(ማሳሰቢያ፤ ያገሬ ባላገር “እገሌ ቦለቲኸኛ ነው” ካለ ውሸታም ነው ማለቱ እንደሆነ እናውቃለን። አባባሉን ዓለም የሚስማማበት ይመስለኛል። ቅኔው በጅምላ በዓለም ፖለቲከኞች ጭምር ላይ የቀረበ ስለሆነ ምናልባት ባገራችን በተቃዋሚ ጎራ ያሉ ከልብ የሚደክሙ በጣም ጥቂት ትጉኀን ፖለቲከኞችን ካስቀየመ አስቀድሜ ይቅርታ እጠይቃለሁ። በተቃውሞ ጎራ ካሉት ውስጥ የሚበዙት ኃይላቸውን አጠናክረው ገዢውን ፓርቲ ወደ ሕግ ስር ከማምጣት ይልቅ እርስ በርስ በመጎናተል የሚያባክኑት ጊዜ ቅር ስለሚያሰኘኝ ነው ይህን ቅኔ የተቀኘሁት። ለዚያውም የባላገሩን አባባል ስለምጋራ እኔ መልክና ቅርጽ ሰጥቼ ተቀኘሁለት እንጂ አባባሉ የሱው (የባላገሩ) ስለሆነ እኔ አዲስ ነገር አላመጣሁም።)

ቦለቲኻ

(የአማርኛ መወድስ)

ቦጋለ በየነ

 

ስልቻ ቀልቀሎ* ወይም ቀልቀሎ ስልቻ፤

ፖለቲክስ ውሸት፤ ውሸት ፖለቲክስ ቅራቅንቦ

አይለያዩም ሁሉም የሁለት እግር አልቦ።

አያልቅም ስንክሳራቸውም ተነቦ ተነቦ፤

ውሸት ውሸትን እንጂ፤

አይወልድምና ሐቅን ሺ ቢፈላሰፍ ተጠቦ።

 

ለዓለም

 

ሸማኔሂ ፖለቲከኛ ጥበብ ሊሠራ አስቦ፤

አልቻለም ድሩን ሊያጠነጥን ባንከርት በዋግንቦ።**

አጥፍቶታልና ውሉን ፈትሉን በጣጥሶ፤ ተብትቦ።

በሙሬ ጠርጋችሁ ድውሩን ውሉን ፈልጉ እስቲ ባ’ቦ።

 

ቦጋለ ዳኜ ከካሊፎርንያ፤ ጥቅምት 2002 ዓ.ም.

 

* ኦሮም ቀልቀሎ ያለውን አማራ ስልቻ ይለዋል። ሃሳቡ አንድ ሆኖ ሳለ ሁለት ነው ተብሎ አንድ ነገር ሲቀርብ ቀልቀሎም ተባለ ስልቻ ሁለቱም ያው ነው ለማለት የምንጠቀምበት ዘዬ ነው።

** አንከርትና ዋግንቦ ሸማኔ ድር የሚያዳውርባቸው ባህላዊ መሣሪያዎች ናቸው።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ