“የቴዎድሮስ ራእይ” ትያትር

“የቴዎድሮስ ራእይ” ትያትር በአምስተርዳም ከተማ፣ ሆላንድ፤ ሴፕቴምበር ፳፫ ቀን ፳፻፲፯ እ.ኤ.አ.።

ክንፉ አሰፋ

በታሪከኛዋ አምስተርዳም ከተማ በሚገኝ አንድ የሲኒማ ማዕከል ውስጥ የአበሻ ዘር ታጭቋል። ቲያትር ቤቱ ጢም ያለው ቲያትሩ ከመጀመሩ ከሰዓታት በፊት ነው። ወትሮውን በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያዊ በግዙፍ አዳራሽ ውስጥ ሞልቶ የሚታየው በጸሎት ቤቶች ብቻ ይመስለኛል። ምሽት ላይ የሚደረጉ የአበሻ ኮንሰርቶችም ቢሆኑ አረፋፍደው ነው የሚሟሟቁት። በዚህኛው እንግዳ ክስተት አግራሞቴን ገና ሳልጨረስ፣ ሌላ ነገር አየሁ። ትያትሩን ጨርሼ ስወጣ በሩ ላይ ሕዝብ ለሁለተኛው ዙር ተሰልፏል። … ከሰዓት እረፍት በኋላ “የቴዎድሮስ ራእይ”ን በአምስተርዳም ደገሙት!

የኢትዮጵያ ቲያትር በሆላንድ አገር ሲታይ በታሪክ ይህ የመጀመርያው ነው። ቲያትሩ “የቴዎድሮስ ራእይ” መሆኑ ደግሞ ከስኬቱ ጋር ተዳምሮ በሁሉም ዘንድ ልዩ ስሜት የፈጠረ ይመስላል። በጌትነት እንየው ጸሐፊነት፤ በጣይቱ ማዕከል አዘጋጅነት የቀረበው ይህ ቲያትር፤ በዓለምፀሐይ ወዳጆ መሳጭ ትረካ ይጀምራል። ከዚያም በእነ ገብርዬ ጣፋጭ ወግ ዘና እያደረገ ያቆየንና፤ መልሶ ደግሞ ቁጭት ውስጥ ይከትተናል። ገብርዬን ሆኖ የተጫወተው ራሱ ጌትነት እንየው ነው።

“ትልቅ ነበርን፤ ትልቅ እንሆናለን!” ይለናል የቋራው አንበሳ። አንድ በነበርንበት ወቅት ምን ያህል ኀያል መሆናችንን ላላስተዋለው፤ ለዚህ ትውልድ ይህ መልዕክት የንዴት ስሜትን ብቻ ፈጥሮ አላለፈም። መልእክቱ በእያንዳንዱ ተመልካች ልብ ውስጥ የቁጭትን አዝመራም ዘርቷል።

በሰዎች ተገፋፍቶም ይሁን፤ አልያም ሰው ለማግኘት ሲል ወደ አዳራሹ የታደመ ተመልካች ሊኖር ይችላል። እርግጠኛ ሆነን መናገር የምንችለው ግን ተመልካቹ ሁሉ፤ ኀዘኑን በልቅሶ፣ ደስታውን በጭብጨባ እየገለጸ፤ አዳራሹን ያናጋው ነበር። ቁጭትን ያልሰነቀ አልነበረም። ማንነትን እየተፈታተነ የሚገነፍል የወኔ አቶን በደስታ እና በኀዘን ሲቃ የተደበላለቀ ሲወጣ በግልጽ ይታያል።

በትያትሩ ሂደት ውስጥ እየተፈራረቀ የሚከሰተው የደስታ እና የኀዘን ስሜት፤ የተመልካቹን ቀልብ ወጥሮ ይዞት ነበር። ይህ በእያንዳንዱ ልብ ውስጥ የሚጉላላው የቁጭት ሐሳብ ስሜትን እየኮረኮረ ይጓዝና ወደ መሃል ዘለቅ ሲል አንድ ጥያቄ መጫሩ አይቀርም። “ይህ ትያትር ’የቴዎድሮስ ራእይ ነው’ ወይንስ ’የቴዎድሮስ ፈተና’?” የሚል ጥያቄ።

ዘመኑ የርስ-በርስ መባላት ነበር። ዘመኑ አገራችን በውጭ ወራሪዎች ጥርስ ውስጥ የገባችበት ወቅት ነበር። ሕዝቡም ዳር እስከዳር በአጼው ላይ የተነሳበት፣ በአጠቃላይ ”ክፉ” የሚባል ወቅት ነበር። ይህ ሁሉ ቁልል ችግር ያለው አጋዥ ሚስቱ ተዋበችን በተነጠቀው፤ በአጼው ጫንቃ ላይ ነው። የቋራው አንበሳ ዘመኑን ለመዋጀት የሚወጣው አቀበት እና የሚወርደው ቁልቁለት ቲያትሩ በቀላል የትወና ጥበብ ያሳየናል።

“የቴዎድሮስ ራእይ” በረቀቀ ጥበብ ያታጀበ ትያትር መሆኑን የምንገነዘበው በእንደዚህ ዐይነቱ የተመልካቾች ስሜት ነው። የስሜቱ መጠን እና ዐይነት የሚለካው፤ በእያንዳንዱ ተመልካች የታሪኩን አረዳድ ደረጃ መሆኑ እንዳለ ሆኖ። አንዳንዶች ከት ብለው ይስቃሉ፣ ሌሎች ያለቅሳሉ፣ ገሚሶቹ ደግሞ በቁጭት ጥርስ ያፉዋጫሉ።

ያም ሆኖ የራዕዩ ምስጢር የሚገባኝ ትንሽ ዘግየት ብሎ ነው። በንግሥናው ዘመን “እወድሻለው!” የሚላት አገሩን በእልፈተ ሕይወቱ ቅጽበትም ይደግመዋል። አጼ ቴዎድሮስ በእንግሊዝ ጦር ጉልበቱ በተፈታ ወቅት እጁን ለግዞት አልሰጥም ብሎ በራሱ ላይ ሲጨክን፤ ቃሉን በተግባሩ ሲያጸናው እናያለን። ትልቅ ሆና ማየት የሚሻት ኢትዮጵያን “እወድሻለሁ!” እያለ ሽጉጡን ጠጥቶ በክብር አለፈ። የእሱ ራእይ ለዘመናዊዋ ኢትዮጵያ የመሰረት ድንጋይ መጣሉ ብቻ አይደለም፣ ይህ ንጉሥ ለነጻነት ሲል ራስን ሰውቶ በክብር የመኖር ተምሳሌት መሆኑም ነው።

ዓለምፀሐይ ወዳጆ በየመሃሉ ብቅ እያለች ታሪኩን ትተርካለች። እንደጅረት የሚፈሰው እንባዋ ከሚነድደው ከአገር ፍቅር ስሜት የተነሳ ነውና፤ እስዋን የተመለከተ ሁሉ ልቡ እየተነካ ሳያስበው ያነባል። ይህች ውድ የጥበብ ሰው ይህንን ታሪካዊ ትያትር ይዛ አትላንቲክን ስትሻገር፤ በውስጥዋ የሚግለውን የአገር ፍቅር እና አንድነትን ሰንቃ የመጣች መሆኑን ስሜትዋ ብቻ ሳይሆን፤ ተግባርዋም ይነግረናል። በቴዎድሮስ ራእይ የቲያትር ጉዞ፣ አብረዋት የሚዞሩት የጥበብ ሐዋርያትም ግዜያቸውን፣ እውቀታቸውን፤ እንቅልፋቸውን እና ገንዘባቸውን መስዋዕት ማድረጋቸው ያለ ምክንያት አይደለም።

ትናንትናችን ብለን እንደዋዛ ያሳለፍነው ያ ክፉ የክፍፍል ዘመን፣ እነሆ ዛሬያችን ላይ መደቀኑ እንቅልፍ ይነሳል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!