ዘፍናችሁ ቅበሩኝ (ዳግማዊ ዳዊት)
ዘፍናችሁ ቅበሩኝ
ዳግማዊ ዳዊት መስከረም 2002 ዓ.ም. This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ሰውን ሰው አሳዶ - ቢያሳጣው መድረሻ
ጭንቅ ብርክ አስይዞ - ፍፁም መተንፈሻ
ሚሊዮኖች ቢያልቁ - በረሃብ በበሽታ
ጦርነት ቢመረጥ - በሠላሙ ፋንታ
…
መስማማት ተጠልቶ - መናቆር ቢሞገስ
ቅደሱ ቢረክስ - ርኩሱም ቢቀደስ
ሕግ የጉልበት ሆኖ - ፍትህም ተጠልፎ
አስታራቂ ጠፍቶ - ዳኝነት ተገፍፎ
መስገብገብ ሕግ ሆኖ - ሙስና ተለምዶ
ቅጥፈት ተሞካሽቶ - እውነትም ተዋርዶ
ቀማኛን ሆነና - የሚሰማ ጆሮ
ቁብ የሚለው ጠፋ - የደሃን እሮሮ
እጥፍ ድርብ ሆነ - ሰቆቃው ጨመረ
ዓይኔን እንባ ሞላው - ልቤ ተሰበረ።
አንገቴን ደፍቸ - መሬትን እየጫርኩ
መሞት እንደምሻ - ለአምላኬ እየነገርኩ
ፀሎቴ ተሰምቶ - አርጎ ሰማይ
ሞቴ ደረሰልኝ - ይህን እንዳላይ።
ዛሬ መሄጃዬ - ተራዬ ነውና
ከየመንደራችሁ - በጠዋት ውጡና
ሸኙኝ ጨፍራችሁ - በዘፈን በዜማ
ሞትን መርጫለሁ ይህን ከምሰማ።
እናቴ አታልቅሽ - አይመታ ደረት
አባቴም አትተክዝ - እኔስ ልሂድበት
ትቸው የምሄደው - የምተወው ዓለም
ከሞት የባሰ እንጅ - የተሻለ አይደለም።
ፅድቅና ኩነኔ - ቢኖርም ባይኖርም
ለእኔ እዚህ መኖሬ - ከሞት አይሻልም
እኔስ በፈጠረኝ - እመካለሁና
ሕይወት ይኖረኛል - ገነት እንደገና።
አልያም …
ሚካኤል ከበሩ - ባይቀበለኝም
አቡዬን ተክልዬን - ላያቸው ባልችልም
ገነት መግባት ቀርቶ - ገሃነም ብወርድም
ቁርጥ ያጠግባልና - አማረ አላማረም
ከመሞት መኖርን - በፍፁም አልመርጥም
የዚህ ዓለም ኑሮ - የአምሳያዬ ግፉ
ሞትን አስመረጠኝ - ተሽሎኝ ማረፉ።
እናም አታልቅሱ - አልሰማ ዋይ ዋይታ
በምትኩ አሳዩኝ - ዘፈንና እስክስታ
ክራር ጽናጽሉ - ከበሮው ይመታ
በገና ይደርደር - አስራ ሁለት ተርታ
ይነፋ ዋሽንቱ - ሳክስፎን እምቢልታ
ወንዶቹ በሆታ - ሴቶቹ በእልልታ
የዛሬን - የዛሬን - እኔን ደስ እንዲለኝ
ማልቀሱን ተዉና - ዘፍናችሁ ቅበሩኝ።
ዳግማዊ ዳዊት መስከረም 2002 ዓ.ም. This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.