ውሸት ነገሠ

ዳግማዊ ዳዊት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

መስቀል አደባባይ - ሀዝባችን ተጠርቶ

ሕፃን ሽማግሌው ባልቴት እና አዋቂው -

ግልብጥ ብሎ ወጥቶ

የክብር እንግዶች - ከአውሮጳ ከእስያ

ከጎረቤት ሀገር - ጅቡቲ ኬንያ

የአሜሪካው ቆንሲል - ሚስተርም ተገኝተው

ጳጳሱ ተጠርተው - ካህናት ቀድሰው

ቅባ-ቅዱስ ፈልቶ - በአናቱም አፍስሰው

አክሊል ተደፋለት - እምቢልታ ተነፋ

ህዝብ ሠገደለት - ሥልጣን ክብሩ ሰፋ

ከበሮ ተመታ - ሆታውም ቀለጠ - እልልታ ተሰማ

ውሸት ንጉሥ ሆነ - ስርቆት አልጋ ወራሽ - በሀገሬ ከተማ።

 

እናም የእኛ ሰፈር - ትልቅ ሽማግሌ

አንቱ የተባሉት - ትናንት እና ዛሬ

በቁርባን ያገቡት - በክርስትናቸው

ይኸው በአደባባይ - ሲዋሹ ያዝናቸው።

 

መቸ ይኸ ብቻ - ሆነና ነገሩ

በሃሰት ተከስሰው - ተሰማና ፋይሉ

ደግነት ቅንነት - እስር ቤት ገቡ አሉ።

 

እንግዲህ ምን ይሉ - ዘመን ተቀየረ

ውሃ ሽቅብ አይፈስ - ሲባልም ነበረ

ዘመን ተገላብጦ - ውሸት ተከበረ።

 

ኑሯችን ሆነና - ከደሃው ቀምተን

እውነትን ንቀነው - ውሸትን አንግሠን

ወደፊት ለመሄድ - መራመድ አቃተን።


ዳግማዊ ዳዊት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

የካቲት 2002 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ