Ethiopia Zare's weekly news digest, week 52nd, 2012 Ethiopian calendar

ከነኀሴ 25 - ጳጉሜን 1 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ ሃምሳ ሁለተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከነኀሴ 25 - ጳጉሜን 1 ቀን 2012 ዓ.ም.) ባሳለፍነው ሳምንት ዐበይት አገራዊ ጉዳይ ኾኖ የሚጠቀሰው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልል አደርገዋለሁ ያለው ምርጫ የማይጸና ስለመኾኑ የመጨረሻ ውሳኔ ማሳለፉ ነው። የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ሥልጠና መጠናቀቂያ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ሌብነት የብልጽግና ጉዞ ካንሰር መኾኑን የገለጹት በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት ነው። አንታገስም ማለታቸውን ያደመጥንበትም ሳምንት ነው።

የአዲሷ ከንቲባ ከመሬት ወረራ ጋር ተያይዞ የሰጡት ቃለምልልስ ከሳምንቱ ትኩረት ከተሰጣቸው ዜናዎች ተርታ የሚጠቀስ ነበር። የሳምንቱ መጠናቀቂያ የኮሮና ወረርሽኝ ስለመከላከል የወጣው አዋጅ ማጠናቀቂያ ነበርና አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደማይራዘምም እየተነገረ ነው።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድርን ለመግደል ሙከራ ያደረጉ ተጠርጣሪዎች ስለመያዛቸውም ከሳምንቱ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ነው። የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ኢንጂንየር ታከለ ኡማ የይቅርታ ቀን ተብሎ በተሰየመው ጳጉሜን 1 ቀን 2012 ይቅር እንባባል የሚል መልእክት ማስተላለፋቸው ትኩረት የሳበ ጉዳይ ነበር።

በሳምንቱ የፍርድ ቤት ውሎ አቶ ልደቱ አያሌው በሌላ መዝገብ ክስ የቀረበባቸው ሲሆን፣ የአብሮነት ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል በዋስ መፈታታቸው ታውቋል።

በኢትዮጵያ የኮሮና ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች አንድ ሚሊዮን መሻገሩ የተሰማበት ሳምንትም ነው። በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በጐርፍ አደጋ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጐች አደጋ ውስጥ እየገቡ ነው።

መንግሥት ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘ ሕወሓት እየተደረገ ያለውን ሕገወጥ ተግባር ለማስታገስ አልቻለም የሚሉ የተለያዩ ድምፆች ባሳለፍነውም ሳምንት ሲደመጡ ሰንብተዋል። የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ኪት በቀጣዩ ወር በኢትዮጵያ መመረት ይጀምራል። የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ያጠናከራቸውን የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች እነኾ!

የትግራይ ክልልና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል የሚደገው ምርጫ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ስለሚጥል እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና ተፈጻሚነት የሌለው መኾኑን የሚገልጸው ሰሞናዊ ዜና የሳምንቱ ዐበይት ዜና ተደርጐ የሚወሰድ ነው።

በሕገ መንግሥቱ መሠረት የምርጫ ሕግ ማውጣት፣ ለፌዴራል መንግሥቱ ምርጫውን ማስፈጸም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መኾኑን ለማሳወቅ ጭምር የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በማሳወቅ፤ የትግራይ ክልል ምርጫ የማድረግ ምንም ዐይነት የሕግ መሠረት የለውም ብሏል። በዚህም ምክንያት ምርጫው ሕጋዊ መሠረት የሌለውና መቆም እንደሚገባው የወልቃይት አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ፣ የራያ ራዩማ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የትግራይ ዴሞክራሲ ፓርቲ መጠየቃቸውን ጭምር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ በሰጠበት ስብሰባው ላይ አሳውቋል።

የትግራይ ክልል የምርጫ ሒደት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ያልጠበቀ፣ በነፃነት ለመወዳደር የማያስችል መኾኑ ከትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የቀረበውን ጥያቄ አይቷል ብለዋል። ቋሚ ኮሚቴው የትግራይ ክልል በምርጫ ቦርድ ሥልጣን ጣልቃ በመግባትና ሕገ መንግሥቱን በመቃረን በሚያደርገው ምርጫ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ምክር ቤቱ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጠይቋል።

በትግራይ ክልል የሚደረገው ምርጫ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ እንደሚጥል ገልጸው፣ ምርጫው እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና ተፈፃሚነት እንደሌለው ምክር ቤቱ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት በተጠየቀው መሠረት፤ በትግራይ ክልል የሚደረገው ምርጫ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ እንደሚጥል ገልጸው፤ ምርጫው እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና ተፈጻሚነት እንደሌለው የመጨረሻ ውሳኔው አሳልፈል።

ይህንን ውሳኔ የትግራይ ክልል የተቃወመው ሲሆን፤ በክልሉ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ በኩል በተሰጠው መግለጫ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከተሰጠው ሥልጣን ውጭ እየሠራ መኾኑን አመልክተዋል። ከፌዴሬሽኑ ስብሰባ ቀደም ብሎ የክልሉ ምክር ቤት በትግራይ ክልል ሊካሔድ የታሰበው ምርጫን ለማደናቀፍ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ማንኛውንም ውሳኔ ቢያሳልፍ ጦርነት እንደማወጅ እንቆጥረዋለን እስከማለት መድረሱ ይታወሳል። (ኢዛ)

የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ሥልጠና ወሰዱ፤ ዶ/ር ዐቢይ ንግግር አድርገዋል

የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ሥልጠና ላይ ነበሩ። በተጠናቀቀው ሳምንት የሥልጠናው መዝጊያ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ “ሌብነት የብልጽግና ጉዞ ካንሰር ነው” በማለት ተናግረዋል።

የሕዝብ መሪ የኾኑት ከፍተኛ አመራሮች ከፍ ያለ ሕልምና ራዕይ ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል። የትልቅ ሥራና ትልቅ አገር ለመገንባት መነሻቸው ትልቅ ነገር የመሥራት ሕልምና ራእይ መኾኑን በመናገር የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግም አመራሮች ከፍ ያለ ራእይ ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል። የተበላሹ ነገሮችን ለማረምም የአመራር አንድነትና ከብልሽቱ ጸድቶ መገኘት ወሳኝ መኾኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሌብነት ደግሞ የብልጽግና ጉዞ ካንሰር ስለመኾኑና አመራሩ ከብልጽግና ጋር ለመሔድ ከሌብነት ጋር መቆራረጥ አለበት ሲሉ አመልክተዋል። (ኢዛ)

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የጊዜ ገደብ አብቅቷል፤ አይራዘምም እየተባለ ነው

የኮሮና ወረርሽኝ ሥርጭትን ለመከላከል የወጣው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊራዘም እንደማይችል የተገለጸው በዚሁ ሳምንት ነበር። ይህ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጋቢት 30 ወጥቶ ነሐሴ 30 ያበቃል ተብሎ የተደነገገ ነበር። ኾኖም እስካሁን አዋጁን ለማራዘም ጥያቄ ያልቀረበ በመኾኑ፤ በዚህ አዋጅ ድንጋጌ ሥር የነበሩ አስገዳጅ ሁኔታዎች ማብቃታቸውን የሚያመለክት ኾኗል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማራዘም አስፈላጊ እንዳልኾነ የታመነበት ስለኾነም፤ በአማራጭነት በሥራ ላይ ያሉ ነባር አዋጆችንና እነዚህን መሠረት ያደጉ አዳዲስ ደንቦችንና መመሪያዎችን በማውጣት የቫይረሱን የመከላከል ሥራ ይሠራል ተብሎ ይጠበቃል። (ኢዛ)

ርዕሰ መስተዳድሩን ለመግደል የሞከሩ ተያዙ

በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ከተነገሩ ዜናዎች ውስጥ ነኀሴ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድሩን ለመግደል የሞከሩ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን የሚመለከተው ነው።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እንዳስታወቀው የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድርናንና ሌሎች የክልሉ ባለሥልጣናት ሊገድሉ ሙከራ አድርገዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ነው። ተጠርጣሪዎቹ ባለሥልጣናቱን ሊገድሉ የሞከሩት ነኀሴ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በስብሰባ ላይ እያሉ መኾኑንም የክልሉ የፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

ከዚህ የግድያ በሙከራ ጋር ተያይዞ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው 26 ተጠርጣሪዎች ናቸው። ከግድያው ሙከራ ጀርባ በአሜሪካ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች እጅ እንዳለበት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የክልሉ ምክትል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ቱት ኮር ገልጸዋል። (ኢዛ)

ኢንጂንየር ታከለ ኡማ የይቅርታ ቀን ይቅርታ ጠየቁ

በቅርቡ በአዲስ አበባ መሬት ወረራ ሕግን ባልተከተለ መልኩ የኮንዶሚኒየም ቤቶች እደላ ዙሪያ ኢዜማ ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ ስማቸው እየተነሳ ያለው የቀድሞ ከንቲባ ኢንጂንየር ታከለ ኡማ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ያስተላለፉት መልእክት የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ነበር ማለት ይቻላል።

ኢንጂንየር ታከለ ኡማ በፌስ ቡክ ገጻቸው ያሰፈሩት መልእክት አንደምታው “ይቅርታ” ወይም “ይቅር በሉኝ” የሚል፤ ይህንንም “የኢትዮጵያውያን ሁሉ መዲና የኾነችውን ታላቅ ከተማ የማስተዳደርን እድል ላለፉት ሁለት ዓመታት በማግኘት ለማገልገል በመቻሌ ትልቅ ክብር ይሰማኛል።” በማለት ጀምረው፤ “ከተማዋን በማስተዳደር ኃላፊነቴ ወቅት እንዲሁም እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ባለማወቅ ለበደልኩት ለማንኛውም በደል ይቅርታን በትሕትና እጠይቃለሁ።” በማለት ገልጸዋል። በዚሁ መልእክታቸው ላይ ወደዚህ ኃላፊነት አከራካሪ በኾነ መንገድ ብመጣም፣ በወሬ ሳይሆን በሥራ፣ በብሔር ሳይሆን በኢትዮጵያዊነት የሚያምነው መልካምና ሰው ወዳድ ሕዝብ ጋር በፍቅር አብሮኝ ስለሠራና ስላሠራኝ ምስጋናዬ ሁልጊዜም ከፍ ያለ ነው በማለትም አስፍረዋል።

አሁን በሥራ ላይ ያለው በእኅቴ በወ/ሮ አዳነች አቤቤ የሚመራው አስተዳደር የዛሬውን ቀን “የይቅርታ ቀን” ብሎ በሰየመው መሠረት፣ እኔም እንደከተማው ነዋሪና የቀድሞ አገልጋያችሁ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሜ ይቅርታ ይሁንልን በማለት የይቅርታ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

“እኔንም ለበደሉኝ፣ ያለበደሌ ለከሰሱኝ፣ ያለ ተግባሬ መጥፎን ስም ሰጥተው ላሳጡኝ፤ ሕዝብን ለማገልገል በምተጋበት ወቅት አላስፈላጊ ጦርነትን በመክፈት ሲያደክሙኝና አላሠራ ሲሉኝ ለነበሩት ሁሉ ከልብ የኾነ ይቅርታን አድርጌያለሁ።” ያሉ ሲሆን፤ አክለውም አዲሱ ዓመት የምሕረት፣ የፍቅርና የአንድነት ዓመት ይሁንልን። ከስሕተታችን የምንታረምበት፣ ካለፈው ተምረን የወደፊታችንን የምናሳምርበት ይኾን ዘንድ ተመኝተዋል። (ኢዛ)

የአቶ ልደቱ ጉዳይ

ኹከት በማነሳሳት፣ በመምራትና በገንዘብ መደገፍ ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ልደቱ አያሌው፤ “ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ” ሞከረዋል በሚል አዲስ ውንጀላ እንደቀረበባቸው የሚገልጸው ዜና ከሳምንቱ ፍ/ቤት ውሎዎች መካከል አንዱ ነበር።

በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የቢሾፍቱ ወረዳ ፍርድ ቤት አቶ ልደቱ አያሌው በተጠረጠሩበት ወንጀል ፖሊስ ያቀረበውን የተጨማሪ ጊዜ ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የፖሊስን ጥያቄ የሕግ አግባብነት እንደሌለው ጠቅሶ እንደማይቀበለውና የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው እንደገና ማመልከቻ ያስገቡ የሚል ትእዛዝ ቢተላልፍም፤ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ግን በሌላ ፋይል ፍ/ቤት እንዲቀርቡ ተደርጓል። በአዲሱ መዝገብ ፍ/ቤት የቀረቡት አቶ ልደቱ የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ ኾኖ የ15 ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተመልሰዋል።

በአቶ ልደቱ ወቅታዊ የፍ/ቤት ጉዳይ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራሮች “አሁን ባለው ሒደት መፍትሔ ማግኘት እንደማይቻል ተማምነን፤ አካልን ነፃ የማውጣት ክስ ለመመስረት ወስነናል” በማለት ገልጸዋል። የፓርቲው ፕሬዝዳንት ለቢቢሲ እንደገለጹት ደግሞ፤ “አስፈጻሚው ከሕግ አውጪው በላይ ጡንቻ አለው ብለን ስለምናምን፤ ሰኞ አዲስ አበባ ላይ አካልን ነፃ የማውጣት ክስ እንመሠርታለን” ብለዋል። (ኢዛ)

ፌዴራል መንግሥቱ በሕወሓት ላይ ከመጠን ያለፈ ትዕግሥት አድርጓል ተባለ

ሕወሓት እየፈጸማቸው ነው የተባሉ ሕገወጥ ተግባራትን እየጠቀሱ አስተያየቶች የሚሰጡ አባላት በርክተዋል። ባሳለፍነው ሳምንትም ያገባናል ያሉ የክልሉ ተወላጆች በመንግሥት የመገናኛ ብዙኀን እየቀረቡ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል። በዚህ አስተያየታቸው የፌዴራል መንግሥት በሕወሓት ላይ እያሳየ ያለው ከመጠን ያለፈ ትዕግሥት እንዲያበቃ የሕግ የበላይነት ማስከበር እንዳለበት እየጠየቁ ነው።

መንግሥት በሕወሓት ላይ እያሳየ ያለው ከመጠን ያለፈ ትዕግሥትም ለትግራይ ሕዝብ ያለውን ክብር ያሳየ መኾኑን የሚገልጹት አስተያየት ሰጪዎች ሕወሓት በትግራይ ክልል ሊያካሒድ ያሰበው ምርጫ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ መኾኑንም አመልክተዋል።

በመላው ዓለም በርካታ አገራት ሊያካሒዱት የነበረውን ምርጫ በኮሮና ሥጋት እንዲራዘም ማድረጋቸውንም በመጥቀስ፤ ይሁን እንጂ ሕወሓት በትግራይ ክልል አካሒደዋለሁ የሚለው ምርጫ የኮሮና ወረርሽኝ ሥርጭትን ያላገናዘበና ሕገወጥ ነው በማለት የሕወሓትን አካሔድ ኮንነዋል።

ሕወሓት በትግራይ ክልል የምርጫ ኮሚሽን የማቋቋምና ምርጫ የማካሔድ ሥልጣን እንደሌለው በማንሳት፤ በግልጽ የሕገ መንግሥት ጥሰት እየተፈጸመ ስለመኾኑ ጭምር የተናገሩት ተወላጆቹ፤ የፌዴራል መንግሥት እስካሁን በሕወሓት ላይ ያሳየው ትዕግሥት ለትግራይ ሕዝብ ያለውን ክብር የሚያሳይ ቢኾንም በቀጣይ ሕግን ማስከበር እንዳለበትም አስገንዝበዋል። (ኢዛ)

የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ኪት ከአንድ ወር በኋላ መመረት ይጀምራል

በኢትዮጵያ እየሰፋ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ምርመራ ለማስፋት ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ኪት ከአንድ ወር በኋላ ማምረት እንደሚጀመር በይፋ አስታውቃለች።

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ እንደገለጹት፤ ኮሮና ቫይረስን የመመርመር አቅምን ከፍ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩና በአሁኑ ወቅትም ከአንድ ወር በኋላ ከቻይና መንግሥት ጋር በመተባበር የመመርመሪያ ኪት ለማምረት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑንም አስታውቀዋል።

የመመርመሪያ ኪቱን በአገር ውስጥ ማምረት ሲጀመር ከውጭ የሚገባውን ኪት ሙሉ በሙሉ እንደሚያስቀርም ተነግሯል።

በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ 52 የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ማዕከላት የተቋቋሙ ሲሆን፤ እነዚህ ማዕከላት በቀን ከ20 ሺሕ በላይ ናሙናዎችን መመርመር አቅም ያላቸው ናቸው ተብሏል። (ኢዛ)

ሰባተኛው የኃይሌ ሪዞርት በአዳማ ተመርቆ ሥራ ጀመረ

በሆቴልና ሪዞርቶች ኢንቨስትመንት ላይ በመንቀሳቀስ መዳረሻዎቹን እያሳደገ የመጣው የታዋቂው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ድርጅት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ በአዳማ ከተማ ያስገነባውን ሰባተኛውን የኃይሌ ሪዞርት አስመርቆ ሥራ ያስጀመረው ባሳለፍነው ሳምንት ነበር።

የአዳማው ሪዞርት የመመገቢያና የስብሰባ አዳራሾች ጨምሮ 106 የእንግዳ ማረፊያ ክፍሎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ የመዋኛ ገንዳዎች እና ሌሎችንም መሠረተ ልማቶችን ያካተተ ስለመኾኑ በሪዞርቱ ዙሪያ የተሰጠው መረጃ ያመለክታል።

ሪዞርቱ ባለ 4 እና 5 ኮከብ ደረጃን የሚያሟሉ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሲሆን፤ ይህንን ሪዞርት ግንባታውን ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመታትን ፈጅቷል። ሪዞርቱ 300 ለሚኾኑ ዜጎችም የሥራ እድል መፍጠሩ ተነግሯል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!