት ተመዝብሮ ወደ ውጭ ሸሽቷል።

ሀብቱ ሊሸሽ የቻለውም በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በነበሩና ከእነሱ ጋር ጥብቅ ቁርኝት በነበራቸው ባለሀብቶች ትብብር እንደነበረ ይገለጻል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2011 ዓ.ም. የ11 ወራት የሥራ አፈጻጸምን ሪፖርትን ሲያቀርቡ የሸሸውን ሀብት ለማስመለስ ከተወሰኑ አገራት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል። እንዲሁም ከሌሎች አገራት ጋር ሀብቱን ለማስመለስ በጥንካሬ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው ነበር።

ሀብቱ የተደበቀው በእነማን እና የት እንደኾነ ታይቷል ያሉት በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሕዝብ ግንኙነት ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱሉ፣ በወንጀል የተገኘ ሀብትን የማስተዳደር ሥርዓት አለመኖሩ በሒደቱ ችግር መፍጠሩን አንስተዋል።

ዳይሬክተሩ አሁን ላይ ሀብት የማስመለስ ዳይሬክቶሬት መቋቋሙን በመግለጽ፣ በዚህ የተሳተፉ ወንጀለኞች በሕግ እንዲጠየቁ ማድረጉ በትኩረት እየተሠራበት ነው ብለዋል። ጉዳዩ ውስብስብና ጊዜ የሚጠይቅ መኾኑን ያነሱት አቶ ዝናቡ፣ የምርመራ ሒደቱ ሲጠናቀቅ በእነማን እና የት አገር ሀብት ሸሸ የሚለው ወደፊት ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም በአገሪቱ በወንጀልና በሙስና የተዘረፈን የአገርና የሕዝብ ሀብት የማስመለሱ ሥራ መጠናከሩን አቶ ዝናቡ ጠቁመዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!