አቱራጋ ዓለሜ

ተሾመ ምትኩ | Teshome Metiku
እንደወጣ የቀረው አንጋፋ ሙዚቀኛ ተሾመ ምትኩ

የአገር የአስተዳደራዊ ሥርዓት በተለወጠና መሪዎች በተቀያየሩ ቁጥር በርካታ የአገሬው ሰዎች ስደት አይኑ ይጥፋ እያሉ ሕይወታቸውን ለመታደግ ተሰደዋል። እንደወጣ የቀረው አንጋፋ ሙዚቀኛ ተሾመ ምትኩ እመጣለሁ ቢልም መምጫ መንገዱ የተጠረገለት አይመስለኝም። ከዓመታት በፊት አገሬን ማዬት እፈልጋለሁ ብሎ ነበር። ሕልሙ እስካሁን አልሞላለትም።

በሰው ናፍቆት እየተብሰለሰለ በባዕዳን አገር የቀረው ታላቁ የሙዚቃ ሰው። ድምጹን ሳብ አድርጎ እንደወጠረው ትንፋሹን ሳይመልስ እንጉርጉሯዊ ስልትን በያዘው እንደ ሽለላም በሚቃጣው ሙዚቃው እነሆ የ6ኛው የለዛ ራዲዮ ፕሮግራም የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል። "ብዙ ግርግርና ወከባ የሚወድ ሰው አይደለም" አለ ብርሃኑ ድጋፌ የለዛ ሽልማቱን ለሰው ልኮለት ባሳዩት ጊዜ ያሳየውን መልዕክተኛ ቃል ዋቢ በማድረግ።

በወቅቱ ተሾመ ቀኝ ክንዱ የሚለውን ወንድሙን በማጣቱ "ይህን ሽልማት የወንድሜ ማስታወሻ ነው፤ እንባዬ እንዳይመጣብኝ እየታገልኩ ነው" ነበር ያለው።

ታዋቂው ሙዚቀኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ወንድሙና የሙያ ባልደረባውም ነበር።

ከ40 ዓመታት በላይ ልብን ቁንጥጥ አድርገው፤ ቀልብን የሚገዙ ዜማዎችን የጃዝ ስልት ያክልባቸውና ሲፈልግ በባቲ፤ በአንቺ ሆዬና በአምባሰል ትዝታ የአዜዚያም ስልት እየተጠበበባቸው የስደት ዘመኑን ተጉዟል።

በሙዚቃዎቹ ናፍቆትና ሰቀቀን፤ አገርን የመናፈቅና ዘግናኝ ተግባራትን እንዴ ለምን እያለ ሲታገል እስካሁን አለ። ከአገር የመውጣቱም አንዱ ትልቅ ምክንያት አስተዳደራዊ በደልን በአደባባይ መታገሉና መሞገቱ ነበር። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 4000 እስከ 5000 ሕዝብ በታደመበት መድረክ ልደት አዳራሽ ውስጥ የወቅቱ ለውጥ የሚሻ ሥርዓትን "ፋኖ ተሰማራ" ብሎ ዘፍኖ ተሰደደ።

ከአገር ከወጣ ጀምሮ እስካሁንም ድረስ "ምነው ዝም አልሽ" ሲላት ናልኝ ልጄ ብላ ልትቀበለው ያልወደደች አገሩን እየጠራ የልጅነት ወዘናውና ብርታቱ እየጠየመ አለ። ከ50 ዓመታት በላይ በሙዚቃው መድረክ አገሩን ሲናፍቅ፤ ተው ሲል ሲያስታርቅ፤ የኛ ነገር ብሎም ሲገረም፤ ስሞትም አታልቅሱ በአጸደ ሕይወት ሳለን እንተሳሰብ ሲል በግሳጼ አለ።

የዘመድ የባዳ እጅ ባይዳብሰ

ኑሮን ለመታገል ይችላል ወይ ሰው??

Teshome Miteku | ተሾመ ምትኩአገር ቤት ሳለ ከሶል ኢኮስ ባንድ ጋር የተጫዎተው ተወዳጁ ዜማው ነው።

ሙዚቃ በሁሉም ሰው ነፍስ ውስጥ ያለች ረቂቅ ጥበብ ናት። የዘመናት ታሪካችን እንደሚያስረዳን ኢትዮጵያዊያን የአገሬው ሕዝብ አንጎራጓሪ ነው። በአብዛኛው ሰው ልብ ውስጥ ሙዚቃ አለች። ታድለው ድምጻቸውን ለብዙኀኑ ማድረስ የቻሉት ግን እጅግ ጥቂት የሚባሉ ናቸው። ወንዶች በእርሻና ስራ ቦታዎች ሲሸልሉና ሲያቅራሩ፤ ደስታቸውንም ኀዘናቸውንም በፉከራና በሽለላ ሲያስተጋቡት ኖረዋል። ንግግራቸው፤ መከፋታቸው ውስጥ ገብቶ ሙዚቃ የጨመረው መጣፈጥ ብዙ ነው። ሴቶችም ወፍጮና መጅ ሲያገናኙ፤ እንጀራ ሲያሰፉ፤ ውሃ መቅዳት ወንዝ ሲወርዱ፤ የሚያለቅሱ ልጆቻቸውን ለማባበል ሲያንጎራጉሩ የሚያሰሙት ሙዚቃ ነው።

እናቱ ባቲ፤ አምባሰልና አንቺ ሆዬን አሳምረው ይጫዎቱ ነበር። የቤት ውስጥ እንጉርጉርጉሯቸው በቤት ውስጥ ተቀብሮ እንዲቀር የፈለጉ አይመስሉም። "አደራ ልጄ ትምህርትህን እንዳትቦዝን" ይሉት ነበር። ህጻኑ ተሾመ ምትኩ እናቱ ልብስ እያጠቡ፤ ምግብ አያበሰሉ አሳዛኝ የሆኑ ሙዚቃዎችን ሲያንጎራጉሩ ቁጭ ብሎ እየሰማ ያለቅስ ነበር።

"የእናቴ ስሜታዊ አዘፋፈን በሙዚቃዎቼ ላይ ትልቅ ተጽእኖ ያሳደረብኝ ይመስለኛል" ሲል መናገሩም አልቀረም። በእርግጥም ይህ በጎ ተጽእኖ በግልጽ መታየት የሚችል በመሆኑ ማንኛውም ሰው ሊረዳው የሚችል ነው። አብዛኛዎቹ ዜማዎቹ ናፍቆትና ብሶት ብሶት የሚሸቱ ናቸው ማለት ይቻላል። እናቱ በትክክል ተጽዕኗቸውን አጋብተውበታል።

1960ዎች ነገሮች ከአንድ አይነት የክስተት ክፍል ወደ ሌላ አይነት ሕይወትና አኗኗር የተለወጡበት ጊዜ ነው። የአገሪቱ አጠቃላይ ለውጥ የተከናወነበት የሽግግር ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል። ለምን? አዲስ አስተሳሰብ፤ ነገሮችን የማየት በሙዚቃው አዲስ አይነት አዘፋፈን፤ ቅንብር፤ አቀላለጽና አዘገጃጀት የታዩበት ወቅት በመሆኑ። የታላላቅ ባንዶች መስፋፋት ለታናናሽ ሶል ኢኮስና ራስ ባንዶች መፈጠርና መጠናከር የተጫወተው ሚና ቀላል አይደለም። የሙዚቃ ቡድኖችና ክለቦች የተስፋፉበትም ወሳኝ ጊዜ ነበር 1960ዎች።

ተሾመ የአባት አደር ይባል የነበረውን የወቅቱን የቄስ ትምህርት፤ ፊደል ቆጥሯል፤ ዳዊት ደግሟል። ቀጥሎ ያመራው ቀበና ከሚገኘው ኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት ነው። እዚያ ሲማር እናቱ በልጅ ልቡ ሲያንጎራጉሩ ያስለከፉት የሙዚቃ ፍቅር ክፉኛ ተላክፎታል። ትምህርት ቤት ሲሄድ በራዲዮ የሚሰማውን መዝሙር ቆሞ ሲያደምጥ ከክፍል ያረፍድም ነበር። በገናና ክራር ነፍሱ ናቸው። በሰፈሩ የነበሩት ዘበኞች አኮርዲዮንና ዋሽንት ሲጫወቱ ህጻኑ ተሾመ ቁጭ ብሎ ያደምጣል። የክፍሉ አስኳላ ትምህርቱም ይረሳና ሙዚቃ ጋር የጠበቀ ቁርኝት ፈጠረ።

የሙዚቃ ትምህርት እንዲማሩ ከተመረጡ 40 በላይ ተማሪዎች ጋር ለመቀላቀል ፈተናውን ተፈትኖ ማለፍ ቻለ። ወንድሙ ቴዎድሮስ ምትኩ፤ ታምራት ፈረንጅ፤ ተስፋዬ መኮንን የሙዘቃውን ፈተና አልፈው ከተሾመ ጋር የሙዚቃ ትምህርት መማር ጀመሩ።

ህጻኑ ተሼ የሙዚቃ መምህሩ የፓውል ባንክ ሃንሰን ሚስት ማርጋሬት ሃንሰንን "ይህንን መሳሪያ አጨዋወቱን አሳይኝ" ሲል ከቤቷ ያለውን ፒያኖ እያመላከታት ጠየቀ። ሴትዮዋ በጥያቄው መደናገጧ አልቀረም። "አንዴት ይህ ህጻን እንደዚህ አይነት ጥያቄ ይጠይቀኛል?" ስትል።

የፒያኖ አጨዋዎት እየተከታተለች የምታስተምረው የቅርቡ ሰው ሆነች። ሁሌም ቤት እየሄደ መጫዎቱን ቀጥሎ ፒያኖ፤ ትራምፔት፤ ቫዮሊንና ድራም ተጫዋች ሆነ። "ትራምፔቱ ሳንባህን ሊጎዳህ ይችላል።" ብሎ አባቱ ቢያስጠነቅቀውም እንኳን የሙዚቃ ፍቅሩ ግሩም ነበርና ጠዋትና ማታ ባንዲራ ሲወጣና ሲወረድ ትራምፔቱን እየተጫዎተ የሰንደቃላማን ክብር ከፍ ለማድረግ ተፍ ተፍ አለ። በትራምፔቱ አጀበ። ለዚህም ነው ከዓመታት በኋላ በልጅነቱ ተፍተፍ ያለላትን ባንዲራ ክብር ዝቅ ያደረጉትን እዩት ሲለያዩን የሚል ርዕስ በሰጠው ዘፈኑ እንዲህ ሲል የገሰጻቸው ፡-

እዩት ሲለያዩን እዩት ሲለያዩን

ኢትዮጵያ የሚባል አገር የለም ሲሉን

እኛም ዝም ብለን እንለያያለን

ከተነጋገርን ወህኒ እንወርዳለን

እዩት ሲለያዩን እዩት ሲለያዩን

በዘር በኃይማኖት በጎሣ ሲለዩን

እኛማ

እንኳን የመናገር የመኖር መብት የለን

እኛማ

ወህኒ ቤት፤ ቤታችን

አርገን እንቆጥራለን

ሰምተን እንዳልሰማን፤ ምን አሉ እንላለን

ከተነጋገርን ወህኒ እንወርዳለን

በቀበሌ ከፍለው በክልል ሲያጠፉን

እኛም ተቀብለን እንለያያለን

ከተነጋገርን ወህኒ እንወርዳለን

የመናገር መብትን ሰጠንህ አያሉን

በክልል ታግደን ምን እናወራለን

እኛማ

እንኳን የመናገር የመኖር መብት የለን

አይተን እንዳላየን ዘወር እንላለን

እዩት ሲለያዩን

ሰንደቃላማችን ጨርቅ ነው እያሉን

የክብር የመጠሪያ ምልክት ነው ስንል

ከተነጋገርን ወህኒ እንወርዳለን

የዚች አገር ችግር የብሔር ነው ሲሉን።

የሙዚቃ ጽሁፍ በሕይወቴ የገጠሙኝ ነገሮችን የምገልጽበት ነው የሚለው ተሾመ ምትኩ እያንዳንዱ ሙዚቃ የራሱ ታሪክና የት መጥነት አለው ይላል።

የየራሳቸው ስልተ-ምትም አላቸው ይላል። የሙዚቃ ጽሁፍ ከክስተቶችና ኩነቶች ጋር የተገናኘ ነው። ሁሉም የሰራቸው ዘፈኖች በየጊዜያቱ ራሱ ድምጻዊው የነበረበትን ሁኔታ አንጸባራቂ መስተዋቶች ሆነው ነው የተቀረጹት።

አዲስ አበባ ቀበና ተወልዶ ያደገው ተሾመ ብዙም ርቀት አልተጓዘም። አስተዳደጉንና የትምህርተ ቤት ቆይታውን፤ እናቱ ትነግረው የነበረውን አስቦ “ጋራ ስር ነው ቤትሽ” የተሰኘው ሙዚቃውን ግጥም መጻፍ ጀመረ። ትክዝ ብሎም ያየችው እናቱ "ምነው ተሹ? ምን እየሰራህ ነው?" አለችው። እያሰብኩ ነው ሲል ምላሹን ይሰጣታል። አታስብ ሁሉም ይስተካከላል ብላ ታበረታታዋለች። የትምህርት ቤት ሴቶችን፤ ጓደኞቹንና የአካባቢውን ወጣ ገባና ጋራ መሆን በማሰብና በመረዳት የጻፈውን የሙዚቃ ግጥም ክለብ ወስዶ አዜመላቸው። ወደዱለት።

በእጆቼ እየዳሰስኩ እንዳላጫውትሽ

ሰው ከማይደርስበት ጋራ ስር ነው ቤትሽ።

ይህ ዘፈን ዛሬ ላይ በተለያዩ የዕድሜ እርከኖች በሚገኙ ሰዎች ልብ ውስጥ ያለ ቀደምት ዜማ ነው።

የሶል ኢኮስ ባንድ አባላት የሆኑት ተሾመ ምትኩ፤ ቴዎደሮስ ምትኩ፤ አሉላ ዮሃንስ፤ ታምራት፤ አምሀ እሼቴ፤ ፈቃደ አምደ መስቀል፤ ተስፋዬ መኮንን በጋራ በመሰረቱት ባንድ እጅግ ተናፋቂ የሆኑ ስራዎችን ሰርተዋል። ከእነዚህ መካከል የተሾመ ምትኩ የዘመድ የባዳ፤ ሃሳቤ፤ ጋራ ስር ነው ቤትሽና ሞት አደላድሎኝ ዘመናትን አልፈው የሚናፈቁ ስራዎች ናቸው።

የባንዱ አባላት እንጦጦ አካባቢ አንድ ትልቅ 9 የአልጋ ክፍሎች፤ አንድ የተንጣለለ የእንግዳ መቀበያ ያለው ቤት ተከራይተው ስራዎቻቸውን መስራታቸውን ቀጠሉ። በአንድ ላይ እየኖሩ የሙዚቃ ስራ ልምምድ በማድረግ በወቅቱ ተወዳጅ ዜማዎቸን ሰርተዋል። በወቅቱ አስመራ ይገኝ በነበረው ቃኘው ስቴሽን በመገኘት መዚቃ ሰርተዋል። በሆቴሎች፤ ክለቦች፤ ዩኒቨርስቲዎች በመገኘት ሙዚቃ ከማቅረብ በተጨማሪ ከአገር ውጭም በሱዳንና ኬንያ ተፈላጊና ተወዳጅ ባንድ ለመሆን በቅቷል።

"የ1960ዎቹ የመጨረሻ ዓመታት እጅግ እስፈሪ ነበሩ" ብሎ ነበር ተሾመ ከአንድ የወሬ ምንጭ ጋር ባደረገው ቆይታ። በርግጥ እርሱ የመራሄ መንግሥት ልዑክ አልነበረም። የመንግሥት ተወካይም አልነበረም። በወቅቱ በሙዚቃው ትልቅ ተቀባይነትና ተወዳጀነትን ያተረፈ ድምጻዊ እንጂ። በፈረንጆች ጃንዋሪ 27 ቀን 1970 የሚወዳትን አገሩን ለቆ ተሰደደ። በተለያዩ መድረኮች የሙዚቃ ስራዎችን ያቀረበው ተሾመ ምትኩ በሚናፍቃት አገሩ ያዘጋጀው የመሰናበቻ ኮንሰርት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነበር። ተጉዞ ስዊድንና ዴንማርክ እንዲሁም አሁን ካለበት አሜሪካ መግባት ቻለ።

ስዊድን ከ20 ዓመታት በላይ ያሳለፈው ተሾመ የሙዚቃ ክህሎቱን እያዳበረ፤ ትምህርቱን ቀጥሎም በሶሽዮሎጂ የማስተርስ ዲግሪውን ማግኘት ችሏል። በስዊድን የባሌድና የፖፕ ሙዚቃ ዘፋኝ ልጁን ኤሚሊያ ተሾመን ተንከባክቦ አሳድጓል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ልደት አዳራሽ በሶል ኢኮስ ባንድ አጃቢነት በተሰናዳውን ዝግጅት በብሶት ውስጥ የነበሩትን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የልባቸውን ለማድረስ ነበር። በመድረኩ ሰይፉ ዮሃንስ ሦስት ሙዚቃዎችን ካቀረበ በኋላ የተሾመ ተራ ደረሰ። ተሾመ የተለመዱትን ተወዳጅ ዘፈኖች የዘመደ የባዳ፤ ሃሳቤ፤ ሞት አደላድሎኝና ሌሎችን ለመዝፈን እያሟሟቀ መድረክ ላይ ይጠባበቃል። ከአራት ሺህ አስከ 5ሺህ የሚገመተው ልደት አዳራሽ ውስጥ የተሰበሰበው ታዳሚ “ፋኖ ተሰማራን ዝፈንልን” ሲሉ በመጮህ ጠየቁት።

"እንዴ ምን ነካችሁ አብዳችኋል?" ሲል ተሾመ ያልጠበቀው ጥያቄ ነበርና ደነገጠ።

“ፋኖ ተሰማራ

እንደ ሆቺሚኒ እንደ ቼ ጉቬራ”

ታዳሚው በጉጉት የሚጠባበቀው ሙዚቃ ነበር። መዝፈኑን እዘፍናለሁ ግን ኃላፊነቱን ትወስዳላችሁ? አላቸው። መደረኩ ላይ የነበሩት ተሼ ቀጥል ሲሉ ጮሁ። "እሺ መጀመሪያ አልማዝ ምን እዳ ነውን ልዝፈንላችሁ" ሲል ጠየቃቸው። ማንም ደስ አላለውም። ፋኖ ተሰማራን ነው በእግር ጥፍሩ ቆሞ ሁሉም የሚጠብቀው። በመድረኩ መሀልና ዙሪያ ቆመው በአይነ ቁራኛ የሚጠባበቁት ፖሊሶች፤ የክብር ዘበኞችና ወታደሮችን በጎ ፈቃደኛነት ተሼ በቅድሚያ የጦር ኃላፊውን ምን እንዳደርግ ትወዳላችሁ ሲል ጠየቀው። በዚህ ጊዜ ተማሪዎች ፋኖ ተሰማራን እየዘመሩት ናቸው። ከመድረኩ ዘወር ብሎ ተሾመ የጦር ኃላፊውን ሲጠይቀው መዝፈን ትችላለህ። የሚል ምላሽ ሰጠው። መደረኩ እብድ ሆኖ መሬት ላራሹ እየተዘፈነ ነው። ዘፈኑም መዝሙሩም ቀለጠ። ሁሉም ማለት የሚፈልገውን አለበት። የልብ አድርስ መድረክ ሆነ።

ለተሾመ የደስታና የሰላም ምንጮች ከዚህ ቀን ጀምረው ደረቁ። በየሄደበት በፖሊሶችና በጥበቃ አካላት በምርመራና በጥርጣሬ ዓይን መታየቱ እንቅልፉን ነሳው። ለቤትህ ግብር ሦስት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር ትከፍላለህ የሚል ትዕዛዝ ደረሰው።

በአንድ ዕለት ዙላ ክለብ እየተጫወተ ባለበት ቅጽበት ፖሊሶች መጥተው አንገቱን አንቀው ወደ ሦስተኛ ጣቢያ ወሰዱት። ለሦስት ቀናት አስቸጋሪ በሆነ እስራትም አቆዩት።

እነዚህ ሰዎች የኔን በሰላም መኖር አይፈልጉም ማለት ነው ብሎ ጉዞውን ወደ ስዊድን ያደረገው ተሾመ፤ እንደዘበት ከሃያ በላይ ዓመታትን ኖሮ ቀጣይ ጉዞውን አሜሪካ አደረገ። ብዙዎች ሙዚቃዎች መከፋትና ናፍቆት የአስተዳደር በደልን የሚሟገቱና ታሪክን ዞር ብለው የሚያስታውሱ ናቸው።

ምነው ዝም አልሽ፤ መሪ አልባ ሕዝቦች፤ ወሎ፤ እቴሜቴ የሎሚ ሽታ፤ አልችለውም እኔ ካንቺ ተለይቼ፤ ፎቶዬን አይቸው፤ እወድሻለው፤ ሱሰኛሽ፤ ታሪኩ ባጭሩ፤ ቤታችን አንድ ነው፤ ትንሳኤ፤ ስሞት አታልቅሱ፤ የኛ ነገር፤ ውዴ፤ አስራት፤ እዩት ሲለያዩን እና ሌሎች ዜማዎች ከ40 በላይ ዓመታትን በስደት ያሳለፈው ተሾመ ምትኩ ድንቅ የሙዚቃ ችሎታውን የሚመስክሩ ዜማዎቸ ናቸው። ከፍሬ ሕይወት ለማ ጋር የዘፈናቸው በዘመን አልበም ውስጥ የተካተቱት ባቲ፤ ትዝታዬ፤ እሽሩሩና ሌሎችም በዘመናት መንጎድ የማይበገረውን፤ የማይነጥፍ የማዜም ችሎታውን የሚያሳዩ ስራዎቹ ናቸው።

ማንኛውም ሙዚቃዬ ዘመናቱን ወካይ መሳሪያ ነው ያለው ተሾመ አስተዳደራዊ በደሎችን በሙዚቃው አስተጋብቷል። መሪ አልባ ሕዝቦች የተሰኘው ዜማውን ጨምሮ እዩት ሲለያዩን እስከሚለው ዘፈኖቹ ባለውም ሆነ ባለፉት መንግሥታት የሚስተዋሉትን ምስነቶች እንዲያንጸባርቁ የዘመን ገላጭነት ሚናቸው ከፍ እንዲል አድርጎ የሰራቸው ቅርሶች ናቸው። ብልሹ አሰራርን የከተበባቸው የትናንትና የዛሬን ኡደት አመላካች፤ ነገን በትንቢት ቀድመው ዋ! በማለት የሚጠቁሙ ናቸው።

አስራት በሚለው ሙዚቃው የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት መስራችና ዋና ሊቀመንበር በመሆን ታላቅ የወያኔ ተቃዋሚ የነበሩትን ፕሮፈሰር አስራት ወልደየስ ለአገር አንድነት የሞከሩትን ውጥን አውስቷል።

በዘመነ ኢሕአዴግ የነበራቸው ተጽእኖ ፈጣሪነት በማየት መሪዎች በፍርሀት ወደ እስር ቤት እንዲገቡ ካደረጓቸው በኋላ በአገሪቱ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ቀዶ ጠጋኙ የሆኑት በልብ ሕመም ተሰቃይተው እንዲሞቱ የተደረጉ አመድ አፋሽ ሰው ናቸው። እሱም በስራው የዘከረው ይህንን ታላቅነታቸውን ነው።

በ1949 የተወለደው ታላቅ የሙዚቃ ሰው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ልደት አዳራሽ ውስጥ ያቀረበው ፋኖ ተሰማራ መዝሙር ጠንቅ ሆኖት በ1970 ሕይወቱን ለማቆየት ሲል አገሩን እንደተለያት ዛሬም በሰው ናፍቆት እንደተራበ በአሜሪካን አገር አለ።

“እርቆኛል በጣም ያለሽበት አገር፤ ናፍቆቴን አውጥቼ ለማን ሰው ልናገር??” ይህንን እያለ በባእድ አገር ይኖራል።

“በይ ደህና ሰንብቺ የሩቅ ለሩቅ ፍቅር፤ በህልም ተገናኝተን እስክንነጋር” ብሎም ያልናፈቃት ይመስል አገሩን በኩርፊያ መሰል ስንብት እየተጽናና ይብሰለሰላል።

ሐምሌ 16 ቀን የአፍሪካ አባት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የተወለዱበት ቀን ነው። ይህ ታሪኩ ባጭሩ የተሰኘው የተሾመ ምትኩ ዜማ በምስጢር ተድበስብሶ የቀረውን ሥርዓተ ቀብራቸውን የሚገልጽ መለከት ይመስለኛል። እስኪ ታሪኩ ባጭሩ የተሰኘውን የሙዚቃ ግጥም ቀንጨብ አድርገን እናንብበው᎓-

ስበላም አዝዬ

ስጠጣም አዝዬ

ዘመናት አለፈህ ሳትነቃ ማሞዬ

17 ዓመት አስከሬን ደብቄ

ችዬው እኖራለሁ ኀዘኔን አምቄ

አሁንስ ይውጣልኝ ልናገረው ለሰው

እንዲህ ያለ ስቃይ ማነው ያልደረሰው

አንተ የሞትክበትን የጥይቱን ዋጋ

ከፍዬ መጣሁኝ ለማንስ ሰው ላውጋ

ኀዘን ተከልክሎ ኀዘኔ አይወጣልኝ

እሽሩሩ ማሙሽ ነገ ብትነቃልኝ

ቅበረው ይሉኛል ኧረ እንዴት ልሁን

ቀብር መከልከሉን አልሰሙ ይሆን

ተናግሬው ልረፍ ያዋጁን በጆሮ

ሐምሌ 16 ነው የቀብሩ ቀጠሮ

የኀዘን ቀጠሮ።

ተሾመ ምትኩ ወደ አገሩ ለመግባት ብዙ ጊዜያት ፍላጎትና ምኞት አለው። ማንም ሰው እናት አገሩን ማየት እንደሚፈልግ ሁሉ።

በሦስቱም የአስተዳደር ዘመናት ጥበብን ለፍትሕና ለአገራዊ አንድነትና መብት መጠየቂያ አድርጎ ተጠቅሞባታል። ልቡ አገር ቤት ገብቶ እያደረ፤ አካሉ ብቻ በባዕዳን አገር የሚያድረው ወይ የአገሪቱ አገዛዝ አልፈቀደለት፤ እሱም ሁኔታውን ዓለም እንደሚታዘበው ተረድቶት ለመምጣት እግሩ ወደ ኋላ እየተጎተተበት ይሆን?

ማን ይሆን ዓለማት በሙዚቃ ሥራውና ክህሎቱ ያደነቁትን ሰው በሰላም ግባ ብሎ ዕውቅና የሚሰጥ፤ ማን ይሆን ዛሬ በመንደር እየቆረሱ ከሚሰጡት የክብር ምንትሴ ለዘመናት የሙዚቃ አበርክቶቱ ክብርና እውቅና የሚሰጠው?

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!