Ethiopia Zare's weekly news digest, week 35rd, 2012 Ethiopian calendar

ከሚያዝያ 26 - ግንቦት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ ሠላሳ አምስተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከሚያዝያ 26 - ግንቦት 2 ቀን 2012 ዓ.ም.) ያሳለፍነው ሳምንት በዋና አገራዊ አጀንዳነት የሚጠቀሰው የምርጫ 2012 መራዘምና ይህንኑ ተከትሎ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችና ውሳኔዎች ናቸው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀጣዩን ምርጫ ለማካሔድ ያስችላል ብሎ ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ በሚሰጠው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ላይ ውሳኔ ማሳለፉም የዚሁ የሰሞነኛ አጀንዳ አካል ሲሆን፤ በዚህ ጉዳይ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሕግ ምሁራን እንዲሁም የተለያዩ ግለሰቦች በሰፊው አስተያየት የተሰጠበትም ኾኗል።

ይህ ብቻ ሳይሆን በቀጣዩ ምርጫ እና አጠቃላይ ወቅታዊውን የአገሪቱን ሁኔታ በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ መግለጫ ሰጥተዋል። በዚህ መግለጫቸው ከሕገ መንግሥቱ ወጪ በማድረጉ እንቅስቃሴዎች እርምጃ እንወስዳለን ብለው ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

በራሱ ክልል ምርጫ አደርጋለሁ ብሎ ውሳኔ የወሰነው ሕወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ያወጣው መግለጫ በሰፊው ያነጋገረ ሲሆን፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆኑ የሕግ ምሁራን ጭምር ይህ የሕወሓት አካሔድ ሕገ መንግሥታዊ ያለመኾኑን አጉልተው ሲናገሩ ሰንብተዋል።

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ምን መኾን አለበት ብለው የተለያዩ ፓርቲዎች የየራሳቸውን አቋም ያንጸባረቁ ሲሆን፤ በሳምንቱ ከተሰጡ መግለጫዎች መካከል አሁን መንግሥት የያዘውን የተቃወሙና የደገፉ የሚገኙበት ነው። የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ አስፈሪ ገጽታ እየያዘ ስለመምጣቱና ብዙ ተጠቂዎች የተገኙበት ሳምንት ቢኖር ይህ ያሳለፍነው ሳምንት ነው። የተጠቂዎቹ ቁጥር ወደ ባለሁለት አኀዝ ከፍ ያለ ሲሆን፣ አምስተኛ ሞትም ተመዝግቧል።

ከእነዚህ ዐበይት ዜናዎች ባሻገር የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ግብጽ ለተባበሩት መንግሥታት አቤት ያለችበትና ኢትዮጵያም አቋሟን በድጋሚ አንጸባርቃለች።

ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ ረዥም እጅ የነበራቸውና ቱባ ባለሥልጣን የነበሩት አቶ በረከትና ከእርሳቸው ጋር በሙስና ወንጀል የተከሰሱት አቶ ታደሰ ካሣ ፍርድ የተሰማውም በዚሁ ሳምንት ነው። ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የፌደራልና የክልል የመንግሥታት በግዴታ መተግበር አለባቸው ብሎ ያወጣውም መግለጫም ሌላው ተጠቃሽ ጉዳይ ነው። በኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ዝግጅት ክፍል የተጠናከሩት የሳምንቱ አንኳር ዜናዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል። መልካም ንባብ!

የምርጫ 2012 መራዘምንና ወቅታዊው ትኩሳት

ያሳለፍነው ሳምንት አገሪቷ ካስተናገደቻቸው አንኳር አንኳር ከሚባሉ አጀንዳዎች ውስጥ የምርጫ መራዘምን በተመለከተ የተቀሰቀሰው እሰጥ እገባ ነው። የኮሮና ቫይረስ በአገሪቱ መቀስቀሱ ከተሰማ ወዲህ፤ የተጋጋለ ምልልስ የተደረገበት የፖለቲካ ጉዳይ ቢኖር ይኸው ከምርጫ መራዘም ጋር እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችና ይህንንም ተከትሎ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚወረወሩ ሐሳቦችና መግለጫዎች የመገናኛ ብዙኀን ሰፊ ሽፋን እንዲሰጠው አድርገዋል።

የተለየ አመለካከት ያላቸው ወገኖች ምርጫው እንዲራዘም የተሰጠውን የውሳኔ ሐሳብ እንዴት ባለ ሁኔታ መስመር እናስይዘው በሚለው ላይ የተለያዩ አመለካከቶች የተንጸባረቁ ሲሆን፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ለመጀመሪያ ጊዜ ሕገ መንግሥቱ እንዲተረጐም ውሳኔ ያሳለፈበት ሳምንት ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ምርጫን በተያዘለት ጊዜ ሰሌዳ መሠረት ማካሔድ እንደማይችል በማስታወቁ የቀረቡ የመፍትሔ አማራጮችን ተመልክቶ ከቀረቡት አራት አማራጮች ውስጥ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ እንዲሰጥ መጠየቅ የሚለውን የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተስማምቶ አጽድቋል።

ከዚህ ውሳኔ ቀደም ብሎ በዚህ ጉዳይ ብዙዎችን እንደየስሜታቸውና አመለካከታቸው ብዙ አስተያየት ተሰጥቷል። በተለይ በኦኤምኤን ቴሌቪዥን ላይ የቀረቡትና ተጣምረው መቅረባቸውም እንዴት ኾነ የሚል ጥያቄ የተነሳበት የአቶ ልደቱ አያሌው እና የአቶ ጃዋር መሐመድ አስተያየት፤ አገሪቱ አሁን የገባችበትን የፖለቲካ ቀውስ ለመሻገር የሽግግር መንግሥት ያስፈልጋል የሚል ነው። አስተያየታቸውን ጫን ሲያደርጉም፤ “ከመስከረም 30 በኋላ ሁላችንም እኩል ነን” በማለት ሐሳባቸውን ገልጸዋል። መንግሥት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በዚሁ ጉዳይ ላይ ያደረገው ውይይት ጥድፊያ የታየበት ነበር በማለት ተችተዋል። ሕገ መንግሥቱን ለመተርጐም የሚያስችል ምንም ነገር ስለሌለ፤ የሽግግር መንግሥት መቋቋም አለበት፤ አለበለዚያ ከመስከረም 30 በኋላ አሁን ያለው መንግሥት ሕጋዊ አለመኾኑንም በመጥቀስ፤ ድምፃቸውን አሰምተዋል።

ከዚህ ውይይታቸው በኋላ ግን ሁለቱም ግለሰቦች ላይ ተቃውሞ ተሰምቷል። አይብዙ እንጂ ሐሳባቸውን ደግፈው ትክክል መኾናቸውንም የገለጹ አሉ። ነገሩን በሚዛናዊነት ያዩ አካላት ደግሞ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የጠቀሱዋቸው አንቀጾች ትክክል ቢኾኑም፤ ወቅቱን ያልጠበቀ አስተያየታቸውና ፍላጐታቸው አጋጣሚውን ተጠቅሞ ማተራመስ ነው በማለት ገልጸዋል። አቶ ጃዋርና አቶ ልደቱ በአቋማቸው ፀንተው ቢቀጥሉም፤ ምርጫው በዚህ ሰዓት መደረግ የለበትም የሚለውን አመለካከት ግን ብዙዎቹ የተስማሙበት መኾኑን መመልከት ይችላል።

የምርጫው መራዘም ሁሉን አቀፍ ተቀባይነት አለው ቢባልም፤ ሲራዘም የመንግሥት አስተዳደር እንዴት ይሁን የሚለው ላይ ግን ልዩነቶች አሉ። በተለይ የሽግግር መንግሥት ይመሥረት የሚለው እሳቤ ተቀባይነት ማግኘት የማይችል መኾኑን የሚያሳዩ አስተያየቶችም ጐልተው ወጥተዋል። አንዳንዶችም ይህንን ሐሳብ ያራመዱ የነበሩ ፓርቲዎች ሐሳባቸውን ቀይረዋል። በምርጫው ጉዳይ የተለያዩ አስተያየቶች ከተንሸራሸሩ በኋላ የመንግሥታቸውን አቋም ለማንጸባረቅና ቀጣዩን ምርጫ ለማድረግ ሕገ መንግሥታዊ ውሳኔ ለመወሰን የሚችለውን በግልጽ ያስቀመጡት ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፤ ከሕገ መንግሥቱ ውጭ የሚኾን የለም በማለት አቋማቸውን የገለጹ ሲሆን፤ መንግሥት ሕጋዊነትን ተከትሎ እየሠራ መኾኑን፣ እንዲሁም ከወቅታዊው ችግር አንፃር ውጤታማ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወቅታዊውን አገራዊ ጉዳይ በተመለከተ የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ፤ በመግለጫው ላይ አስተያየት ከሰጡት መካከል አንዱ ጃዋር መሐመድ ነው። አቶ ጃዋር አብዛኛው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በአብዛኛው የሽግግር መንግሥትን ሐሳብ በመተቸት ላይ ያተኮረ መኾኑን ገልጾ፤ አከራካሪው ጉዳይ ሕገ መንግሥቱ ስለምርጫ ማስተላለፍ እና ማራዘም ምንም ያለው ነገር ስለሌለ፤ ምርጫው እንዴት መተላለፍ እንዳለበትና አዲስ ምርጫ ማካሔድ እስኪቻል መንግሥት እንዴት መተዳደር እንዳለበት ድርድር እና ውይይት ያስፈልጋል ብሏል። እንደ መፍትሔ አንዳንድ ድርጅቶች የሽግግር መንግሥት፣ ሌሎች የባላደራ መንግሥትን ሲጠቅሱ ሰምተናል። አብዛኞቹ ግን እስካሁን በዚህ ላይ አቋማቸውን እንዳልገለጹ በመግለጽ ሁሉም ድርጅቶች በጋራ እየጠየቁ ያሉት የምክክር እና የድርድር መድረክ ይዘጋጅ ነው። እዛ መድረክ ላይ የድርጅታቸውን ፕሮፖዛል አቅርበው አስማሚ የኾነው መተግበር አለበት የሚለውን እምነት አንጸባርቋል። በመንግሥት ወገን ግን ሕገ መንግሥቱን ተከትሎ መደረግ አለበት ያለውን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስወስኖ ሕገ መንግሥቱ እንዲተረጐም ወስኗል። ይህንንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰፊው ያብራሩ ሲሆን፤ ከሕገ መንግሥቱ ውጭ የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ግን ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ በማስጠንቀቅ ጭምር አስታውቀዋል።

ከሰሞኑ በተከታታይ ከወጡ የፖለቲካ ድርጅቶች መግለጫና በተናጠልም የድርጅቶቹ መሪዎች ከሰጡዋቸው አስተያየቶች መገንዘብ የሚቻለው፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ የሚደግፍ መኾኑን ያሳያል። በዚህ ጉዳይ ላይ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን አስተያየት ከሰጡት መካከል፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም አንዱ ናቸው። ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ መጠየቅ የሚለውን ከአማራጮቹ መካከል የውሳኔ ሐሳብ አድርጎ ማጽደቁ ለተግባራዊነቱ አመቺ መኾኑን አስረድተዋል።

አቶ ሙሳ ሕግ ለመተርጎም የተቀመጡ አካሔዶች እንዲሁም የሚያልፋቸው የተለያዩ ደረጃዎች በመኖራቸው፤ ይህ አማራጭ እንዲተገበር መመረጡ ተገቢ መኾኑንም ያምናሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው ችግር እስኪያልፍ ድረስ እንደ ሕዝብና እንደ አገር መቀጠል እንዲቻል፤ ባለድርሻዎች የጋራ ሊኾን በሚችል መንገድ አስተዋጽኦ ማበርከት ይገባቸዋል ብለዋል። ለአገራዊ መግባባት ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበራትና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ከመንግሥት ጋር ውይይት ሊያደርጉ እንደሚገባም ከሰሞኑ ከሰጡት አስተያየት ለመረዳት ተችሏል።

“ፓርቲያቸው በዚህ ወቅት የፖለቲካ ጉዳይ አጀንዳችን አይደለም” የሚል አቋም እንዳለው የገለጹት የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አወሉ አብዲ፤ “አጀንዳችን ወረርሽኙን መከላከል ቀዳሚው ጉዳይ ነው። የሕዝብን ሕይወት መታደግ ነው። ከዚህ በኋላ ፖለቲካውን እንደርስበታለን። በዚህ ወቅት ስለምርጫ የሚያስብ አከል ካለ፤ ምርጫው የተራዘመበት አጀንዳ መዘንጋት ነው” ሲሉ አቶ አወሉ ይገልጻሉ።

መንግሥት የኮሮና ወረርሽኝ የሚያደርሰውን ጉዳት ከግምት በማስገባት ምርጫው እንዲራዘም ማደረጉ፤ ከሕግ አግባብ ውጭ እንደሠራ ተደርጎ ሊቆጠር እንደማይገባ ያመለከቱት አቶ ዛዲግ አብርሃ ናቸው። የዴሞክራሲ ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሚኒስትሩ አቶ ዛዲግ፤ ይህን አስቸጋሪ ወቅት አልፎ ምርጫ ለማካሔድ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ ተቀባይነት ያለው አሠራር ስለመኾኑ አስረድተዋል።

“ዘንድሮ ምርጫ እንዲካሔድ ፍላጎት ያላቸው ፓርቲዎች በሥልጣን ላይ ቢሆኑ ሊወስዱት የሚችሉት እርምጃ ነው የተወሰደው” በማለትም በመንግሥት የተወሰደውን እርምጃ አግባብ ስለመኾኑ ተናግረዋል። በዚህ ጊዜ ሕዝብ እየሞተ እኛ እንመረጥ ማለትም አግባብ ያለመኾኑንም ተናግረዋል። (ኢዛ)

የሕወሓት የምርጫ አዙሪትና ሕገ መንግሥታዊ ያልኾነው እንቅስቃሴ

ምርጫን መራዘሙን በተመለከተና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ ከማሳለፉ በፊትም ኾነ በኋላ፤ የተለየ አቋም ያራመደው የሕወሓት ሰሞናዊ ምልከታ በተለየ የታየና ሰሞናዊ መነጋገሪያ አጀንዳ ነበር። የኮሮና ቫይረስ ከመቀስቀሱም በፊት ቢሆን ምርጫው በተያዘለት ጊዜ የማይከናወን ከኾነ የትግራይ ክልል በራሱ ምርጫ በክልል ይደረጋል የሚል አመለካከቱን በተለያዩ መንገዶች ሲያንጸባርቅ ነበር።

በዚህ ሳምንት አጋማሽ ላይ ግን የሕወሓት ሥራ አስፈፃሚ ስብሰባ ተቀምጦ የደረሰበት ድምዳሜና ያወጣው የአቋም መግለጫው ውስጥ፤ ምርጫውን በክልል ደረጃ ለማድረግ ዝግጅት ይደረግ የሚል ውሳኔ ሥራ አስፈፃሚው እንደወሰነ በይፋ ገልጿል። በዚህ መግለጫው መንግሥት ምርጫውን ለማራዘም የፈለገው የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም ነው በማለት ሰፊ ማብራሪያ የሰጠበትን አመለካከቱን ያንጸባረቀ ነበር። ይህ ውሳኔው ወይም ሕገ መንግሥታዊ ያለመኾኑ የሚታወቅ ቢሆንም፤ ሕወሓት በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን አቋም በተለያየ መንገድ ሲገልጽ የሰነበተበት ሳምንት ነው።

የሕወሓት መግለጫን ተከትሎ የምርጫ ቦርድን ጨምሮ የተለያዩ ፓርቲ መሪዎችን የሕግ ምሁራን ጭምር እንዲሁም በትግራይ ክልልን መሠረት ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕወሓት እያራመደ ያለው አቋም ፈጽሞ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የሌለው ስለመኾኑ አሳውቋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ከሰጡት ውስጥ የምርጫ ቦርድ ሰብሰቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፤ ሕወሓት ያወጣውን መግለጫ መመልከታቸውንና ነገር ግን ለቦርዱ ይህንን የሚገልጽ ጥያቄ ያለመቅረቡን አስታውቋል። በአጭሩ ግን በኢትዮጵያ ምርጫን የማካሔድ ሕገ መንግሥቱ ሥልጣን የሰጠው ለምርጫ ቦርድ መኾኑን አስታውቀው፤ የሕወሓት አካሔድ ሕገ መንግሥታዊ ካለመኾኑም በላይ ሕገወጥ ድርጊት መኾኑን ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተውበታል።

የቦርዱ ሰብሳቢዋ የትግራይ ሕዝብ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንዳለው በማስታወስ፤ ሕወሓት ለትግራይ ሕዝብ እውቅና ከሚሰጡ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በመኾን ክልላዊ ምርጫን ለማካሔድ ዝግጅት እንዲደረግ ውሳኔ ቢያሳልፍም፤ ውሳኔው ተግባራዊ ቢኾን የክልሉ መንግሥትም ኾነ ክልሉን የሚያስተዳድረው ፓርቲ ሕጋዊ እንደማይኾን አሳውቀዋል።

ወይዘሪት ብርቱካን አክለውም “ክልላዊ ምርጫውን ለማካሔድ አስበው ከኾነ ትክክለኛ አካሔድ አይደለም። ሕገ መንግሥታዊ አይሆንም” ብለዋል። በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 መሠረት ምርጫ ቦርድ በፌዴራል፣ በክልል እና በቀበሌ ደረጃ የሚካሔዱ ምርጫዎችን የማስፈጸም ብቸኛ ሥልጣን የተሰጠው መኾኑን በማመልከት፤ የሕወሓት ውሳኔ ሕግን የተከተለ ስላለመኾኑ በመጥቀስ፤ እንዲህ ያለውን ተግባር እንደማይፈጽም ተስፋ እንዳላቸውም ጠቁመዋል።

“በራሴ ክልል ምርጫ አደርጋለሁ” የሚል ክልል ከሕገ መንግሥቱ አንፃር አግባብ መኾን አለመኾኑን ጥያቄ ቀርቦላቸው የነበሩት ታዋቂው የሕግ ምሁሩ አቶ ሙሉጌታ ጉዳዩን እንዲህ ተንትነዋል።

ክልሎች ይሄ ሕገ መንግሥት ሳይነካ ምንም ዐይነት ምርጫ ማድረግ አይችሉም። ይህም ሕገ መንግሥቱን ሳይዳፈሩ ወይም ሳይጋፉ ክልሎች የራሳቸውን ምርጫ ማድረግ አይችሉም።

ይህንን ጉዳይ ሲያብራሩም፤ ይሄ ሕገ መንግሥት የፌዴራል ሕገ መንግሥት ነው። የፌደራሉ ሕገ መንግሥት የተሠራው በክልሎች ነው። ዘጠኙም ክልሎች አንድ የፌደራል ሕገ መንግሥት ሠርተዋል። ስለዚህ የፌዴራል ሕገ መንግሥት ሠርተዋል። ስለዚህ የፌደራል ሕገ መንግሥት ባለቤቶች ክልሎች ናቸው። ስለዚህ ክልሎች በተናጠል የፌደራሉን ሕገ መንግሥት የሚፃረር ተግባር መፈፀም ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው ብለዋል።

በመኾኑም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውና በሕገ መንግሥቱ የሚታወቀው አንድ የምርጫ ቦርድ መኾኑን በማስታወስ፤ ከቦርዱ እውቅና ውጭ በክልል ደረጃ ምርጫ ማካሔድ የማይችል መኾኑ አስረድተዋል። በክልል ደረጃ ምርጫ ማድረግም ኾነ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ምርጫን ማካሔዱ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ያለው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ መኾኑንም ገልጸዋል። በክልል ደረጃ ምርጫን ለማካሔድ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ይጠይቃል ብለዋል።

የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔን በተመለከተ፤ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሰጡት አስተያየትም ተመሳሳይ ነበር ማለት ይቻላል። የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነብዩ ስሑል ሚካኤል በዚሁ ጉዳይ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ የሕወሓት ሥራ አስፈፃሚ ያወጣው መግለጫ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው ብለዋል። በአገሪቱ ምንም ዐይነት ምርጫ ማካሔድ የሚችለው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው። ሥልጣኑም የሱ ነው። ከዚህ ውጭ የሚደረግ ምርጫ እንደ ወንጀል የሚቆጠር ነው። ስለዚህ እንዲህ ካለው ሕገ መንግሥታዊ ጥሰት ሕወሓት እንዲቆጠብ በተለያየ መንገድ እያሳሰብን ነውም ብለዋል። አቶ ነብዩ አክለው እንዳመለከቱትም፤ “ይህ የማይታረም ከኾነ ሕግን ተከትሎ እርምጃ የሚወስድ ይሆናል” የሚል መልስ ሰጥተዋል።

የአረና ፓርቲን አቋም በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት አቶ አብረሃ ደስታ በበኩላቸው፤ ፓርቲያቸው ምርጫው መራዘሙን የሚደግፍ መኾኑን አስታውቀዋል። ምርጫው ጊዜው አሁን አይደለም ያሉት አቶ አብረሃ፤ የወረርሽኝ ሥጋት ባለበት ወቅት ምርጫ ማካሔድ የሕዝብን ደኅንነት ማጋለጥ ነው። ስለዚህ ምርጫ ከወረርሽኙ በኋላ በማለት፤ “በክልል ምርጫ ጉዳይ ያለን አቋም” በሚል ርዕስ ባሰፈሩት ጽሑፍ ላይ ገልጸዋል። (ኢዛ)

የምርጫው መራዘምና የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሰሞናዊ ምልከታ

በሰሞኑ የምርጫ መራዘምን በተመለከተ እስካሁን በተለያዩ ሚዲያዎች አስተያየታቸውን የሰጡ፣ በጉዳዩ ላይ መግለጫ ያወጡና አማራጭ ሐሳባቸውን ያሳወቁ አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች በምርጫው መራዘም ላይ ምንም ዐይነት ተቃውሞ አላቀረቡም። በምርጫው መራዘም እንዳለበት የሚስማሙ መኾናቸውን የሚያመለክቱ ናቸው። በምርጫው መራዘም ላይ የሚስማሙ ኾነው፤ ነገር ግን ምርጫው ሲራዘም የመንግሥት አስተዳደሩ ላይ ሊሆን ይገባል ብለው ያሉትና ለየት ያለ አቋማቸውንም የገለጹ አሉ።

በዚህ ሳምንት እንዲህ ያላቸውን አቋም ካንጸባረቁት ውስጥ ኢዜማ አንዱ ሲሆን፤ ከወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ምርጫው መራዘሙ ተገቢ መኾኑን ገልጾ፤ ምርጫው ሲራዘም አንድ ዓመት ያልበለጠ መኾን አለበት ብሏል። ኢዜማ በሰሞኑ መግለጫው ከሕግ አማራጭ ውጭ የፖለቲካ መፍትሔ ያለመኖሩን ጠቁሞ፤ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ አማራጭ የተሻለ ስለመኾኑ ገልጿል።

አሁን የገጠመንን አጣብቂኝ ለመሻገር የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ተግባራዊ የሚደረግ ከኾነ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተጨማሪ ክልል ምክር ቤቶችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶችም የሥልጣን ዘመን በሚያራዝም መልኩ መተግበር ይኖርበታልም የሚል እምነቱን በመግለጫው ላይ አንጸባርቋል።

የሽግግር መንግሥት ያስፈልጋል የሚል አመለካከት እንዳለው በተለያዩ መንገዶች ሲያንጸባርቅ የነበረው አብንም (የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄም)፤ ምርጫው ተገቢ መኾኑን ብቻ ሳይሆን፤ አሁን ባለው አገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውስ ለመውጣት እንዲሁም ፓርቲው የተቀመጠለትን ዓላማ ለማሳካት፣ በአገሪቱን መረጋጋትን ለማምጣት የሽግግር መንግሥት ይመሥረት የሚለውን አቋም የማይቀበለው መኾኑን አሳውቆ፤ እስከነችግሩም ቢኾን አሁን ሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ በኃላፊነቱ ላይ ቆይቶ የሽግግር ጊዜ ይሰጥ የሚለውን አቋሙን አሳውቋል።

በኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱ አራት ፓርቲዎችም በወቅታዊ ጉዳይ ላይ አቋማቸውን ገልጸዋል። በምርጫው መራዘምና የሕገ መንግሥት ትርጓሜውን በተመለከተ ከሰሞኑ መግለጫ ካወጡት የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የኦሮሞ አንድነት ነፃነት ግንባር (ኦአነግ)፣ የተባበሩት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ተኦነግ) እና የኦሮሞ ሓርነት ፓርቲ (ኦሓፓ) የተባሉት ፓርቲዎች ይገኙበታል።

ፓርቲዎቹ የአገሪቱ አንገብጋቢ ችግሮች ናቸው ያሏቸውን በጋራ በመምረጥና በመምከር መግለጫ አውጥተዋል። ፓርቲዎቹ ባወጡት የአቋም መግለጫ ላይ፤ “በኮሮና ምክንያት የሕዝባችን ጤንነት እና ሕይወት ለከፍተኛ አደጋ በተጋለጠበት፥ በህዳሴ ግድብ ውኃ ሙሌት ምክንያት የአገራችን ሉአላዊነት ሥጋት ላይባለበት እና በኮሮናና በሌሎች ምክንያቶች በኢኮኖሚያችን ላይ ከፍተኛ የድቀት አደጋ በተጋረጠበት በአሁኑ ወቅት ልዩነቶችን አቻችሎ በአንድነት መቆም ሲገባ፤ ትናንሽ አጀንዳዎችን በመፍጠር ሕዝቡ ራሱንና አገሩን ለማዳን እንዳይረባረብ ማድረግ ከክህደቶች ሁሉ በላይ ክህደት ነው” በማለት ያላቸውን አቋም አንጸባርቀዋል።

በኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም አግኝቶ፤ ዲሞክራሲያዊ መብቶቹ ተከብረውለት የፈለገውን ፓርቲ አውጥቶ አውርዶ አመዛዝኖ የተስማምውን መምረጥ የሚችልበት በር ስለመከፈቱ የሚገልጹት የትግራይ ትብብር ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሔ ደግሞ፤ ለውጡ ከመጣ ወዲህ ሐሳቦች በነፃነት ይንሸራሸራሉ፤ እንደ ወንጀለኞች፣ እንደ ከሐዲዎችና ባንዳ ስንታይ የነበርን የፖለቲካ ኃይሎች አገራችን ገብተን በሰላም ለመንቀሳቀስና የፈለግነውን ሐሳብ ለማንሸራሸር ችለናል። ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅ እርምጃ ነው ብለው፤ ይህንን የተከፈተ እድል እንዳይባክን ግን ተቋማዊ እንዲኾን ማድረግ ይገባናል ብለዋል።

አንዳንድ የፖለቲካ ቡድኖች ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ አዲስ ጊዜያዊና የሽግግር መንግሥት ይቋቋም የሚሉ መኖራቸውን በማስታወስም፤ ፓርቲዎች እንዲህ ያለ ሐሳብ ማንሳታቸው ግራ ያጋባል የሚል መግለጫ አውጥተዋል።

ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ሌላ ከብልጽግና ፓርቲ ውስጥ አካላትም ተመሳሳይ አቋማቸውን አንጸባርቀዋል። እስካሁን በምርጫው መራዘም ላይ የተለየ አቋም እያራመደ ካለው ሕወሓት ሌላ ባይቶና የተባለውና በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሰው ድርጅትም ምርጫው መራዘም የለበትም ብሏል።

ብሔራዊ ባይቶና አበይ ትግራይ (ባይቶና) የዘንድሮ ምርጫ መራዘሙን ተቃውሟል። ፓርቲው ምርጫው በኮሮና ወረርሽኝ ከማራዘም በጥንቃቄ ቢካሔድ የሚል አቋም ያለው ሲሆን፤ ምርጫውን ለማራዘም ከመንግሥት የቀረቡት የመፍትሔ ሐሳቦችም ምርጫውን ለማስረዘም ተብሎ የቀረቡ መኾኑን ገልጿል። (ኢዛ)

ኮሮናና አስደንጋጩ ሳምንት

መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በኢትዮጵያ ያሉ አብዛኛዎቹ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ያሠራጩት ዜና በየነበሩበት ቦታ ዜናውን ለሚከታተሉ ኢትዮጵያውያን እጅግ ያስደነገጠ፤ ወዲያውም የሰዎች እንቅስቃሴ የለወጠ ነበር። ይህ ዜና በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ የተገኘበት እንጂ ጃፓናዊ መገኘቱን የሚያመለክት ስለነበር ብዙዎች ተረበሹ። ኮሮና ኢትዮጵያ ገባ ተብሎ ሁሉም በየአቅጣጫው የመሰለውን በስሜት አደረገ። የአፍ መሸፈኛ ጭምብል 250 ብር ለመግዛት የደፈረ ብቅ ሲል፣ በተባለው ዋጋ እስከ መግዛት የተደረሰበት ዕለት ነበር።

በማግስቱም (መጋቢት 5 ቀን 2012 ዓ.ም.) በተመሳሳይ ሁኔታ የገበያ ቦታዎች በሰዎች ተጨናንቀው፣ የመደብር መደርደሪያዎች ጐድለው ያልተገባ ትርምስምስ ተፈጠረ፤ “ራሴን ላድን” በሚል ስሜት በዚያን ሰሞን የተፈጠረው ትርምስምስ ሰዎች ራሳቸውን ለመጠበቅ አስበው ነው ተብሎ በቅን ልቦና ቢታሰብም፤ ስግብግብነትም ነግሦ የሰነበተበት ነበር። ነገሩ አደጋ አለውና መንግሥት ዜጐች እንዲጠነቀቁ መከረ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ወጥተው እባካችሁ ራሳችሁን ጠብቁ፣ የጤና ባለሙያዎችን ስሙ አሉ። አደጋውን ለመከላከል በተከታታይ ውሳኔዎች ተወሰኑ፤ የተለያዩ ዝግጅቶችም መደረግ ጀመሩ። የአገር አጀንዳ ኮሮና ቫይረስ ኾነ። በመጀመሪያው ሰሞን የታየው ትምስምስ የግብይት ሥርዓትና ተያያዥ እንቅስቃሴዎች በሽታውን ለመሸመት የተመቻቸ በመኾኑም፤ ኧረ እንዲህ ካለው መዘናጋት ውጡ የሚለው ጩኸት ግን ብዙ አልተሰማም። ከቤት ተቀመጡ የሚለውን ወሳኝ መመሪያም ለመተግበር አስቸጋሪ ኾነ። ቤተእምነቶች ተዘጉል በቴሌቪዥን እግዚኦ እየተባለ ሳምንታት ተቆጠሩ፤ ይባስ ብሎ የትንሣኤ ዋዜማ ላይ የነበረው የግብይት ሒደት በኢትዮጵያ ምንም የተፈጠረ አይመስልም ነበር። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን፤ በየዕለቱ አንድ ሁለት ሦስት የሚኾኑ ሰዎች በበሽታው ተያዙ የሚለው ዜና ቀጥሏል።

አንድ ሰው ሞተ ሲባል ደግሞ የቀደመ ድንጋጤው በብዙዎች ዘንድ ቢኖርም፤ አሁንም ለቫይረሱ አጋላጭ እንቅስቃሴዎች አልቆሙም። ሁኔታው እንዲህ እያለ በመቀጠሉ መንግሥትም የአስቸኳይ ጊዜ አወጀ።

የሚመረመሩ ሰዎች ቁጥር እያደገ ሲመጣ በዕለት አንድና ሁለት በሽተኛ ተገኘ የሚለው ዜና ሰባትና ዘጠኝ መድረስ ጀመረ።

ባሳለፍነው ሳምንት ግን እጅግ በተለየ ሁኔታ በየዕለቱ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከአንድ አኀዝ ወደ ሁለት አኀዝ ተሻገረና። 17 ሰው ተገኘ የሚለው ዜና ቀዳሚ ነበር፤ ቀጥሎ 29 በአንድ ቀን መገኘቱ ተሰማ። ከዚያም ቀጠለ … ከዚያም 31 መድረሱ ተመለከተ፤ ይህ እስከ እሑድ ግንቦት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. የነበረ መረጃ የአገሪቱን በኮሮና ቫይረስ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ እንደሚሔድ ያሳየ ነው። ባለፈው ሳምንት ከሰኞ ሚያዝያ 26 ቀን እስከ እሁድ ግንቦት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ብቻ 117 አዳዲስ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ግለሰቦች መገኘታቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

የዚህን ሰሞኑን በተለየ አስደንጋጭ ያደገው የቁጥሩ ማደግ ብቻ ሳይሆን ተጠቂዎቹ ከለይቶ ማቆያ ውጭ ያሉ ሰዎች መኾናቸው ጭምር ነው። ዛሬ (ሰኞ ግንቦት 3 ቀን 2012 ዓ.ም.) ላይ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 250 ደርሷል። ተጠቂዎች የተገኙበት የአገሪቱ ክፍል ደግሞ ከአዲስ አበባ ውጭ በአራቱም አቅጣጫዎች መኾን ጉዳዩን የበለጠ አስፈሪ እያደረገው መጥቷል።

በሌላ በኩል የዜጐች ጥንቃቄ አሁንም ከወትሮ የተለየ ያለመኾኑና የተመርማሪዎች ቁጥር እየጨመረ ከሔደ ከዚህም በላይ ሊገኝ ይችላል የሚለውን ግምት ያሳድገዋል። ይህ ለኢትዮጵያ አደጋ ነው። እንደ መጽናኛ የምንወስደው ደግሞ እስካሁን ከተያዙት በሽተኞች ውስጥ 105 ያህሉ ማገገማቸው ነው። (ኢዛ)

ያገረሸው የግብጽ ጉዳይና የኢትዮጵያ ዝግጅት

ተደደራራቢ ፈተናዎች የተደቀኑባት ኢትዮጵያ ከሰሞኑ የምርጫ መራዘሙንና ከዚሁ ጋር ተያይዞ እሰጥ አገባው ጐልቶ በወጣበት ሰዓት፤ ግብጽም ብቅ ብላ ሌላ አጀንዳ የፈጠረችበት ሳምንት ኾኗል።

የኮሮና ወረርሽኝ ጋብ አድርጐት የነበረውን የታላቁ ህዳሴ ግድብና የግብጽ ተገለባባጭ አጀንዳዎችን መልሳ ለመንቀሳቀስ ከሰሞኑ ብቅ ብላለች። የሰሞኑ እንቅስቃሴ ደግሞ የተለመደውን ፍላጐትዋን ለማጉላትና የህዳሴ ግድብን ጉዳይ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ይዛ በመቅረብ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የውኃ ሙሌቱን እንዳይጀምር ለማሰነካከል ስለመኾኑም በግልጽ እየታየ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ግን በያዘው የጊዜ ሰሌዳ የውኃ ሙሌቱን እንደሚያካሒድና በአጭር ጊዜም ሁለት ተርባይኖቹን ለማንቀሳቀስ እየሠራ ሲሆን፤ ግብጽ አሁንም ጉዳዩን በጋራ ምክክር መደረጉ ብቻ እንዲታይ ማድረግ ይኖርባታል እንጂ የኢትዮጵያን ውሳኔ ማስቀየር እንደማትችል አሳውቋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ያለ አንዳች የጸጥታ ችግር እንዲካሔድ የምዕራብ ዕዝ ፈርጀ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ዕዙ አስታውቋል።

የዕዙ አዛዥ ጀኔራል ተስፋዬ ተመስገን በግድቡ አካባቢ ጸጥታን የማረጋገጥ ሥራዎች በመሥራት ላይ የሚገኙትን የሠራዊት አባላት በጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት፣ “የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንደ አገር ትልቅ ትኩረት የተሰጠው፤ ሕዝባችን ፍፃሜውን በከፍተኛ ትኩረት የሚከታተለውን ይህን ፕሮጀክት ሠራዊታችንም በንቃት እየጠበቀው ይገኛል” ብለዋል።

ማንም ኃይል የታላቁ ህዳሴ ግድብ የግንባታን ማስቆም እንደማይችል ጠቁመው፤ ሠራዊቱ በከፍተኛ እልህና ሞራል የተጣለበትን ኃላፊነት ከመወጣት ባሻገር ለሰባተኛ ጊዜ በወር ደምወዙ የቦንድ ግዥ መፈጸሙን እንደተናገሩ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። ከሰሞኑ ግለት ጋር በተያያዘ መንግሥት በተጠንቀቅ ስለመቆሙ አመላካች ተግባራት እየታዩ ነው። (ኢዛ)

አስገዳጁ አዋጅና የዓቃቤ ሕግ መግለጫ

ባሳለፍነው ሳምንት ከፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የወጣ አንድ መመሪያ ከክዋኔው እንደ አዲስ የሚታይ ነው። ይህም የፌዴራል መንግሥት አስፈፃሚ መሥሪያ ቤቶችና ለፌዴራል መንግሥት ተጠሪ የኾኑ የከተማ አስተዳደሮችን የሚያወጧቸውን ረቂቅ መመሪያዎች ከማጽደቃቸው በፊት የሕጋዊነት ጉዳዮችን ለማጣራት የሚመለከት ነው። በዓቃቤ ሕግ መግለጫ መሠረት፤ እነዚህ ተቋማት ማናቸውንም ረቂቅ መመሪያዎችን ከማጽደቃቸው በፊት ለፌዴራሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መላክ እንዳለባቸው የሚያስገድድ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ጸድቆ ተግባራዊ መኾኑን ያመለክታል።

በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መንግሥታዊ አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በኾነ መንገድ መከናወን እንዳለበትና ማናቸውም የመንግሥት ባለሥልጣን ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ የሚያደርግ እና በሰዎች መብቶችና ጥቅሞች ላይ የሚያስከትሉትን ጣልቃ ገብነት በሕግ ለመምራት፣ ተገዥ እና ተጠያቂ ማድረግ የሚያስችል አዋጅ መኾኑንም ገልጿል። “የፌዴራል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012” በሚል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ተግባራዊ ስለመኾኑ የሚያትተው የዓቃቤ ሕግ መግለጫ፤ የአስተዳደር ተቋማት በሕግ የተሰጣቸውን መመሪያ የማውጣት ውክልና ተግባራዊ ሲያደርጉ፣ ባለድርሻ አካላትንና ተገልጋዮችን በግል ማሳተፍ፣ በተዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ ላይ አስተያየት ለመሰብሰብና የውይይት ማካሔጃ በቂ ጊዜ መስጠት እንዳለባቸው በአስገዳጅ መስፈርትነት ግዴታ እንደሚጥልም ያሳያል።

“ማንኛውም በአስተዳደር ተቋም ረቂቅ መመሪያ ከማጽደቁ በፊት የሕጋዊነት ጉዳዮችን ለማጣራት ሲባል ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መላክ ይኖርበታል።” በማለትም ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በረቂቅ መመሪያው ያለውን አስተያየት አካትቶ በ15 ቀናት ውስጥ መመለስ የሚገባው ሲሆን፤ በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ካልመለሰ ግን ተቋሙ መመሪያውን ማጽደቅ እንደሚችል ስለመደንገጉ ያመለክታል።

በአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጁ መሠረት መመሪያው ከጸደቀ በኋላ ወዲያውኑ ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተልኮ መመዝገብና አለበት። እንዲሁም ተቋሙ በድረ-ገጹ ላይ እንዲጫንም አስገዳጅ ኾኖ በአዋጁ የጠቀሰ ሲሆን፤ ተቋሙ የተላከለትን መመሪያ ቁጥር ሰጥቶ መመዝገብ እና መመሪያው ስለመመዝገቡ ለአስተዳደር ተቋሙ ማሳወቅ እንዳለበትም አስታውቋል።

በዓቃቤ ሕግ መግለጫ መሠረት ማንኛውም የአስተዳደር ተቋም አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ሥራ ላይ የነበሩ መመሪያ አዋጅ ቁጥር 1183/2012 በወጣ በ90 ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በመላክ እንዲመዘገብ ማድረግ አለባቸው ብሏል። መመሪያው ተፈጻሚ መኾን የሚጀምረው በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ከተመዘገበበትና በተቋማቱ ድረ-ገጽ ከተጫነበት ቀን አንስቶ እንደኾነ ያመለክታል።

በመጨረሻም መመሪያው በረቂቅ ሕጉ የተቀመጡትን የመመሪያ አወጣጥ ድንጋጌ ሳይከተል ጸድቆ ሥራ ላይ የዋለ፣ በማናቸውም መንገድ ሕግን የሚጥስ ኾኖ ሲገኝ እና ውሳኔዎችን በተመለከተ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን የመመልከት ሥልጣንም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ብቻ እንደሚኾንና ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው ውሳኔም ይግባኝ የማይኖረው የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚኾንና፤ ነገር ግን የሕግ ስህተት በሚኖርበት ጊዜ ብቻ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እንደሚቀርብ በአዋጁ የተደነገገ መኾኑን ይኸው ሰሞነኛ የዓቃቤ ሕግ መግለጫ አመልክቷል። (ኢዛ)

ከለውጡ ወዲህ በቱባ ባለሥልጣን ላይ የተሰጠ ውሳኔና የእነ አቶ በረከት ፍርድ

ከሳምንቱ ዐበይት ዜናዎች መካከል፤ በኢሕአዴግና በፌዴራል ደረጃ ከፍተኛ ሥልጣን የነበራቸውና በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ሁነኛ ሚና እንደነበራቸው የሚጠቀሱት አቶ በረከት ስምኦንና ከእርሳቸው ጋር የተከሰሱት አቶ ታደሰ ካሣ ላይ ፍርድ መሰጠቱ ነው። የነአቶ በረከትን የክስ መዝገብ ሲመለከት የቆየው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እነአቶ በረከት ላይ በተከሰሱበት መዝገብ ብይን የሰጠው ሚያዚያ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ሲሆን፤ በዚህም ውሳኔ በአቶ በረከት ስምኦን ላይ ስድስት ዓመት እና በአቶ ታደሰ ካሳ ላይ የስምንት ዓመት የእስር ውሳኔ አስተላልፏል።

ከጥረት ኩባንያ ጋር በተያያዘ በኃላፊነት ላይ በነበሩበት ወቅት ሥራን በማያመች መንገድ ሥራ መምራት የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸው ክርክር ሲያካሒዱ መቆየቱ ይታወሳል።

ጉዳዩን የተመለከተው ችሎትም አቶ በረከትና አቶ ታደሰ በተከሰሱባቸው የክስ መዝገቦች ላይ ጥፋተኛ በመባላቸው ብያኔ ከተሰጠበት በኋላ፤ እነአቶ በረከት ቅጣት ማቅለያቸውን አቅርበዋል። የዓቃቤ ሕግን የቅጣት ማክበጃ ጨምሮ የተመለከተው ፍርድ ቤቱ መጨረሻ ላይ አቶ በረከት ስምኦን ላይ የስድስት ዓመት እስር እና የ10 ሺሕ ብር የቅጣት ውሳኔ ሲያስተላልፍ፤ አቶ ታደሰ ካሣ ላይ ደግሞ የስምንት ዓመት የእስር ቅጣትና የ15 ሺሕ ብር የቅጣት ውሳኔ ወስኗል።

እነ አቶ በረከት ይግባኝ የማለት መብትታቸው የተጠበቀ መኾኑን ፍርድ ቤቱ ያስታወቀ ሲሆን፤ አሁን ባለመረጃ ደግሞ የእነ አቶ በረከት ጠበቆች ይግባኛቸውን እንደሚያስገቡ ገልጸዋል። ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ሥልጣን ከተረከቡ ወዲህ ከሙስናና ከሰብዓዊ መብቶች ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ከሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት በፍርድ ቤት ጉዳያቸው ታይቶ ውሳኔ ከተሰጠባቸው ክሶች ውስጥ የመጀመሪያው የእነ አቶ በረከት ጉዳይ ሊኾን ችሏል። (ኢዛ)

የነኦፌኮ አቋም

ከወቅታዊው አገራዊ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የተለየ የአቋም መግለጫ ከነበራቸው ጥቂት የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ኦነግና ኦፌኮን ጨምሮ ስድስት የፖለቲካ ድርጅቶች ይገኙበታል። እነዚህ ተጨማሪ የፖለቲካ ድርጅቶች የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር፣ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ፣ የአገው ብሔራዊ ሸንጎ፣ የሞቻ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ አረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ፣ ከፋ አረንጓዴ ፓርቲ ሲሆኑ፤ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ላይ ከደረሱባቸው ነጥቦች ውስጥ ናቸው።

ከወቅታዊ ጉዳይ ጋር ከመንግሥት ጋር መደረግ አለበት ካለው የሚያምኑ መኾኑንና ይህም ውይይቱ እና ድርድሩ በምርጫ 2012 ለመወዳደር ተመዝግበው መስፈርት ያሟሉ የፖለቲካ ድርጅቶችንና ጥምረቶችን ብቻ ያሳተፈ መኾን አለበት የሚለው አንዱ ነው።

ውይይቱ እና ድርድሩ ገለልተኛ በኾነ አካል መመራት እንደሚኖርበት፣ በድርድሩ የሚደረሰው ስምምነት በሁሉም ወገን ተፈጻሚነት ያለው (binding) መኾን እንደሚገባው በመግለጫው ላይ ጠቅሰዋል።

አሁን አለ ያሉትን ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ ለመፍታት በመንግሥት የቀረቡትን አማራጮች በሚገባ መመርመራቸውን የገለጹት ፓርቲዎቹ፤ ምርጫው በሕገ መንግሥቱ በተሰጠው የጊዜ ገደብ መደረግ ባለመቻሉ እና መተላለፉን ተከትሎ የቀረቡት አማራጮች አንዳቸውም የመንግሥትን የሥራ ዘመን ለማራዘም የሚያስችል ሕገ መንግሥታዊ መከራከሪያ ማቅረብ እንዳልቻሉም ተገንዝበናል ብለዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ምርጫን ማስተላለፍም ኾነ የመንግሥትን የሥራ ጊዜ ማራዘም ሕገ መንግሥቱ አይፈቅድም። በተለይ ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል የመንግሥትን የሥልጣን ዘመን ማራዘምም ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የሌለው ከመኾኑም ባሻገር መደበኛ የምርጫ ጊዜ ለማራዘም የሚደረገው የሕግ ማሻሻል ሒደት ውስብስብ ሥራዎችን የሚጠይቅ፤ አለመግባባቶችን የሚፈጥር እና ሰፊ የሕዝብ ውይይት ሒደት የሚጠይቅ ነው የሚልም አቋማቸውን አሳውቀዋል። ይህንን ማድረግ ደግሞ አሁን ባለው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ፈጽሞ እንደማይኾን የገለጹት እኒሁ ፓርቲዎች፤ በተጨማሪም ከዚህ በፊት ፍትሐዊና ነፃ ምርጫ ባልነበረበት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ በአንድ ፓርቲ በተያዙ የፌዴራል እና የክልል ምክር ቤቶች ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል መሞከርም ኾነ በሕገ መንግሥቱ የሌለ አንቀጽ ለመተርጎም መንቀሳቀስ የሚፈጠረውን ክፍተት ፍትሐዊ እና ቅቡልነት ባለው መልኩ ለመሙላት የሚጠቅም ኾኖ አላገኘንም ብለዋል።

በአንድ ፓርቲ አባላት በተያዘ ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ ያልተካተተን ጉዳይ ተርጉሞ የመንግሥትን የሥራ ዘመን ማራዘም ቅቡልነትን የባሰ የሚሸረሽር እንጂ የሚያጠናክር አካሔድ ያለመኾኑን ያስገነዘቡት እኒሁ ፓርቲዎች፤ እንደ አራተኛ አማራጭ የቀረበው ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሐሳብም ቢሆን መፍትሔም ሊሆን አይችልም በማለት የተለየ አቋማቸውን አንጸባርቀዋል። ይህ የማይኾንበት ምክንያት ብለው የገለጹት ደግሞ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን ለመተርጎም ሥልጣን ቢኖረውም፤ በሕገ መንግሥቱ ሰፍረው ካሉት አንቀጾች ውስጥ ሥልጣን ማስተላለፍንም ኾነ ምርጫን ማራዘም በሚመለት ክርክር ያስነሱ አንቀጾች የሌሉ በመኾናቸው ነው ይላሉ። ምርጫን ማስተላለፍንም ኾነ የመንግሥት ሥልጣንን ማራዘም የሚመለከት አንቀጽ ፈጽሞ በሕገ መንግሥቱ ያልተካተቱ በመኾኑ፤ ምክር ቤቱ በሕገ መንግሥቱ ያልተካተቱ ጉዳዮችን መተርጎም እንደማይችልም በዚሁ መግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።

መፍትሔው በአንድ በኩል የኮሮና ቫይረስ አደጋን በጋራ እየተከላከልን እና በሌላ በኩል ለምርጫ እየተዘጋጀን ወረርሽኙ አልፎ ምርጫ እስክናካሒድ ድረስ የሚፈጠረውን የመንግሥት ሥልጣን ክፍተት ለመሙላት የሚረዳ አገራዊ የፖለቲካ ስምምነት ላይ መድረስ ብቻ ነውም ብለዋል። ያለው አንዱ የፖለቲካ አማራጭ የሽግግር ወቅት የፖለቲካ አደረጃጀት የሚያስፈልግ መኾኑ ቢታወቅም፤ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ይህን ማከናወን ቀላል እንደማይኾን የሚያምኑና ስለዚህ አሁን ያለውን መንግሥታዊ መዋቅር ተጠቅመን የዕለት ተዕለት የመንግሥት ሥራ ማከናወን አለበት ብለው የሚያምኑ መኾኑን ግን አመልክተዋል። የፖለቲካ መፍትሔ ነው ብለን የደረሱበትን በዝርዝር የሚገልጽ ሰነድ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና የሕግ አውጪው አካል ለማቅረብ እየተዘጋጁ መኾኑን ያከሉት ፓርቲዎቹ፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትም በመንግሥት በተገባው ቃል መሠረት የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ለማወያየት ዝግጁ ናቸው ብለው በተስፋ እየጠበቁ ስለመኾናቸው አሳውቀዋል።

ከዚህ ውጪ የሚወሰድ ማንኛውም እርምጃ ግን ፖለቲካዊ፣ ሕጋዊ እና ሕዝባዊ ተቀባይነት ስለሌለው፤ አገሪቱን ወደ ከፋ የፖለቲካ ቀውስና ብጥብጥ የሚወስድ ነው የሚል ሥጋት ያላቸው መኾኑንም ከሰሞኑ ባወጡት መግለጫ ገልጸዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!