አቢ ላቀውና ሔለን በርሔ

አቢ ላቀውና ሔለን በርሔ

አቱራጋ ዓለሜ

ይሄንን ለማለት ያበቃኝና ሐሳብ የጫረብኝ በቅርቡ የወጡ አዳዲስ ተናፋቂ የነበሩ ድምጻዊያት ሥራዎች በየቦታው፤ በመጠጥ ቤቱ፤ ታክሲው፤ መንገዱ፤ ባርና ሬስቶራንቱ፤ መዝናኛና መስተጓጎያ ቦታዎች መከፈት የተከለከሉ መስሎ ስለተሰማኝ ነው።

የመጀመሪያዋ ሴት ዘፋኝ አቢ ላቀው ናት፤ ሥራዋ እንደ ፋሲል ደሞዝ ሙዚቃዎች ሞልቃቃ ነቷ ለልማቱ አይበጅም በሚል የተከለከለ ይመስል፤ እሷን ሲያደምጥ የተገኘ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተወገዘ ይመስል፤ ደብዛዋ ጠፍቷል።

ማን አለ እና ደስታ የተሰኙ ሙዚቃዎቿ ቀደምት ከሆነው አልበሟ ውስጥ ተደማጭና ተወዳጅ እንዳደረጓት አውቃለሁ።

ከእነዚህ ባለፈ ደግሞ በቅርብ ያወጣችው የኔ ሐበሻ የተሰኘ ነጠላ ዜማ ቪዲዮ ስሟን የናኘ ሥራዋ ነው።

ይህች ዘፋኝ ይሄንን ጽሑፍ እየጻፍሁ ባለሁበት ቅጽበት ዩቱዩብ የምስል ማከማቻና መመልከቻ ላይ ያለው የኔ ሐበሻ የሚለው የሙዚቃ ቪድዮ 23,077,658 ብዛት ታይቷል።

8,011 አስተያቶች፤ 42 237 ላይክ 7592 ደግሞ አን ላይክ ያለው ዩትዩብ ላይ ከተጫኑ ኢትዮጲያዊ ምስሎች በአንደኛነት እየመራ ያለ የሙዚቃ ቪድዮ ነው።

ይህ ለመሆኑ ሌላ ጥናት የሚያስፈልግ ቢሆንም እንኳን ይሄንን ያልህ አስተያየት፤ ላይክና አን ላይክ፤ እንዲሁም ተመልካች ማግኘቱ፤ ተወዳጅና የአድማጩን ቀልብ የሳበ መሆኑን ያሳያል።

አቢ ላቀው በዚህ ሙዚቃዋ የአድማጭ ልብ ውስጥ ተወዳጅ ድምጻዊት በሚል እንደሰፈረችና ስትሞላቀቅ ያምርባታል ተብላ እንደተወራላት አውቃለሁ።እናንተም አይታችኋት ስትሞላቀቅ፤ እህ እውነት ነው እንዳላችሁ እገምታለሁ።

ታዲያ አቢ ላቀው በዚህ የአድማጭ ተቀባይነትና ተወዳጅነት ሙቀት ሌላ አልበም ይዛ ከተፍ አለች።ርእሱን ቀደም ሲል ባወጣችው አንድ ነጠላና ተወዳጅ የሙዚቃ ርእስ የኔ ሐበሻ አለችው።

የአልበሙንም ሽያጭ ለበጎ አድራጊው መቄዶንያን ይሁንልኝ አለች። ይህ በሆነ በቅርበት ጊዜ ሆዴን ሰው ራበው የሚል አንድ ምስላዊ ሙዚቃ ከአልበሙ ውስጥ እንደ ቃጫ ተመዞ ወጥቶ መደመጥ ጀመረ።

አቢ ሆዬ እንደ ለመደችው መሞላቀቅ ያምርብሻል ብሎ ባሞገሳት አድማጭ ፊት፤ በጥራት ምስል፤ በአቀራረጽ፤ ታሪክን በማስተዋወቅ፤ በግሌ ምርጥ ያልሁትን ሥራ ይዛ መጣች።ዜማውና ሌላው ነገር ባይጥመኝም።

የግሌን ስሜት እንጂ ሙያዊ ነገሩን የሚተች አቅም ስለሌለኝ እሱን ለባለሙያዎች እተወውና፤ ዜማው ግን ምንም ደስ የሚል ነገር የለውም።በቃ ሆዴን ሰው ራበው የሚለው የአቢ ላቀው ሙዚቃ ጎንደርን ከነ እምነቷ፤ ባሕሏ፤ ሙዚቃዋ ፍንትው አድርጎ በጥሩ ካሜራ ለማሳየት የተሰራ ማስታወቂያ መስሎ ነው የተሰማኝ።ሲጀምር እንዲያውም የተዋሕዶ መዝሙር መስሎኝ ነበር፤ ቆይቶ ግን አቢ ጎንደር ግንብ ጥግ ቆማ ስትሞላቀቅ በማየቴ ሙዚቃ ነው ብያለሁ።

የሆነው ሆኖ የአቢ ላቀው አዲስ የኔ ሐበሻ የተሰኘ አልበም በመጠጥ ቤቶች፤ ታክሲ ውስጥ፤ ጎዳናዎች ላይ መሰማት፤ በቴሌቪዠን መታየት አቆመ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ እንደ አዲስ አልበም መደመጡ ቀርቶ፤ ዝምታ ሆነ።

በግሌ ሙዚቃ ላይ ዜማ እንጂ መልእክት ከአቢ ላቀው አልጠብቅም፤ ብዙው ሰውም ከሙዚቃ መልእክት ይልቅ ለዜማ ትኩረት የሚሰጥ ይመስለኛል።በመሆኑም የአቢ ላቀው አልበም እየተደመጠ ያይደለው ምናልባት ዜማው ሳቢ ባለመሆኑ ይሆን ስል እጠራጠራለሁ።

እርግጥ አድማጭ ቀልቡ የት ጋ እንዳለ፤ ምን አይነት ሙዚቃዎችን እንደሚወድ፤ ለየትኛው የሙዚቃ አይነት ጆሮ እንደሚሰጥ ማወቅ ከባድ ነው።የአድማጭ ቀልብ እንደ ሱናሜ የሚሆንበት እድል ሰፊ ነው። ስሜት ወላዋይ፤ ወቅትና ሁኔታ፤ ማንነትና ሌሎች ሁኔታዎችን ተከትሎ የሚፈስ ጅረት በመሆኑ።

ለማወቅ በሚቸግረኝ ሁኔታ የአቢ ላቀው ሙዚቃ ዝም ብሎ፤ በሳይለንት እየሄደ ነው።እንደ አዲስነቱ እዚህም እዚያም እየተሰማ አይደለም።

ሙዚቃችን የትኛው ዘርፍ ላይ ው ያለው፤ የሚያስጨፍር፤ የሚያስደንስ፤ የሚያስቆዝም፤ የሚያስደነግጥ፤ የሚያስገርም፤ ታሪክንየሚነግር፤ የሚያሞግስ፤ የሚረግም፤ ባሕላዊ ዘመናዊ፤ ወይስ የብሔር ብሔረሰብ ሙዚቃዎችን በማስተጋባት ላይ ነው ?? የሚለውን ጉዳይ የዘርፉ ባለሙያዎች በጥናት የሚለዩት ሆኖ።

አንዳንድ ዜማዎች፤ ዘፋኞች አሉ እርግጥ ቆይተው የሚደመጡ። እዮብ መኮንን በዚህ ምሳሌነት ይጠቀሳል።

ሁለተኛዋ ሴት ሔለን በርሔ ናት።ሔለን እኔ ሳስታውሳት፤ ኦዛዛሌና በሚል ስሟን ከአድማጭ ጋር ያስተዋወቀች ዘፋኝ ሆና ለፊልም ማጀቢያ በሰራችው ፔንዱለም ሙዚቃም ተወዳጅነቷን ከፍ አድርጋለች።

ከዚህ ባለፈ ሔለን ዘፋኝ ሆና ስሟን በዝና ያሳወቀችው 2003 ላይ ባወጣችው ከማይ አልበም መሆኑ ግልጽ ነው።በብዙዎች ተፋቃሪያን ዘንድ እንደ ግብዣ የሚቀርቡ ሙዚቃዎቿ ዛሬም ድረስ ኅሊናዬ ውስጥ እንዳሉ፤ በብዙዎቹ የሙዚቃ አድማጮች ዘንድም የማትረሳ ዘፋኝ ናት።ሙዚቃው በወጣበት ወቅት የፍቅር አዲስ ነቃ ጥበብ እምቢ አልበም፤ አስቴር አወቀ ጨጨሆ አልበም ባዲስነት እየተደመጡ ነበር።

የሔለን በርሔ ከማይ አልበም እነዚህን ተደማጭነት ያላቸውና ተወዳጅ ዘፋኞችን ሥራ ጥሶ የተደመጠ ሙዚቃ ነው ብል ሁላችሁም የምታስታውሱት ሀቅ ነው።

ሔለን በርሔ አዲስ አልበም ልታወጣ ነው በሚል ሲወራ ጀምሮ እኔን ጨምሮ አድናቂዎቿ ወይም አድማጮቿ ምን አይነት አሪፍ ዜማ ነው ይዛ የምትመጣው በሚል፤ ቀድሞ በልባችን ካለው ስሟ ትንሴት ጓጉተን ነበር።

እውነታው ግን አልበሙ ወጣ፤ እኔ በግሌ ስጠብቀው የነበረው አልበም ዋጋ አንድ ቀደማ በለቀቀች፤ እስኪ ልየው በሚለው ቪድዮ ቀድሞ ኮምሽሿል።ዜማው ፍጹም ከምጠብቀው አይነት ጋር አልመጣጠንለህ አለኝ።ሙዚቃ መዝፈን ሁሉ አቁማ የቆየች መስሎኝ ነበር፤ የት ሄደ ያ ከማይ ላይ በስስት ስንሰማው የነበረው ለዛዋ፤ የት ሄደ ያ አታስፈራራኝ፤ የሕልሜ ጓደኛ፤ የኔ ፍቅር፤ ልቤ እና ሌሎች ውስጥ ያለው ለዛ እና ጣፋጭነት??

የነጻነት መለሰ ድጋሜ የተሰሩ ስብስብ ዘፈኖችም ሌሎች ተወዳጅ ድምጻዊያን አድሰው(ሪሚክስ )አድርገው እንዳስደመጡን ሥራዎች ሁሉ (ኤፍሬም ታምሩና የጸጋዬ እሸቱ ሥራዎች ምን ያህል እንደተደመጡ፤ አሁንም እንዴት ያህል እየተደመጡ እንዳሉ እናንተም እኔም ምስክር ነኝ) ሳይደመጡና አንድ ሳምንት ያህል በሬድዮና መጠጥ ቤቶች፤ ታክሲ ላይ ስሰማቸው ቆይተው አሁን ዝምታ ውስጥ ያሉ ሆነዋል።

ሌላው በቅርብ የሙዚቃ አልበሙን በነጠላ ዜማ ለሚያውቁት አድማጮች ያደረሰው ወጣት ድምጻዊ እሱባለው ይታየው (የሺ ይባላል፤ እናቱን ስለሚወድ መሰለኝ) ትርታዬ ብሎ የሠየመውን አዲስ አልበሙን ማድረሱ የሚታወስ ነው።

ይሄ ልጅ ከዓመታት በፊት ማሬ በሚል የታወቀበትን ነጠላ ዜማ ለአድማጮች ማድረሱና በብዙዎች ዘንድ ማሬ የሚል ቃልና ዘፈን እንድንሰማ ምክንያት የሆነ ይመስለኛል።

ከዛ ወዲህ ብዙዎች ማሬ ማሬ የሚል ሙዚቃዎችን አሰምተውናልና። እርግጥ ቀድሞ በእነ አስቴር ከበደ ዘመን፤ በነ ሰማሀኝ በለው ዘመን ማሬ የሚሉ ቃላትን ሙዚቃ ውስጥ መጨመር፤ አፍቃሪን የማር ጥፍጥና ሰጥቶ ማድነቅ የተለመደ ነው።ሰማሀኝ አንቺ ልጅ ማር አለሽ፤ ጎጃም ተወልደሽ ብሎ እንዳሞገሰ ሙዚቃው ማስረጃ ሊሆነን ይችላል።

አንዱን ጥሎ አንዱን ነው መቼም እና እንዳልኋችሁ፤ እሱባለው ይታየው ትርታዬ የሚለው አልበሙ በደምብ እየተደመጡ ካሉ አዲስ የሙዚቃ ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ ነው።

እኔ የእሱን ልጅ ሙዚቃ አዲስ አበባ ውስጥ የትም እሰማዋለሁ፤ በሬድዮ፤ በታክሲ፤ በምግብና መጠጥ ቤቶች ሁሉ እጅግ እየተደመጠ ያለ አልበም ነው ብል ማጋነንና አድልዎ አይሆንብኝም።

ከዓይኔ አትጠፊም፤ ትርታዬ፤ ተው፤ የትም ይመቸኛል፤ ደግሞ ደግሞ፤ ህያው ስምና ሌሎችም ሙዚቃዎቹ በርካታ ቦታዎች፤ ግለሰቦች አፍ ላይ አልጠፉም፤ ተደማጭ ነው ማለት የምችለው እኔ ባለሁበት አካበቢ ሆኖ፤ እንደሰማሁት፤ እንደምሰማው ልጁ ሙዚቃው እየተደመጠለት ነው።

ልጁን በግሌ አድማጭ ባልሆንም እንኳን የዜማና የግጥም ችሎታ ባለቤት፤ ባለ ተሰጥኦ መሆኑን አደንቃለሁ።በእሱ እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣት ልጆችን ግጥምና ዜማ እየሰጠ በሙዚቀኛነት መዝገብ እንዲሰፍሩ እያደረጋቸው መሆኑን አደንቃለሁ።

ጤና አዳሜና እንጃ ሰሞኑን የሚሉ ግጥምና ዜማዎችን ጽፎ ቃለ አብ ሙሉ ጌታ ለሚባል ልጅ፤ የቀን ቅዱስ ግጥምና ዜማን ለሚለና ቢኒያም፤ መገን እኔ ግጥምና ዜማ ለዮሐንስ ግርማ  እና ለሌሎችም ጀማሪ ድምጻዊያትና ድምጻዊያን ግጥምና ዜማ ደርሶ መስጠቱ፤ ችሎታ እንዳው ማሳያ ነው ለማለት እደፍራለሁ።

ለሁሉም ነገር፤ ሙዚቃ የመደመጥና ያለ መደመጥ ችግር የዜማው መጣፈጥና የድምጻዊያን ሙዚቃዎቸውን እሽት አድርገው፤ ጊዜ ወስዶ የመሥራት እንዲሁም የሙዚቃ ገበያውን በአግባቡ ተረድቶ የመዝፈን ጉዳይን በአግባቡ መረዳት ላይ ይመስለኛል።

ጌታቸው ካሳ በአንድ ወቅት ዜማ አልቋል ብሎ መናገሩን አስታውሳለሁ፤ ይሄንን ሐሳብ ተሾመ ምትኩም ደግሞታል እንዲያውም ዜማ የማለቁን ጉዳይ ዜማ ከጃማይካ ነው እየመጣ ያለው በማለት ነበር ያስረዳው።አሁንም እንደምናስተውለው ዜማዎች ቀደምት ከሆኑት ሙዚቃዎች በተወሰነ መልኩ እየተመሳሰሉ ነው።

ፀሐዬ ዮሐንስም በአንድ ወቅት ባደረገው ቃለ ምልልስ "ድሮ ዜማዎችን እኔ ራሴ እሰራ ነበር፤ አሁን ግን የራሴ ዜማዎች እየተመሳሰሉብኝ ስለሆነ ሰዎች እንዲሰሩልኝ አደርጋለሁ "በማለት ድምጻዊያን ራሳቸው በሚደርሷቸው ዜማዎችም ተመሳስሎሽ እንደሚያጋጥም አስረድቷል።

እርግጥ ፈጠራ፤ አዳዲስ ዕይታዎችን ማየት እስከተቻለ ድረስ፤ የፈጠራ ባለቤቶች ጥረት እስከታከለበት ድረስ አዳዲስ ሐሳብ ማፍለቅ ባይቻልም እንኳን አዳዲስ ዜማዎችን መሥራት እንደሚቻል፤ ዜማ እንዳላለቀ፤ እንዳልሞተ፤ እንዳልተከተተ የሚያሳዩን ጥሩ ዜማ ደራሲያን፤ ጥሩ ሙዚቀኞች አልጠፉም።

የሙዚቃው አይነት፤ አካሄድ ዓለማቀፍ ዠዋዠዌ እያላጋው፤ ዘመናዊነትና ኋላቀርነት እያጠናገረው በየዘመናቱ የራሱን መስመር እየተከተለ፤ ሞተ ሲባል እየተነሳ፤ ተነሳ ሲባል ሞተ እየተባለ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በቅቷል።

በአገራችን ዘመናዊ ሙዚቃ ታሪክ የሚጀምረው የባንዶችን መስፋፋትና፤ የምሽት ቤቶችን ሙዚቃ የማጫዎት ክስተት ተከትሎ ነው።ይሄም ዘመን 1950ዎቹ ጥላሁን ገሠሠ፤ ተፈራ ካሳ፤ ተዘራ ኃይለ ሚካኤል፤ ማህሙድ አህመድና ሌሎች ድምጻዊያን ይሰሩበት የነበረውን ሾፌሮች ቡና ቤትን መመስረት ተከትሎ ነው።

ያንን ጊዜ ሙዚቃው የውጭውን አገር አለባበስ፤ የሙዚቃ መሳሪያ፤ መድረክ አመራር፤ የቅንብር ስልት ተከትሎ፤ ከበሮ፤ ማሲንቆ፤ ዋሽንት፤ ክራር፤ በገና እና ሌሎችንም የአገሪቱ መሳሪያዎች ተከትሎ ከሰለጠነው ክፍለ ዓለም አውሮፓ የሚመጡ የሙዚቃ መሳሪያዎችን የተቀበለበት ዘመን ነበር።

ዘመናዊነቱ ከኦርኬስትራ የታጀበ፤ ሳክስፎን፤ ጊታር፤ እምቢልታ፤ ክላርኔት፤ ፒያኖ፤ ኦርጋንና ሌሎችን ዘመናዊ የሚባሉ የውጪው ዓለም የሙዚቃ መሳሪያዎች መጠቀሙና የሚያነሳቸው ጉዳዮች ቀደምት አዝማሪዎች ከሚነግሩን በተለዬ መልኩ ስለ ግለሰባዊ ፍቅርና ገጠመኝ የሚተርኩ መሆናቸው ይመስላል።

በዚህ ጊዜ ሙዚቃው ከቀደምት አዝማሪዎች ዘንድ ጥሩ ተቀባይነት አላገኘም ነበር፤ ለዚህም የአለማየሁ እሸቴ የአዘፋፈን ስልትና ዳንስ ስታይል፤ በወቅቱ ገናና ከነበሩት ኤልቪስ ፕሬስሊንና ጀምስ ብራውን ጋር ተመሳሳይነት የነበራችው በመሆኑ፤ ቅኔ በሚነገርበት አገር ይሄንን ማድረግ ተገቢ አይደለም ሲሉ አለማየሁና ዘመናዊ ሙዚቃው ላይ ትችት የሚሰነዝሩ አዝማሪዎች እንደነበሩ ባንድ ወቅት ስለ አለማየሁ እሸቴ የተጻፈ ጋዜጣ ላይ ማንበቤን አስታውሰለሁ።

እነ ንጋቷ ከልካይ፤ ሽሽግ ቸኮል፤ ሜሪ አርምዴ፤ ፈረደ ጎላ አሰፋ አባተ አገር ፍቅር ቴያትር በነበሩበት ወቅት የአገር ፍቅር ሙዚቃዎችን ይዘፍኑ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል።እንዲያውም ጥላሁን ገሠሠ ሕጻን ሆኖ አገር ፍቅር ቴያትር ቤት ሲቀጠር ኢዩኤል ዮሐንስ "እድሜህ ከሚፈቅድልህ ውጭ የፍቅር ዘፈን እንዳትዘፍን" ማለቱ በጥላሁን ገሠሠ የሕይወት ታሪክ ማስታወሻ መጽሐፍ ላይ ሰፍሯል።

ቀደም ብለን በእነ ንጋቷ ከልካይ፤ ሽሽግ ቸኮል፤ ሜሬ አርምዴ ጊዜ የነበሩትን ዘፋኞች አውድ ሙዚቃ ስንመለከት በብዛት ቅኔ አዘል መልእክት ያላቸው፤ ሽለላና የአገርን ክብር የሚያወድሱ ዘፈኖች ሆነው እናስተውላለን።

ምናልባት ያ አልደፈርም ባይነት በፈጠረው ጣሊያንን መልሶ ለማባረር በተከፈለ ጀግንነት የተፈጠረ ስሜት ትንሴት፤ ሙዚቃው የአገርና የጀግንነት ሊሆን ቻለ ብሎ መገመት ይቻል ይሆናል።

በዘመናዊው ሙዚቃ ዘመን፤ ደግሞ ዓለም የአንድነትን ዜማ የሚያስተጋባበትና፤ ብዙዎቹም የአፍሪካ አገራት ነጻ በመውጣታቸው፤ የፍቅርና የእለት ከእለት የሆኑ ግልጽ ሐሳቦች ላይ ሊጠመዱ ችለው እንደሁስ??

በ1970ዎቹ ምናልባት ከዘመኑ ጋር ሊገናኝ ይችል እንደሁ አላውቅም፤ የትዝታና የናፍቆት፤ የቁዘማ፤ የመከፋት የኀዘን መሳይ ሙዚቃዎች የተስተጋቡበት ጊዜ ነበር ለማለት ያስፈደፍራል።

ጸጋዬ እሸቱ፤ አረጋሀኝ ወራሽ፤ ሐመልማል አባተ፤ አስቴር አወቀ፤ ሙሉቀን መለሰ፤ ቴዎድሮስ ታደሰ፤ ኤፍሬም ታምሩ፤ ነዋይ ደበበ እና ሌሎች በርካታ ድምጻዊያን ሙዚቃዎች ከላይ ባልኋቸው መሰረታዊ የሐሳብ ጭብጦች ላይ ያተኮሩ ነበሩ።

በዘመናዊው የሙዚቃ ዘመን ሙዚቃው ባንድ ወቅት ዘመናዊ ሆኖ፤ ወርቃማው ዘመን ላይ ደረሰ ሲባል ባንድ ወገን ደግሞ አበድሁልሽ፤ ሞትሁልሽ ይዘት ያላቸው፤ ግልጽነት ጎልቶ የሚታይባቸው ሙዚቃዎች ከነ ዳንሱ ስታይል አውሮፓዊ አካሄድ የተከተሉ ይመስላሉ። የወቅቱ የተግሳጽና ወቀሰ መነሻም ይሄው ነበር ማለት ይቻላል።

የኢትዮጲያ ቴሌቪዠን በአንድ ወቅት ምናልባትም 1980 ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሺ እመቤት ዱባለ፤ ኬነዲ አባተ፤ ጌራ ወርቅ ነቃ ጥበብና ሌሎችም ያሉበትን ዘመን በማንሳት ሙዚቃው ሄዶ ሄዶ ሞተ፤ ቀድሞ የተዘፈኑትን እንደገና እያደሱ የሚዘፍኑ ፍራሽ አዳሽ ሙዚቀኞች እየበዙ ናቸው በሚል፤ ሙዚቃው ከፈጠራ ነጠፈ፤ ሞተ ብሎ ፕሮግራም ሰርቷል።

አሁን ላይ ምናልባትም በጃኪ ጎሲ ሰላ በይ ዘመን ብቅ ያለው ባሕል ዘመናዊ የሚባል ቅልቅልና እስክስታ የበዛበት የሙዚቃ ዘርፍ በብዙዎች ዘንድ፤ ሙዚቃ ድሮ ቀረ እየተባለ እንዲነገርና በርከት ያለው ሰው ወደ ድሮ ሙዚቃዎች እንዲመለስና የልጅነት ሙዚቃዎችን እንዲያዳምጥ የተገደደ ይመስላል።

የሙዚቃ ባለሙያው ሰርጸ ፍሬ ስብሀት ባሳለፍነው ዓመት የቴዲ አፍሮ ሙዚቃ በወጣበት ወቅት ቴዲን የሚያደንቅ እንጂ የሚከተል ድምጻዊ እንደሌለ ጠቅሶ፤ የአገራችን የሙዚቃ ጉዞ ሄዶ ሄዶ ፍቅር ወጣ የሚባልበት ጊዜ ላይ ደርሷል ሲል በቁጭት መናገሩን አስታውሳለሁ።

ይህ ፍቅር ወጣ የሚል፤ ሄድ መለስ የተሰኘ ሙዚቃ ደግሞ ያመቱ ምርጥ ክሊፕ ተብሎ ተሸላሚ መሆኑ፤ ነገሩን ይበልጥ ውስብስብ ያደርገዋል።ባለሙያዎች የሚፈልጉትና የሚሉት ሕዝቡ ወይም ሙዚቃ አድማጩ ከሚለው ጋር ፍጹም የማይገናኝና ሆድና ጀርባ እንደሆነ ማሳያ ነው።

ወጣቱ ሙዚቃ አድማጭ አሁን ላይ የሚወጡ እስክስታ-በዝ ሙቃዎችን እየወደዳቸው፤ እየዘፈነባቸው፤ እየጨፈረባቸው እንዳለ እናያለን።

ባለሙያዎችና ቀደምት ዘመን ላይ የነበሩ ሰዎች ደግሞ ሙዚቃ ድሮ ቀረ የሚል ሙሾ ላይ ናቸው።ያሁን ወጣቶች ደግሞ ነይ ማታ ማታን ሙዚቃ ከፍተው ደስተኞችና ዘፋኞች ሆነዋል።የቀድሞ ሙዚቃዎች ለቅሶ የሚመስለሏቸውም በርካቶች ናቸው።

በትውልድ መካከል የተፈጠረውን ክፍተት ሊሞላው የሚችል የትኛው ዘፋኝ ነው፤ ትናንትናና ዛሬ ላይ ያሉ ዘፋኞችንና አድማጮችን አንድ ስሜት ውስጥ በአዲስ ሙዚቃ ማስተሳሰር የሚችል?

የትኛው ነው ትክክል፤ የዛሬው ሙዚቃ ወይስ የትናንቱ፤ ምናልባት ሁሉንም እንደዬ ዘመኑ መለካትና መመልከት አስፈላጊ ነገር ሊሆን ይችላል።

አሁንም እኔ የምለው የአገራችን ሙዚቃ የት ላይ ነው ያለው?? በብዛት አሁን እየተደመጡ ያሉት ሙዚቃዎች ባሕል ዘመናዊ ተብለው የሚጠሩትና እስክስታ የበዛባቸው ናቸው። ከዚህ ውጭ ያሉት ከቴዲ አፍሮና ከሌሎች ውስን ድምጻዊያን በቀር እስክስታ ከሌላቸው የማይደመጡ ሆነዋል።

ምናልባት አሁን ካለው ስርዓት ጋር አብሮ የሚራመድ ይሁን አላውቅም፤ ሙዚቃው የብሔረሰብ የሚመስል መልክ አለው።ብዙ የብሔረሰብ ሙዚቃዎች እየተሰሩ፤ እየተደመጡ ናቸው።

ቀደም ብዬ መግቢያዬ ላይ ያልተደመጡ የሙዚቃ አልበሞች በሚል የጠቀስኋቸው ዘፋኞች እነዚህን ጉዳዮች የሚያስዳስሱ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ።አሁን ላይ ዘመናዊ ብቻ ሙዚቃ አዋጭ አይደለም፤ ዘመኑ እስክስታ ይፈልጋል ማለት እንድደፍር አድርጎኛል።ሌሎች የግጥምና የዜማ ሥራዎች ተጠናቀው መሠራት እንዳለባቸው ሆኖ።

ይህ እንዳይባል ደግሞ አሁን ላይ እስክስታ ብቻ ዘፍነው ያልተደመጠላቸው እንዳሉ ሁሉ፤ እስክስታ የሌለው ሙዚቃ አዚመው እየተደመጠላቸውና እየተወደደላቸው ያሉ ዘፋኞች አሉ። የእሱባው አልበም ለዚህ ማሳያ ነው።

የሙዚቃ አድማጩን ስሜት ማወቅ ቢቸግርም እንኳን የገበያ ጥናት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ አምናለሁ፤ ሙዚቃ የነፍስ መሆኑ ቀርቶ የብር እስከሆነ ድረስ፤ ጥሩ ሙዚቃዎችን ሰርቶ የተሻለ ተደማጭነትን ማግኘት ይበጃል።ለሙዚቃውም እድገት ሚና ይኖረዋል።

መልካም ጊዜ ይሁንላችሁ።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!