አራት ኪሎ

ብርዞ

የጀግኖች ሰማዕት ካንቺ ከፍ ብሎ

በክብር ለሞተ ለሀገሩ ተጋድሎ

የየካቲት ኃውልት ከጎንሽ ተተክሎ

ባንዳው ከረመብሽ ምነው አራት ኪሎ

 

የዘረኛ መንጋ ወሮሽ አራት ኪሎ

እየዋሸ ያድራል ሲያሴርብሽ ውሎ

የታሪክ ውራጁ ብረቱን ተማምኖ

ሕጉን ጨፈለቀ ቃሉ ጥይት ሆኖ

 

ከአራት ኪሎ ግቢ የነገሠው ውሸት

በማሳፈር ፈንታ ያሳብጣል ዕብሪት

የታጠበ በጨው ያ ዓይነ ፈጣጣ

ዘባርቆ ቢለግግ ከእውነቱ ቢወጣ

ዘልቆ ላይሻገር ተጉዞ ላይገፋ

ይቀደድ ይተርተር ላይሆንለት ይልፋ

 

የሂሳብ ሕጋግት የስሌቱን ቀመር

ሲበዛ ሲቀነስ ካልሆነም ሲደመር

ባለፈውም ሆነ በቀጣዩ ነገር

ከረሃብ ተውሶ ለዕድገቱ መጨመር

ከአራት ኪሎ ግቢ የስጦች ጎተራ

ተሰፍሮ እየወጣ ቢነዛ ቢወራ

በሞቱ ቢቀለድ ህዝቡ ባይፈራ

መብቱ ቢሾፍበት ቢገፋ ከሀብቱ

ቢላገጥበትም ቢበዛ እንግልቱ

እንኩዋን ሊቀምስና ሊልሰውም ቀርቶ

ሊያየው ያልታደለ አንድ ጥሬ አጥቶ

የረገፈው ሕፃን አረጋዊው ሳይቀር

የእህል ውሃ ፍርጃ የመከራ በትር

ቀጥፎት ያለቀኑ ያደረገው አፈር

የአራት ኪሎ ዋሾ ጅቡ ሲቀባጥር

አስፈንዳቂ ዕድገት ደስታ ጥጋብ ነበር

 

ቁልፉ ቢበጣጠስ ሸሚዝ ተገፍትሮ

ቤተመንግሥት ድግስ ሆዱ ተወጥሮ

ለአረቄ ያደረ ህሊናውን ታስሮ

በክህደት ያነጋ ሐቅን ተሰውሮ

አስራ ስምንት ዓመት ዋሽቶ ያልጠረቃ

ስግብግብ ዘረኛ የባዕድ ጠበቃ

ሃክ እንትፍ ተብሎ የተወረወረ

ወሬውና ስሙ ሥራው የመረረ

ነውረኛ ጸያፍ ግብረገብን ያጣ

የማይጠራ ጉድፍ የርጉም ቀን ዕጣ

 

ሥልጣኑን ሊያስረክብ በአፉ ወለምታ

ሲደነፋ ከርሞ ሲያብል ሲያምታታ

ሊቅ ጠፋ ተብሎ ተኪ በሱ ፈንታ

የምርቃናው ዶሴ በጨብሲ ተፈታ

በአናተ ዱሽ መሃል ስለተወተፈ

አንድ ጣት በምን ቤት ሆነና አረፈ

 

ሽምጠጣና ዕብሪት ጭካኔና ቅጥፈት

ማፈንና መግደል ማሰር ማሰቃየት

በዝርፊያ ዘመኑ ልምዱን ያዳበረ

ዓለምን የናቀ ሕግ ያላከበረ

ፍርዱን የሚጠብቅ ተስፋው የኮሰሰ

ለጋ የቀጠፈ ነፍስን ያረከሰ

የዘመን ኋላ ቀር የትውልድ ነቀርሳ

በደም ተጨማልቆ ግፉ ሳይረሳ

ከዙፋኑ ወርዶ ሳምንት እንደማይዘልቅ

ጊዜ ፊት አዙሮ እንደሚጠፈር ሲያውቅ

ምን አርጎ ይወርዳል ያጃጅላል ሰው

ክፋቱ ወጥሮት ተንኮሉ ሥራው

ሰፍሮ በአናቱ ላይ እስከሚፈነዳ

አይቀጥልም ጉዞው ዘረኛው ይረዳ

ይቀምሳል አይቀርም የቻውቼስኮን ፍዳ


 

ብርዞ - መስከረም 21 ቀን 2001 ዓ.ም. (01/10/2009)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ