”ኖረ”

ፊልጶስ ከሆላንድ

በልቶ ጠግቦ አደረ ምንም ሳይርበው

ወይም አልጠግብ ባይ ቁጣን አመመው

ጠፍቶ የሚቀምሰው ወይም ጠኔ ጣለው፤ …

ሲቀረሻ ዋለ ካላቅሙ ጠጥቶ

ወይም ደርቆ ዋለ ጉሮሮው ውሃ አ’ቶ፤ …

ምርጥ - ምርጥ ለበሰ እጅግ አማረበት

ወይ እርቃኑን ሄደ ቡቱቶው አልቆበት፤ …

ሲፈነጥዝ ታየ ደስታ ፈነቀለው

ወይም ኀዘን ችግር ባልንጀራ አ’ረገው፤ …

ህሊናውን ሸጦ - ላላፊ ጥቅም ለውሸት አደረ

ከሕግ በላይ ሆኖ በሥልጣን ባለገ - ፍትህን አሰረ

ወይ ሳያወላውል ጊዜ ሳይለውጠው ከእውነት ጋር አበረ

በአግባቡ ፈረደ - ትህትናን ተሞልቶ ህዝብን አከበረ፤ …

በቁሙ የሚሞት - እየሞተ እሚኖር ፈሪ ሆነ ‘ርብትብት

ወይም ቆራጥ ጀግና ባላማው የፀና - የማይፈራ ሞት፤ …

ት’ግስተኛ አዋቂ እጅግ ደግ የዋህ ነው - የለበሰ ፍቅርን

ወይም ”ጠብ ያለሽ በዳቦ” ችኩል ጨካኝ ይሁን፤ …

ብቻ … በምድር ላይ እስትንፋስ ካለው

እንደ አፈጣጠርም ሥራም ዥንጉርጉር ነው

ከመሸም ከነጋ ውሎ ካደረ ሰው

ስሙ መጠሪያው ለሁሉም የወል ነው

ጥንትም ሆነ ዛሬ ”ኖረ” ነው እሚባለው።


 

ፊልጶስ ከሆላንድ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ