ዲበኩሉ ቤተማርያም

Kinfu, Teddy and Teborne
ክንፉ አሰፋ፣ ቴዲ አፍሮ እና ተወልደ (ተቦርነ) በየነ

ምሳሌያዊ አነጋገሮች፣ ተረቶች፣ የታላላቅ ሰዎች አባባሎች መጻሕፍትና ገጠመኞች እየተጠቀሱ ንግግር መክፈቻም ሆነ የጽሁፍ መነሻ መሆን በፊትም የነበረ፣ አሁንም የቀጠለ፣ የተለመደ ነገር ነው። እንደዚሁም የክርስቶስ ቃል የሀዋርያት ትንቢት ምሳሌና ተግሳፅም እንደቦታው አስፈላጊነት የሚጠቀስበት ጊዜ አለ። ይህም የሚሆነው ትምህርት ለመስጠት የእግዚአብሔርን ቃል ለመስበክ እንደአስፈላጊነቱም ጊዜውና የተፈጸመውን ድርጊት ለማስተማር ነው። በሠርግ ጊዜ ጌታ በሠርግ ቦታ ተገኝቶ ባዶዎቹን እንስራዎች በጣፋጭ ወይን ሞላቸው ተብሎ ትምህርት እንደሚሰጠው።

አንተም ለጽሁፍህ መነሻ ያደረከው ቃል በማትዮስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፯፣ ቁጥር ፲፩ ሰፍሮ ይገኛል። ቃሉም እንደሚያስረዳው እየሱስ በዛን ጊዜ ይሁዳ አሳልፎ ሰጥቶት ሽማግሌዎችና የካህናት አለቆች ተማክረው ሊገድሉት ለክስ የሚሆናቸውን ቃል ከአፉ ለመስማት ይፈልጉ ስለነበር ዝምታ መረጠ። ገዥውም በጠየቀው ጊዜ ”አንተ አልክ?” የሚል መልስ የሰጠው ለዚህ ነው።

ሁኔታው እንዲህ ሆኖ እያለ “ተቦርነ ቴዲን ተቸው” ብሎ ይሄን ቃል መጠቀም ተገቢ አልነበረም። ተያያዥነትም የለውም። ግድየለም አላዋቂነት ነው ብለን እንዳናልፍ፤ ለአረፍተ ነገሩ መጠቅለያ ያደረከው፣ ሰማይን ያለ ምሰሶ ያቆመው ክርስቶስ “ጥፋ” የምትል ቃል ብቻ ከአንደበቱ ቢያወጣ ኖሮ ጲላጦስ አይደለም መላው ቄሳር ከምድረ-ገጽ በጠፉ ነበር።” ያልከው ቃል ደግሞ፤ ለስህተትህ ሌላ ማጠናከሪያ ሆኖ ይታያል። ለመሆኑ በውቅቱ ስንት ቄሳሮች ናቸው ያሉት? ከአውግስጥስ ቄሳር ውጪ ሌላ ቄሳር አልነበረም። ቄሳሮች በየተራ የሚተኩ ንጉሦች ነበሩ። ምናልባት የሚጠፉት አይሁዳውያንና ፈሪሳውያን፣ ጣፊዎችና የካህን አለቆችን ማለትህ ይሆን? ደግሞስ እንደጠቀስከው ምሳሌ ቴዲ ጥፋ ቢል ተቦርነና መሰሎቹ ይጠፋሉ ማለት ነው? በምን ኃይሉ ነው የሚያጠፋቸው? መጥፊያቸውስ የት ነው? ማንንም ማድነቅ ይቻላል። ቴዲም መደነቅ የሚገባው ነው፤ አድናቆትህ ግን ልክ ይኑረው። (ክንፉ አሰፋ "ተቦርነ በየነ "አንተ አልክ?" - ቴዲ አፍሮን" በሚል ርዕስ ያስነበበውን ጽሑፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ! ... ተወልደ (ተቦርነ) በየነ በኢሳት ራዲዮ "ሁሌ አዲስ" ዝግጅት ላይ የተናገረውን ከዚህ ጽሑፍ መጨረሻ ላይ ያገኙታል።)

ጽሁፍህ ብዙ ስህተቶች የታጨቁበት በመሆኑ አንተ ካልከው ቃል ሳልወጣ ወደ ሌላው ልለፍ። ”ታዋቂዎች በአዋቂዎች ላይ የሚቀልዱበት ይህ የገሃዱ ዓለም እውነታ ግብረ-ገብ ወደ ግብግብ በተቀየረበት በዚህ ዘመን ባሰበት እንጂ አልጠፋም። ጥንት አንቺ-ትብሽ፣ አንተ-ትብስ ይባል የነበረው ብሂል፤ አሁን በ”አንቺ ብስብስ”፣ ”አንተ ብስብስ” ተቀይሯል ሲል አንዱ አጫወተኝ። ከቶውንም ስድብን እንደ ስንቅ በከረጢት ቋጥረው በሚጓዙበት የፌስ ቡክ ዘመን መስመር የመልቀቁ ነገር አዲስ ሊሆን አይችልም። አንተ አልክ?” ብሎ ማለፍ ምን ይጎዳል?” ያልከው ደግሞ ይበልጥ ያስገርማል። አዋቂው ቴዲ፤ ታዋቂው ደግሞ ተቦርነ መሆኑ ነው ወይ? ለመታወቅ ከሆነ ቴዲ ከተቦርነ በላይ ታዋቂ ነው። በእውቀት ከሆነ ሁለቱን ያወዳደርካቸው በምን ላይ ተመርኩዘህ ነው? ቴዲ ከየትኛው ዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ነው የዘፈን፣ የግጥምና የዜማ ዲግሪውን የተቀበለው? ተቦርነ ፈተና ወድቆ ነው ማለት ነው ጋዜጠኛ የሆነው? የማይገናኙ ነገሮችን አብረህ አትሰር። ሰው አጫወተኝ ብለህ ያቀረብከው እንቶ ፈንቶ ከተነሳህበት ጉዳይ ጋር እንኳን ዝምድና ሊኖረው ይቅርና ትውውቅም የለው። ሰው የተናገረው ሁሉ አይጻፍም እኮ ወዳጄ፤ ሰብሰብ ኮምጨጭ በል።

ከዚህ ጽሁፍህ ዝቅ ስል ደግሞ በእንግሊዞች አፍ የተናገሩት ተርጉመህ አቅርበሃል፤ ይሄስ ቢሆን ምን ያስፈልጋል፤ “ሕዝቤ እውቀት ከማጣት የተነሳ ጠፍቷል” ምን አመጣው? ፌስ ቡክንም ቢሆን ለብቻው መተቸት የሚገባው ሊኖር ይችላል፤ እዚህ ጋ ደንጉረህ አብረህ መፍጨት ምን ያስፈልጋል? የምጨምረው ነበረኝ ትቼህ ዝቅ ልበል።

የከተፋ ወግ ከመግባቴ በፊት ትለናለህ፤ ከተፋ ምንን ቃል ይወክላል? የምትጽፈው እኮ ስለትልቅ ጉዳይ ነው፤ ትላልቅ አንባቢዎችም ፊት የሚቀርብ እኮ ነው። እና እነዚህ ሰዎች ከተፋ፣ ወቀጣን የሚወዱልህ ይመስልሃል? መጽሐፍ ቅዱስ አዋቂ ነኝ ብለህ፣ አራዳነትን በቋንቋ ሽፋን ተላብሰህ ዱርዬ መሆን አብረው አይሄዱምና፤ አንዱን ያዝ። ወይ መንፈሳዊነቱን ወይ ዱርዬነቱን ምረጥ። “እኔ ማለት ምችለው ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/ ዘፋኝ ብቻ ሳይሆን፣ የጠፋውን የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የመለሰ ልብ አስታራቂ ልጅ ነው።” ብለህ የጠቀስካትም ትዝብት ላይ ጥላሃለች። ኃይሌን ስታበሻቅጡት እንዳልከረማችሁ፤ ዛሬ ስለቴዲ ይችን ተናገረና ያ ሁሉ ውርጅብኝን አወራረደ ማለት ነው። እግዚዎ!

እንዳልከው የዘፈንን ሙያ ለመተቸት አቅም ስለሌለኝ እዛው ውስጥ ገብቼ አልንቦራጨቅም። ይህ ማለት ግን ምንም አልናገርም ማለት አይደለም። ተቦርነንም እንደሰማነው ቴዲ የይርጋ ዱባለን ዘፈን በዘፈኖቹ መሀል እንደተካተተ ተናገረ እንጂ ሌላ ያለው ነገር የለም። በርግጥ ቴዲና ተቦርነ፤ ወይም አንተና ተቦርነ፤ ወይም ሌላ ሰበብ የምትፈላለጉበት ነገር ከሌለ በቀር፤ ይሄን ሁሉ ውርጅብኝ የሚያስወርድ ጽሁፍ መጻፍ የሚያስፈልግህም አልነበረም። ያንን ሁሉ ተረትና ምሳሌ በዚህ ጽሁፍ ምን አዘረገፈህ? ቆጥበህ ለሌላ ጽሁፍ ብታውለው አይሻልም ነበር?! አንድ ሺህ ዝንብ ... ሽሩባ ልትሠራ ሄዳ ... አሽቃባጭ እና ጥሩምባ ነፊ ምናምን ለምን አስፈለገ?

ጽሁፍህን ወደ ታች እያነበብኩ በወረድኩ ቁጥር፤ “ወይ ጉድ!” እያልኩ ነው የተጓዝኩት። ተቦርነ ኢሳትን ምርኩዝ አድርጎ ምናምን ያልከውም ሌላው አስገራሚ ነገር ነው። ተቦርነ በኢሳት ራዲዮ መደበኛው ዝግጅት አለው። በዛ ዝግጅቱ ላይ ቴዲንና ሥራውን በተመለከተ እንደ ጋዜጠኛ መጠነኛ ገለጻ አደረገ እንጂ፤ ኢሳትን ተመክቶ ምን ነገር ፈጠረ? ስለ ቴዲ ለመናገር የሚሠራበትን ቦታ ትቶ ወደ ሌላ ራዲዮ ጣቢያ መሄድ ነበረበት ወይ? ወይስ ከኢሳት ዝግጅት መልቀቅ ያስፈልገው ነበር? አንተም ተቦርነን የተቸህበትን ጽሁፍና ምስል፤ እንዲሁም የድምጽ ቅንብር ባንተው ገጽ ላይ አውጥተህ (ለጥፈህ) የለም እንዴ? ድረ ገጽ ስላለህ በዛ ተመክተህ ወይም አመቺ ስለሆነልህ ነው የጻፍከው ልትባል ነው? የምታቀርበው ነገር ሁሉ ፍጹም ያልተያያዘ ስለሆነ እየሰለቸኝ ነው፤ አላስችል ብሎኝ እንጂ ንዴቴን ዋጥ አድርጌ ልተውህ ፈልጌ ነበር። ነገር ግን ተናጋሪ ጠፍቶ ስህተትህ ላይ ወድቀህ እንዳትቀር ስለሰጋሁ የግድ መናገር ኖረብኝ።

ተቦርነ አለ ብለህ ወዳሰፈርከው ደግሞ እንሂድ። “በቴዎድሮስ ካሳሁን አዲሱ ኢትዮጵያ የሙዚቃ አልበም ውስጥ የአንጋፋውን የባህል ድምጻዊ የይርጋ ዱባለን ጎንደር የተሰኘ ሥራ ጨምሮ፣ 14 ያህል የሙዚቃ ሥራዎች ተካትተዋል።” አለፍ ብለህም ደግሞ፤ “ከአንጋፋው ይርጋ ዱባለ ጎንደር የተሰኘው ሥራ ውጭ ሌሎች አስራ ሦስት የሙዚቃ ሥራዎች ግጥም እና ዜማ ድርሰቶች የድምጻዊ የቴዎድሮስ ካሳሁን ናቸው።” ብሏል ትለናለህ ይሄን ማለቱ ምኑ ነው ጥፋቱ? በርግጥም ዘፈኑ ይመሳሰላል ባህላዊ ዘፈኖች ደግሞ ብዙውን ጊዜ ይወራረሳሉም። ይመሳሰላሉም። ያን ተባለና ቴዲ ምኑ ተነክቶ ነው አንተን ቡራ ከረዩ ያሰኘህ? ወዳጄ ሆይ! መለስ ብለህ የጻፍከውን ቃኝ፤ አሳፋሪም አስነዋሪም ነው። የሽያጭ ሰልፍም ከቴዲ አወዳደረ ብለህ የተቆጣህ መሰለኝ፤ ተቦርነ የጠቀሳቸው ተወዳጆቹና አንጋፎቹ ዘፋኞችን በጊዜው ይብዛም ይነስም፣ እንደ ቴዲ ይሁን አይሁንም ያሳተሙትን የሙዚቃ ካሴት በሰልፍ ሸጠው ነበር መባሉ ቴዲን ያንኳሰሰው እንዴት አድርጎ ነው? ሕዝብ ናቀ ያልከውስ በምን መልኩ ነው? ሕዝብ የናቀው የዚህን መልስ ካንተው በስተቀር ማንም ሊናገረው አይችልምና ላንተው ልተወው።

ወደ ማገባደጃህ ግድም ደግሞ አንድ ያላወቅነው ቁርሾ እርስ በርሳችሁ እንዳለ የሚገልጽ አባባል ይታያል። ይሄን እርስ በርስ ፍቱ እንጂ ሕዝብን ከትታችሁ ልታንጫጩ አትሞክሩ። ቆዳ ሲወደድ ... የሚለው የጽሁፍህ የመዝጊያ መጀመሪያ አለቦታው የተወተፈ ነው። እጅህን ከቴዲ አንሳ! የሚለውን ማሳረጊያህ ደግሞ ከላይ የጠቀስከውን የመጽሐፍ ቃል አጠናክረህ ለመናገር የፈለክ አስመስሎሃል። ተቦርነ እጁን ከቴዲ ላይ የማያነሳ ከሆነ ያችን አስፈሪዋን ጥፋ የምትል ቃል ቴዲ ያወጣትና ተቦርነና መሰሎቹ ተለቃቅመው እንደሚጠፉ ማስጠንቀቂያ መናገርህ መሰለኝ።

በዚህ በፍጹም በፍጹም አትስጋ፤ ቴዲ ተቦርነን ግፋ ይለው እንደሆን እንጂ፤ ጥፋ ሊለው እንደማይደፍር እወቅ። እንኳን በአንድ ቃል በአንድ ሺህ ቃላትም እንደማያጠፋው ያውቃል። ምክንያቱም እንዳተ ምሳሌያዊ አባባል ቴዲም እየሱስ፣ ተቦርነም ጺላጦስ አይደሉምና፤ ሊጠፋፉ አይችሉም።

አቤቱ አምላክ ሆይ! ... ክንፉ ባለማወቅ ላደረገው ይቅር በለው! ልቦናና ማስተዋልም ስጠው! - አሜን!!

*(ተወልደ/ተቦርነ በየነ በቴዲ አዲስ አልበም ዙሪያ በኢሳት ራዲዮ "ሁሌ አዲስ" ዝግጅት ላይ የተናገረውን ለማድመጥ የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑ!)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!